መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ዓለም እና ተገኘወርቅ የሌዘር ምርቶች ማምረቻ

ዓለም እና ተገኘወርቅ የሌዘር ምርቶች ማምረቻ

ዓለም እና ተገኘወርቅ የሌዘር ምርቶች ማምረቻ የኅብረት ሽርክና ማኅበር የተመሠረተው በአቶ ተገኘወርቅ ጫንያለው በ2008 ዓ.ም. ነው። ይህ ድርጅት አጠቃላይ የቆዳ ውጤቶችን በጥራት የሚያመርት ድርጅት ሲሆን በይበልጥ ደግሞ ጫማዎችን በስፋት እያመረተ የሚገኝ ድርጅት ነው።

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች

  • የሴት ጫማ እና ቦርሳዎች
  • የህጻናት ጫማዎች
  • የወንዶች ቦርሳ እና ጫማዎች እንዲሁም የላፕቶፕ መያዣ ቦርሳዎችን ያመርታል።

የሚያመርታቸው ምርቶች ዋጋ

  • የወንዶች ቦርሳ ከብር 800 (ከስምንት መቶ ብር) እስከ ብር 1,500 (አንድ ሺሕ ዐምስት መቶ ብር)
  • የሴቶች ቦርሳ ከብር 800 (ከስምንት መቶ ብር) እስከ ብር 1,500 (አንድ ሺሕ ዐምስት መቶ ብር)
  • የወንዶች ጫማ ከብር 800 (ከስምንት መቶ ብር) እስከ ብር 1,200 (አንድ ሺሕ ሁለት መቶ ብር)

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

ድርጅቱ የተመሠረተው በሁለት መሥራች አባላት ነበር። አሁን ላይ የመሥራች አባላት ቁጥር ወደ ዐምስት ከፍ ብሏል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ድርጅቱ ለሰባት ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፤ የካፒታል አቅሙንም ወደ ብር 500,000 (ዐምስት መቶ ሺህ ብር) አሳድጓል። ድርጅቱ አሁን ባለው የማምረት አቅም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሦስት መቶ ቦርሳዎችን ማምረት ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ባለው ሰፊ የመሥሪያ ቦታ እና በቂ የሰው ኅይል አቅርቦት ከዚህ የበለጠ ሥራ ከመጣ አስፈላጊውን የሰው ኅይል በመቅጠር መሥራት ይችላል።

ድርጅቱን ምርቱን ለማስተዋወቅ ባዛር፣ ቢዝነስ ካርድ፣ የምርት ማሳያ ሱቅ ይጠቀማል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ መርካቶ አካባቢ የሚገኙ ሱቆች በመሄድ ምርቱን ይሸጣል። እንዲሁም ደግሞ አንዳንድ ደንበኞች እየመጡ የሚገዙ አሉ።

የድርጅቱ መሥራች ወደ ቆዳ ሥራ የገቡበትን አጋጣሚ እንዲህ ሲሉ ነበር የገለጹት። ይህን ሥራ መሥራት ከመጀመራቸው በፊት የታክሲ ሥራ ነበር የሚሠሩት። በሆነ አጋጣሚ ቤተሰብ ለመጠየቅ አንድ ዘመዳቸው ጋር ሲሄዱ ዘመዳቸው ጫማ ሲሠሩ ያገኟቸዋል። በጣም ይገረሙና ጫማ ሀገራችን ይሠራል እንዴ በማለት ይጠይቃሉ። እሳቸው በፊት የጫማውን ሶል ሲመለከቱ የጣልያን ስለሚል ጫማ እዚህ ሀገር እንደሚሠራ በፍጹም ገምተውም አያውቁም ነበር። ከዛም በእዛ ድርጅት ውስጥ ኅላፊ ሆነው ተቀጠሩ። ካላቸው ፍላጎት ሥራውን ስለወደዱት በደንብ አብረው መማር ጀመሩ። በደንብ መሥራት ሲችሉ ሀገር ውስጥ የሚሠሩት ጫማዎች በብዛት የሚሠሩት በልምድ ስለሆነ ብዙም ውበት የላቸውም፤ ስለዚህ ዕውቀት እንዲኖረኝ ብማር የተሻለ ነው ብለው ለመማር ወስነው በጊዜው በሀገራችን የሌዘር ኢንስቲቲዩት ተከፍቶ ሥልጠና ሲሠጥ እሳቸውም በ1997 ዓ.ም. አራተኛ ዙር ሠልጣኝ ሆነው ለአንድ ዓመት ተማሩ። ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ደግሞ ተሸላሚ ተማሪ ስለነበሩ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ለአንድ ዓመት አስተምረዋል።

