ብራይት ማኑፋክቸሪንግ የተመሠረተው በአቶ ሠለሞን መገርሳ እና በሁለት ጓደኞቻቸው በ2021 (እ.ኤ.አ.) ነው። ድርጅቱ የእንሰት ተክልን በመጠቀም ከግሉተን ነጻ (gluten free) የሆነ ስታርች እና የፋይበር ምርቶችን ያመርታል። እነዚህም ምርቶች ለተለያዩ ተጠቃሚ ደንበኞች፣ የግብርና ውጤት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች፣ ሱፐርማርኬቶች እና የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ያቀርባል። በቅርቡም ወደ ውጭ ሀገር ምርቱን ለመላክ (export ለማድረግ) አውሮፓ ካሉ ገዢዎች ጋር እየተነጋገረ ይገኛል።
ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት
አቶ ሠለሞን እና ሁለት ጓደኞቻቸው ብራይት ማኑፋክቸሪንግን የመሠረቱት ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸው በፊት ተወልደው ባደጉበት አካባቢ የነበረውን የእንሰት ችግር ጠንቅቀው ያውቁ ስለነበር ያንን ችግር ለመፍታት ነው። ችግሩን ጠንቅቀው ማወቃቸው ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በኋላ የመመረቂያ ጽሑፋቸውን በእንሰት ላይ ለመሥራት እንዲወስኑ አድርጓቸዋል። በደንብ እንዲገፉበት ያበረታታቸው ነገር ደግሞ ሥራውን የሚሠሩት እናቶች መሆናቸው እና ለሥራው የሚያወጡት ጉልበት እና ኅይል ውጤቱ ከሚያስገኘው ገቢ ጋር ተመጣጣኝ አለመሆኑ ነበር። ከዚህም ይባስ ብሎ ሥራው አድካሚ ከመሆኑም በላይ የወንዶች ተሳትፎ በእንሰት ሥራ ላይ እንደ አሳፋሪ ነገር ስለሚቆጠር እናቶቹን የሚያግዛቸው የለም። ይህም ምክንያት እነ አቶ ሠለሞን ይበልጥ በደንብ ጠንክረው እንዲሠሩ አድርጓቸዋል። ሌላው ምክንያት የእንሰት ተክል በኢትዮጵያ ብቻ ስለሆነ በስፋት ለምግብነት የሚውለው ከውጭ ሃገር የሚመጣ ምንም ዓይነት ማሽን አይገኝም።
ስለዚህ እነዚህን ምክንያቶች ታሳቢ በማድረግ እንዲሁም ምን ዓይነት ማሽን ብንሠራ ያለውን ችግር ወደ ቢዝነስ መቀየር እንችላለን? ብሎም ማኅበረ ሰቡን ተጠቃሚ ከማድረጉም ባሻገር ራሳችንን መጥቀም የሚችል ሥራ መሥራት እንችላለን? በተጨማሪም ይሄንን ድርቅ የሚቋቋም ተክል በጥቂት የሀገራችን ክፍል ብቻ በምግብነት አገልግሎት ከሚሰጥ በመላው ሀገሪቱ ውስጥ እንዲት ሊስፋፋ ይችላል? የሚሉትን ጥያቄዎች በማሰብ ማሽኑን መሥራት የጀመሩት። የማሽኑን ዲዛይን በመንደፍ ሳምፕል በመሥራት እና ውጤታማነቱን በማስመስከር የአእምሮ ንብረት (Patent Right) ሊሰጣቸው ችሏል። እንደ ጀማሪ ድርጅት ማሽኑን አምርቶ ለገበሬዎች ማከፋፈል ግን የድርጅቱ አቅም አይፈቅድም።
ስለሆነም የድርጅቱ መሥራቾች ያመጡት ሀሳብ አንድ ቦታ ማሽን በመትከል ማኅበረ ሰቡ ደግሞ እንሰትን እንደ ጥሬ እቃ ለፋብሪካው እንዲያቀርብ ነው። ፋብሪካው ደግሞ በተመጣጣኝ ዋጋ እንሰቱን በመግዛት ምርቱን በፋብሪካ ውስጥ በማምረት ለሰፊ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ገበያ ያቀርባል። እንዲሁም የኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆነውን ለኢንዱስትሪዎች በማቅረብ የማኅበረ ሰቡን ሥራ በማቅለል እና የበለጠ ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ አመቻችቶ እየሠራ ይገኛል።
ብራይት ማኑፋክቸሪንግ የሚያመርተው ምርት ልዩ የሚያደርገው ከሌሎች ከውጭ ሀገር ከሚገቡ የስታርች (ስታርች) ምርቶች በተለየ በውስጡ ምንም ዓይነት ግሉተን (gluten) አለመቀላቀሉ ነው። እንዲሁም የድርጅቱ ምርት ከግሉተን ነጻ የሆነ ስታርች መሆኑ በውጭ ሀገር ገበያ በጣም ተፈላጊ ያደርገዋል። በጠቅላላው ስናየው ከውጭ ሀገር እየገቡ የሚሸጡ ምርቶችን በመተካት፣ ያለውን ከፍተኛ የዋጋ ልዩነት ተመጣጣኝ በማድረግ፣ ብሎም የውጭ ምንዛሬ ወጪን በማስቀረት፣ እንዲሁም ምርቱን ወደ ውጪ ሀገር በመላክ የውጭ ምንዛሬን የሚያመጣ ለሀገር እድገት ዕሴት የሚጨምር ድርጅት ያደርገዋል።
ድርጅቱ አሁን በሚገኝበት አርባ ፐርሰት (40%) የማምረት አቅም በአንድ ዓመት ሰማንያ አራት ቶን ግሉተን ፍሪ (gluten free) ስታርች (Starch) እና አሠር (Fiber) ለማምረት ዐቅዶ እየሠራ ይገኛል። ምርቱንም ለሱፐርማርኬቶች በአንድ ኪሎ እና በግማሽ ኪሎ በማሸግ እያቀረበ ነው። ለአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች ደግሞ አሠር (Fiber) በኩንታል ያቀርባል።
እነ አቶ ሰለሞን ድርጅቱን ሲመሠርቱ የነበራቸው የራሳችው ሀሳብ እና ፍላጎት ነበር። ያለመታከት በመሥራት እና በሂደት ብዙ ልምድ እና ተሞክሮ በማካበት በመማር በብዙ ችግሮች አልፈዋል። ለምሳሌ ሲጀምሩ የነበራቸው ዕውቀት ቀጥታ የዩኒቨርሲቲ ዕውቀት (academic knowledge/technical skill) ብቻ ነበር። የቢዝነስ ዕውቀት አልነበራቸውም። ሌላው ደግሞ ከተመረቁ በኋላ ያለው የተለመደ መንገድ ሥራ መያዝ ቤተሰብ የሚጠብቀው ነገር ሲሆን፣ ጠንከር ያለ ችግር የነበረው ደግሞ ለሥራ ማስኬጃ እና መንቀሳቀሻ የሚሆን የገንዘብ እጥረት (Limited or Inconsistent Cash Flow)። እነዚህ ችግሮች ለማለፍ የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅመዋል። የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር (MiNT) እና ጂአይዜድ (GIZ) በመተባበር በ2020 (እ.ኤ.አ.) ባዘጋጁት የAGRO BUSINNES IDEA COMPETITION ሀገር አቀፍ ውድድር ላይ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን በመወከል ተሳትፈው ገንዘብ/ፈንድ አሸንፈዋል። ይህም አስፈላጊ የሚባሉ ነገሮች ለማድረግ ጠቅሟቸዋል። በዚህ አጋጣሚ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን ማመስገን ይፈልጋሉ፤ ኢንኩቤሽን ሴንተር በመስጠት ለስድስት ወር የገበያ ጥናት (Market Research) እና ሌሎች ተያያዥ ሥራዎችን እንዲሠሩ ከጂአይዜድ ጋር በመተባበር ድጋፍ አድርጎላቸዋል።
ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት አዋጭ መሆናቸው ለታመነባቸው ቢዝነሶች የተለያዩ ድጋፎች የሚያደርግ ሲሆን ከእነዚህ ድጋፎች አንዱ ደግሞ የሥራ ቦታ ማመቻቸት ነው። በዚህም ምክንያት ብራይት ማኑፋክቸሪንግ ተጠቃሚ መሆን ችሏል። ድርጅቱ በተጨማሪም አዳዲስ ደጋፊ ኢንቨስተሮች (የአክሲዮን ድርሻ ገዝተው ድርጅቱ ውስጥ የሚገቡ ኢንