sar-bet-credit-and-saving

ሳር ቤት የገንዘብ ቁጠባና ብድር

ሳር ቤት የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ የኅብረት ሥራ ማኅበር በሳር ቤት አካባቢ ተወልደው ባደጉ አብሮ አደጎች መነሻ ሃሳብ አመንጪነት የመኖሪያ አካባቢን መሠረት አድርጎ የተቋቋመ የኅብረት ሥራ ማኅበር ነው። ዋነኛ ዓላማው አድርጎ የተነሳው የአባላቱን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች የቁጠባን ባህል በማስረፅ እና በእቅድ በመበደር የሚፈቱበትን መንገድ ማበጀት ነው። ከዚህ በተጨማሪ የአባላቱን ማኅበራዊ ትስስር ከፍ ወደ አለ ደረጃ ማሳደግና በጋራ የመሥራት ባሕልን ማበልጸግ ነው።

ሳር ቤት የገንዘብ ቁጠባና ብድር፦ ራዕይ፣ ተልዕኮ፣ ዓላማ እና መርሖች

ራዕይ

በአካባቢያችን ጠንካራ የኢኮኖሚ አቅምና ማኅበራዊ ትስስር ያለው ማኅበረሰብ በ2020 ዓ.ም. ተፈጥሮ ማየት

ተልዕኮ

በፍላጎትና እቅድ ላይ መሠረት ያደረገ የቁጠባና የብድር ባሕልን ማሥረጽና የአባላትን ኢኮኖሚያዊ ችግር መፍታት

ዓላማ

  • በፍላጎት ገንዘብ የመቆጠብና በእቅድ የመበደር ባሕልን ማዳበር
  • የኢኮኖሚ ችግሮችን በተባበረ ጥረት መከላከል፣ መቋቋምና ማስወገድ
  • የቁጠባና ብድር አገልግሎት እንዲዳብርና እንዲስፋፋ ማድረግ
  • አባላትን በማቀራረብ እርስ በእርስ የመረዳዳትና የመተሳሰብ ልምድ እንዲያዳብሩ ማድረግ
  • አባላት ዲሞክራሲያዊ የሆነ የአመራር፣ የአስተዳደርንና የቁጥጥር ልምድ እንዲቀስሙ መርዳት

መርሖች

  • አባልነት ክፍት ሆኖ በፈቃደኝነት ላይ ይመሠረታል
  • አባላት በሙሉ እኩል ድምፅ ይኖራቸዋል
  • ከጣልቃ ገብነት ተፅዕኖ ነጻ ሆኖ ራስን በራስ ማስተዳደር
  • በኅብረት ሥራ ማኅበራት መካከል ትብብርና ኅብረት መፍጠር

ሳር ቤት የገንዘብ ቁጠባና ብድር፦ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች

  • 2 ጉድር ፎቶግራፍ
  • የመታወቂያ ኮፒ
  • የመመዝገቢያ 100 ብር መክፈል
  • ቢያንስ የአንድ ዕጣ ክፍያ ብር 500 መክፈል
  • የአባልነት ፎርም መሙላት
  • የወራሽ ፎርም መሙላት

የቁጠባ ዓይነቶች

መደበኛ ቁጠባ

  • አባሉ በማህበሩ ውስጥ እስካለ ድረስ ያለማቋረጥ በየወሩ ይቆጥባል።
  • የማህብሩ የመደበኛ ቁጠባ ዝቅተኛ የቁጠባ መጠን 50 ብር ሲሆን አባሉ አቅሙ ከፈቀደ ከዛ በላይ የፈለገውን ያህል በየወሩ መቆጠብ ይችላል።
  • አባሉ ወርሃዊ ቁጠባውን በፈለገው ጊዜ መጨመር ወይም መቀነስ ይችላል። ከ50 ብር በታች ማድረግ ግን አይቻልም።
  • ለአሠራር አንዲመች አባሉ የሚቆጥበው መጠን ለ6 ወራት ያህል ተመሳሳይ መሆን አለበት።
መቆጠብ የሚያስገኘው ጥቅም ምንድን ነው?
  • አባሉ ለቆጠበው ብር መጠን ዓመታዊ ወለድ 7% ይታሰብለታል
  • አባሉ ብድር መበደር ሲፈልግ የቆጠበውን 4 እጥፍ መበደር ያስችለዋል
  • ስለዚህ የቁጠባ መጠንን ከፍ ማድረጉ በቆጠቡት ልክ ከፍ ያለ ወለድ ትርፍ እንዲኖር እና መበድር ሲያስፈልግ ከፍ ያለ ብር መበደር ያስችላል።
የመደበኛ ቁጠባን ወጪ ስለ ማድረግ
  • የመደበኛ ቁጠባ ወጪ ማድረግ የሚቻለው አባሉ ከማኅበሩ ሲሰናበት ብቻ ነው።
መደበኛ ቁጠባ መክፈያ ጊዜ
  • ዘወትር ወር ከገባ እስከ 30ኛው ቀን ድረስ በባንክ (የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1000282026876) እና አቢሲኒያ ባንክ (33297637)
  • ወይም በወሩ የመጨረሻ ቅዳሜ የማኅበሩ ቢሮ በመምጣት በጥሬ/ ካሽ መክፈል ይችላል።

የፍላጎት ቁጠባ

አንድ አባል ከመደበኛ ወርሃዊ ቁጠባ ውጪ የፍላጎት ቁጠባ በተጨማሪነት መቆጠብ ይችላል። ይህ የቁጠባ ዓይነት የመጠን ገደብ የሌለው በፈለገው ወቅት የፈለገውን ያህል ቆጥቦ በፈለገው ወቅት ማውጣት የሚችለው ነው።

የዝግ ቁጠባ

ይህ የቁጠባ ዓይነት አባሉ ጠርቀም ያለ ገንዘብ ለረዥም ጊዜ ማውጣት በማይቻልበት ሁኔታ በማኅበሩ ዘንድ የሚያስቀምጠው የቁጠባ አይነት ሲሆን የተሻለ የወለድ ጥቅም የሚያስገኝ ነው። የጊዜ ገደቡና የወለዱ መጠን በአስቀማጩና በማኅበሩ ሥራ አመራር በኩል በሚደረግ ስምምነት የሚጸና ነው።

የልጆች ቁጠባ

ይህ የቁጠባ ዓይነት አባሉ ለልጆች/ ታዳጊዎች የሚቆጥበው ቁጠባ ሲሆን በየወሩ ከ10 ብር ጀምሮ መቆጠብ ይችላል።
የማኅበሩ ዋንኛ ዓላማ አባላት የቁጠባ ባሕላቸውን እንዲያዳብሩና በቆጠቡት ልክም ለተለያየ አገልግሎት የሚውል ጠርቀም ያለ ገንዘብ በአነስተኛ ወለድ በብድር እንዲያገኙ ማድረግ ነው። በመሆኑም ማኅበሩ ለተለያዩ ፍላጎቶች የተለያየ ብድር በተለያየ የወለድ ምጣኔ ይሰጣል።
  • አባሉ ብድር ለመበደር ቢያንስ ስድስት ወር ሳያቋርጥ መቆጠብ ይኖርበታል።
  • የማንኛውም ብድር የመመለሻ ጊዜ ከ3 ዓመት - 7 ዓመት ሆኖ ዝርዝሩ በብድር መመሪያ መሠረት ይሆናል።

ዋና ዋና የብድር ዓይነቶች

የመደበኛ ብድር

ይህ የብድር ዓይነት አባሉ ባስቀመጠው ጠቅላላ ቁጠባ ላይ ተመርኩዞ የሚሰጥ ሲሆን አባሉ ያስቀመጠውን ጠቅላላ ተቀማጫ አራት (4) እጥፍ ያህል መበደር ይችላል። የመደበኛ ብድር ጣሪያ በአባሉ የጊዜ ቆይታ ይወሰናል። ይህውም አባሉ በማኅበሩ ያለው ቆይታ
    • ከ6 ወር እስከ 18 ወር ከሆነ 100 ሺህ ብር
    • ከ18 ወር እስከ 24 ወር ከሆነ 150 ሺህ ብር
    • ከ25 ወር እስከ 36 ወር ከሆነ 200 ሺህ ብር
    • ከ36 ወር ባላይ ከሆነ 250 ሺህ ብር ነው።

ልዩ ብድር

ይህ የብድር ዓይነት ከፍተኛ ፍጆታ ላላቸው ለቤት፣ ለኮንዶሚኒየም ቅደመ ክፍያ፣ ለመኪና እና ለልዩ ልዩ ማሽነሪ ግዢዎች የሚውል ነው።
    • የልዩ ብድር ወለድና መሰል ጉዳዮች በብድር መመሪያው መሠረት ወቅትን ተከትሎ የሚሰላ ይሆናል።
    • ማናቸውም የብድር አገልግሎት በማኅበሩ የብድር መመሪያ መሠረት የሚከናወን ይሆናል።
  • የአባላት ዋስትና
  • የመሥሪያ ቤት ዋስትና
  • የቋሚ ንብረት(ቤት)
  • የተንቀሳቃሽ (መኪና)
  • ማንኛውንም የማኅበሩ አባል የአክሲዮን ባለድርሻ ይሆናል። በአክሲዮን ድርሻው ልክም የማኅበሩ ትርፍና ኪሳራ ተካፋይ ይሆናል።
  • የአንድ አክሲዮን ዋጋ 500 ብር ሲሆን አንድ አባል ቢያንስ አንድ አክሲዮን ሊኖረው ይገባል።
  • በአክሲዮን ድርሻ እና በጠቅላላ ተቀማጭ መካከል የሚኖረው ምጣኔ ቢያንስ 1 ለ 6 መሆን አለበት።
  • በመሆኑም የአክሲዮን ድርሻው ከቁጠባው መጠን ጋር በንፅፅር ቀስ እያለ የሚያድግ ይሆናል።
  • መግዛት የሚቻለው ትልቁ የአክሲዮን ድርሻ መጠን 100 እጣ ብቻ ነው። ከዚህ በላይ መግዛት አይቻልም።
  • አክሲዮን ዕጣ ከፍ የማድረግ ጥቅም፦ የዕጣ ጥቅሙ በዋነኝነት ለትርፍ መካፈያ ነው። በዓመቱ መጨረሻ ላይ የሚገኘው ትርፍ ለአባላት የሚከፋፈለው አባላት ባላቸው የዕጣ መጠን ብቻ ነው። በመሆኑም ከፍ ያለ አክሲዮን ዕጣ ያለው አባል ከማኅበሩ ዓመታዊ ትርፍ ላይ ከፍ ያለ ድርሻ ይኖረዋል ማለት ነው።
  • አባሉ መጠነኛ ብድር በሚፈልግበት ጊዜ አክሲዮጣው እንደ ዋስትና ያገልግለዋል።
  • የአክሲዮን ድርሻ ለማሳደግ ለሽያጭ የተዘጋጀው ዕጣ መጠን ተሽጦ እስካላለቀ ድረስ አንድ አባል በፈለገው ጊዜ የአክሲዮን መጠኑን እስከተፈቀደው መጠን ድረስ ማሳደግ ይችላል።
  • ለአክሲዮን የተከፍለ ገንዘብ ተመላሽ የሚደረገው አባሉ ሲሰናበት ብቻ ነው።

ሳር ቤት የገንዘብ ቁጠባና ብድር፦ አድራሻ

  • አድራሻ፦ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ፣ ወረዳ 03፣ የቤት ቁጥር 100፣ ሳር ቤት ሱዳን ክለብ ፊት ለፊት በሚያስገባው ኮብል ስቶን መንገድ 100 ሜ. ያህል ገባ ብሎ
  • ስልክ
    • 0980 160767
    • 0980 160209
    • 011 8549521
  • ኢሜይል፦ sarbetsaving@gmail.com

ማስታወሻ፦ ይሄ መረጃ የተዘጋጀው ከሳር ቤት የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ የኅብረት ሥራ ማኅበር  ድረ ገጽ በተገኘው መረጃ ላይ ተመሥርቶ ለጥቃቅን እና አነስተኛ ድርጅቶች በሚጠቅም መልኩ ተቀናብሮ ነው።

ይህንንም ይመልከቱ

liyu-logo

ልዩ የገንዘብ የእገዛ ተቋም

ልዩ የገንዘብ የእገዛ ተቋም መንግሥት ባወጣው የአንስተኛ ፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 40/88 መሠረት …