አቶ ተገኘ ከአስተማሪነታቸው በኋላ ከጓደኛቸው ጋር በመሆን ይህን ድርጅት መሥርተዋል። ድርጅቱ አሁን ከሚያመርታቸው ምርቶች ውስጥ በስፋት በጫማ ላይ እየሠራ ይገኛል። ይህ ድርጅት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በጨረታ ላይ የመሳተፍ እድሉ አልነበረውም። ሰዎች ተሳትፈው የሚያመጡትን ጨረታ ነበር የሚሠሩት ይህም ከሦስት እስከ አምስት የሚደርስ ሰንሰለት በውስጡ የያዘ ስለሆነ ብዙ ትርፋማ አያደርጋቸውም። ከጨረታ በደንብ የመጠቀም እድሉ አልነበራቸውም። አሁን ግን 2merkato.com ለጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ያዘጋጀውን የከፍታ አገልግሎት ፓኬጅ በመጠቀም ጨረታዎች እየተከታተሉ ይገኛሉ።

የኮቪድ ተፅዕኖ

በኮቪድ ሥራ ሙሉ በሙሉ ቆሞ ነበር። በዚህ ጊዜ የድርጅቱ አባላት በግል ሳኒታይዘር እና ማስክ በመሸጥ በግላቸው የራሳቸውን ኑሮ ለማሸነፍ ሲሠሩ ቆይተዋል። በተጨማሪ የቤት ኪራይ መክፈል ስላልቻሉ የመሥሪያ ቦታው ለአንድ ዓመት ታሽጎ ነበር። በኮቪድ ከባድ ጊዜ ካሳለፉ በኋላ አሁን ጀሞ ላይ ከመንግስት ሼድ ተሰጥቷቸው በጥሩ ሁኔታ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

ምክር እና ዕቅድ

አዲስ ወደ ዘርፉ የሚገቡ ሰዎች መገንዘብ ያለባቸው ነገር ገበያው ገና ያልተነካ እንደሆነ ነው። አንድ መቶ ሃያ ሚሊዮን ሰው አለ፤ በዓመት ሦስት ጥንድ ጫማ ቢያደርግ በአንድ ዓመት ብቻ ሦስት መቶ ስልሳ ሚሊዮን ጥንድ ጫማ ያስፈልጋል። ስለዚህ በዘርፉ ብዙ የሥራ ዕድል አለ። የሀገር ውስጥ ገበያ ብቻ ገና ምንም አልተነካም ። ነገር ግን አስመጪዎች የግላቸውን ጥቅም በማሰብ እንዲሁም አንዳንድ የመንግሥት አሠራሮች አስቸጋሪ በመሆናቸው (ለምሳሌ አንድ ማሽን ለማስገባት በግል ከሆነ ቀረጡ ብዙ ነው በመንግሥት ደግሞ የማይሆን ማሽን ይመጣና ከተበላሸ መለዋወጫ አይኖረውም) ሥራ ለማስፋፋት አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። መንግሥት ለእነዚህ ችግሮች ላይ ቶሎ መፍትሔ ቢያገኝ የጫማ ሥራን ለማሳደግ በጣም ጥሩ ዕድል አለ ብለው ያምናሉ።

ድርጅቱ ወደ ፊት ዘመናዊ የሆኑ ማሽኖችን በማስገባት ወደ ፋብሪካ ደረጃ የማደግ እና አሁን ባለው የኑሮ ውድነት ጫማ መግዛት ለማይችሉ ሰዎች ከኮቪድ በፊት ጀምሮት የነበረውን የብድር ጫማ እንደገና ለመቀጠል እቅድ አለው። የብድር ጫማ ማለት አንድ ሰው ጫማውን ከገዛ በኋላ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ከፍሎ ዕዳውን የሚጨርስበት የሽያጭ ዓይነት ነው።

አዲስ ወደ ዘርፉ የሚገቡ ሰዎች በጫማ ሥራ ገና ገና በጣም ብዙ መሥራት ይቻላል፤ ግን ጥንካሬ እና ዕውቀት ሊኖቸው ይገባል ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።

የድርጅቱን አገልግሎት መጠቀም የሚፈልጉ የድርጅቱን ስልክ በዚህ ሊንክ በመግባት ዓይተው መደወል ይችላሉ

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …