መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ዓለም ግዛቸው ልብስ ስፌት
alem garment

ዓለም ግዛቸው ልብስ ስፌት

ዓለም ግዛቸው ልብስ ስፌት የተመሠረተው በ 2011 ዓ.ም በ ወ/ሮ ዓለም ግዛቸው የግል ኢንተርፕራይዝ ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የልብስ ስፌት ሥራዎችን የሚሠራ ድርጅት ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የልብስ ስፌት ሥራዎችን የሚሠራ ድርጅት ቢሆንም በብዛት ግን የህጻናት አልባሳትን ነው የሚሠራው። ከአራስ ጀምሮ እስከ ሥራ አራት አመት ለሚገኙ ህጻናት የሚሆኑ ልብሶችን በብዛት ያመርታል።

ድርጅቱ ከሚያመርታቸው ምርቶች መካከል

  • የህጻናት የወንዶች እና የሴቶች አልባሳት
  • የአዋቂዎች አልባሳት
  • የወንዶች እና የሴቶች የሀበሻ አልባሳት
  • አጠቃላይ የአዋቂዎች አልባሳት
  • የተለያዩ የሶፋ ጌጣጌጦች
  • ማስኮች
  • ማንኛውም ቦርሳ፣ ቀበቶ በጥራት ያመርታል

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

ወ/ሮ ዓለም ድርጅቱን ከመመሥረታቸው በፊት የመንግሥት ሥራ ነበር የሚሠሩት፤ በነበራቸው ትርፍ ሰዓት ደግሞ ቀለል ቀለል ያሉ ሥራዎችን ቤታቸው ይሠሩ ነበር። ይሁን እንጂ ከሃያ አመት በላይ የዳይሬክተር ጸሐፊ ሆነው የመንግሥት ሥራ ሲሠሩ የቆዩ ቢሆንም በቂ ገቢ ግን ልያገኙ አልቻሉም። ይህንም ለማስተካከል ቦሌ አካባቢ በሚገኘው ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ ለሦስት ዓመት የልብስ ሥፌት ትምሕርት ተምረው ካጠናቀቁ በኋላ የሥራ መልቀቂያ በመጠየቅ ወደ ልብስ ስፌት ሥራ ሊገቡ ችለዋል። የትምሕርት ማስረጃቸውን ይዘውም የመሥሪያ ቦታ ሲጠይቁ ተሰጣቸው በፊት እቁብ በመጣል ማሽኖች ገዝተው ስለነበር የተሰጣቸው ቦታ ላይ በመሥራት በጣም ውጤታማ መሆን ችለዋል። በመንግሥት ሥራ ከሃያ ዓመት በላይ ቆይተዋል ነገር ግን አንድ ሺህ ብር እንኳን መቆጠብ አልቻሉም ነበር። አሁን የሀምሳ ሺህ ብር ካፒታል እና ለአንድ ሠራተኛም የሥራ እድል መፍጠር ችለዋል። ከወረዳው ሁለት ጊዜ ተጠርተው መሠረታዊ ሥልጠናዎችን ወስደዋል፤ እነዚህም ሥልጠናዎች ስለ ገንዘብ አያያዝ፣ ገበያ ጥናት፣ ምርት አጠቃቀም እና ተያያዥ ነገሮች ስለሆኑ በጣም ጠቃሚ ናቸው። አሳቸውም በሚገባ ተግብረዋቸዋል።

ወ/ሮ ዓለም ስለ ትምሕርት የሚከተለውን ብለዋል “ትምሕርት የሚጠቅመው የምርት ብክነትን ለመቆጠብ ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው አንድ ቀሚስ ለመስራት ሁለት ሜትር ተኩል ጨርቅ ሊፈጅ ይችላል። ከተማረ ግን በአንድ ሜትር ጨርቅ እንዴት አድርጎ የዲዛየን ፓተርኖችን አብቃቅቶ ማስቀመጥ እንዳለበት ስለሚያውቅ  በአንድ ሜትር ጨርቅ ቀሚስ ማውጣት ይችላል። ይህ ደግሞ አላስፈላጊ ብክነትን ወይም ወጪን ይቆጥባል።”

የድርጅቱ አቅም ከአንድ ወደ ስድስት ማሽኖች አድጓል። በቀን ዐሥራ አምስት ልብሶችን የማምረት አቅም አለው። እንዲሁም ሁለት የጅምላ ተረካቢ ደንበኞችን አፍርቷል። ወ/ሮ ዓለም በአጭር ጊዜ ውጤታማ ሊሆኑ የቻሉት ለሥራው ትልቅ ፍላጎት ስለነበራቸው ነው። እሳቸው ሥራውን ሲጀምሩ ገንዘብ ላይ ሳይሆን ሥራው ላይ ነበር ትኩረታቸው፤ እንዴት ላሻሽለው የሚለውን ነገር ከሰዎች ጋር በመነጋገር፤ ልምድ በመቅሰም የሥራው ጥራት ላይ በጣም ይሠሩም ነበር ይህም ጥሩ ውጤት አሳይቷል። ድርጅቱ አሁን ሥራዎችን የሚሠራው በሰው በሰው ነው።

የኮቪድ ተፅዕኖ

ኮቪድ ለድርጅቱ መሥራች ጥሩ አጋጣሚ ነበር። እሳቸውም በአጋጣሚው በመጠቀም ማስኮችን እና ሌሎች የልብስ ሥራዎች በመሥራት ተጨማሪ የልብስ ስፌት ማሽኖችን መግዛት ችለዋል።

ምክር

ማንም ሰው ለሚሠራው ሥራ ድፍረት ያስፈልገዋል። እንዳንድ ሰዎች ዕውቀት እያላቸው የሚፈሩ ሰዎች አሉ፤ ገንዘብ የለኝም እቃው የለኝም ብለው። ምንም ባይኖራቸው እንኳን በትንሹ የሚፈልጉትን ሥራ ለመሥራት የሚያስችል የመጀመሪያውን እርምጃ ከተራመዱ ቀስ ቀስ በቀስ ማደግ ይችላሉ፣ ስለዚህ ድፍረት አስፈላጊ ነው። በተጨማሪ ደግሞ ሥራውን ሲጀምሩ ደንበኛን በትሕትና እና በጥሩ አቀባብል መቀበል  እና መሸኘት አስፈላጊ ነው።
አንድ አዲስ ወደ ልብስ ስፌት የሚገባ ሰው ሙያው ካለው በአንድ ማሽን በበቂ ሁኔታ መሥራት ይችላል፣ ሥራ በጣም ከበዛ ግን መጨመር አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ የልብስ ስፌት ሥራ መሥራት የሚፈልጉ ሰዎች በቀላሉ አንድ ማሽን በመግዛት በቤታቸው መጀመር እና ማደግ ይችላሉ ብለዋል ወ/ሮ አለም።

ዕቅድ

ድርጅቱ ወደ ፊት አሁን ያለበትን የቦታ ጥበት ችግር በመቅረፍ ብዙ ማሽኖችን በማስገባት እና ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ራሱንም ተጠቃሚዎችን ለመጥቀም እቅድ አለው። እንዲሁም የከፍታን ፓኬጅ በመጠቀም በጨረታዎችን ላይ ለመሳተፍ እና ብዙ ሥራዎችን የመሥራት እቅድ አለው።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …