ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ አስናቀ ፈጠነ የግል ኢንተርፕራይዝ ሆኖ በ2007 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ እስከ ደረጃ 6 የሚደርሱ አጠቃላይ የኮንስትራክሽን ሥራዎች የሚሠራ ድርጅት ነው።
ድርጅቱ የሚሠራቸው ሥራዎች
- የሕንጻ ግንባታ
- የሕንጻ ማጠናቀቂያ ሥራዎች
- የመንገድ ሥራ
- የድልድይ ግንባታ
- የሕንጻ ጥገና ሥራዎች እና
- አጠቃላይ የፊኒሺንግ እና የኮንስትራክሽን ሥራዎችን ይሠራል
ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት
አቶ አስናቀ በዚህ የሥራ ዘርፍ የዐሥራ አንድ ዓመት የሥራ ልምድ ያላቸው ሲሆን የኮንስትራሽን ሥራ ገና ሀ ብለው ሲጀምሩ ጀማሪ ሙያተኛ ሆኖ በመቀጠር ነበር። ከዛም በሂደት ነገሮችን እየተማሩ ራሳቸውን እያሳደጉ ሲመጡ፣ ለሥራው በቂ ዕውቀት ሲኖራቸው፣ የሚያስቧቸው አንዳንድ ሥራዎች እንዲህ እኮ ቢሠራ የተሻለ ነው፣ ወይም እኔ የተሻለ አድርጌ እሠራዋለሁ እያሉ ማሰብ ሲጀምሩ፤ ለምን አልሠራም እያሉ ከራሳቸው ጋር ከተወያዩ በኋላ ነው በግል የመሥራት ሀሳብ የመጣላቸው።
አቶ አስናቀ የግላቸውን ድርጅት ለመመሥረት ቅድሚያ ፈቃድ ማውጣት ነበረባቸው፤ ስለዚህም ፈተናዎችን ኤጀንሲ በመሄድ ፈተና ተፈትነው ፈተናውን ካለፉ በኋላ የተሰጣቸውን ሰርተፍኬት በመያዝ ደረጃ ስምንት የኮንስትራክሽን ፈቃድ በማውጣት ይህን ድርጅት መሥርተዋል። ድርጅቱ ቀስ በቀስ ከደረጃ ስምንት በማደግ አሁን ደረጃ ስድስት ላይ ያለ ሲሆን ወደ ደረጃ ዐምስት እየተጠጋ ይገኛል። ለዚህም እድገት አቶ አስናቀ እንደሚሉት ታጋሽ መሆን እና ከሥራው ጥራት በተጨማሪ ለደንበኞች ትሁት እና ሰው አክባሪ መሆን ዋና የእድገቱ መሠረቶች እንደሆኑ ጠቅሰዋል፤ የእሳቸውም ዕሴት (ጠንካራ ሠራተኛ) መሆን እንዳለ ሆኖ።
አስናቀ ፈጠነ ሕንጻ ተቋራጭ አሁን ባለው የኮንስትራክሽን ፈቃድ እስከ ስድስት ፎቅ የሚደርስ ሕንጻ መሥራት ይችላል። አንድ ስድስት ፎቅ ሕንጻ ቢዘገይ በስድስት ወር ጊዜ ከፈጠነ ደግሞ በአራት ወር ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ ይችላል። ድርጅቱ ሥራዎችን የሚሠራው በሁለት መንገዶች ሲሆን አንድ ከመንግሥት ጋር ጨረታ በመሳተፍ ሁለት ደግሞ በግለሰብ ሰው በሰው ሥራውን እያዩ በሚመጡ የሰብ ኮንትራክት ሥራዎች ነው። በዚህም ለመንግት ስድስት ሕንጻዎችን ሠርቶ ያስረከበ ሲሆን በሰብ ተቋራጭነት ደግሞ ሃያ ዐምስት ሥራዎችን መሥራት ችሏል።
አቶ አስናቀ 2merkato.com ለጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ያዘጋጀውን የከፍታ አገልግሎት መረጃ ያገኙት በክፍለ ከተማ ለሥልጠና በተጠሩበት አጋጣሚ እንደሆነ እና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሆኑ ገልጸዋል።
የኮቪድ ተፅዕኖ
ድርጅቱ በኮቪድ ወቅት ከባድ ጊዜ አሳልፏል፤ ምንም ሥራ ባለመኖሩ ለሠራተኞች የሚከፈል ደመወዝ አልነበረም። ስለዚህ ሃያ ዘጠኝ ሠራተኞችን በመቀነስ ነው ጊዜውን ያሳለፈው። ድርጅቱ ከኮቪድ በኋላ በማገገም ወደ ሃያ ለሚደርሱ ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ሲሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ የነበረውን መነሻ ስድስት ሺህ ብር ካፒታል ወደ አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሺሕ ብር (ብር 1,500,000) ማድረስ ችሏል።
ምክር እና እቅድ
አቶ አስናቀ ወደ ኮንስትራክሽን ሥራ ለሚገቡ የሚከተለውን ምክር አስተላልፈዋል፦ ታጋሽ መሆን እና ነገሮችን ማሳለፍ መቻል፤ በተለይ ደግሞ ከደንበኛ ጋር ሌላው አስፈላጊ ነገር ደግሞ ከሰው ጋር ተግባቢ መሆን ነው። ይህ ደግሞ ሥራው ቢበላሽ ራሱ ተግባብቶ በራስ ኪሳራ መሥራት መቻል አለበት። ይሄም ደንበኛው ደስተኛ እንዲሆን እና ለሌሎች ሥራዎች መንገድ ይከፍትለታል። ከተጣላ ግን በተቃራኒው በዛ ሰው በኩል የሚመጣ ሥራ እንዳለ ይቀራል ማለት ነው። በሥራ ብዙ ችግር ሊኖር ይችላል ወደ ኮንትራክሽን ሥራ ሲመጣ ደግሞ መጠኑ ይሰፋል ስለዚህ ታጋሽ እና ቶሎ መፍትሔ መፍጠር የሚችሉ ሰዎች ወደ እዚህ ሥራ ቢገቡ ጥሩ ነው።
ድርጅቱ ወደ ፊት አሁን የሚሄድበት መስመር ጠብቆ በመጓዝ በየዓመቱ አንድ ደረጃ የማደግ አቅድ አለው። ይህም ማለት ከሚታየው የማሽነሪ እና ሃብት መጠን በተጨማሪ የሰው ኃይል (የሠራተኞቹ) አስተሳሰብ እና ዕውቀት አብሮ ማደግ እንዳለበት በማመን፣ በማቀድ እና በማከናወን ላይ ይገኛል።
የድርጅቱን አገልግሎት መጠቀም የሚፈልጉ የድርጅቱን ስልክ በዚህ ሊንክ በመግባት ዓይተው መደወል ይችላሉ።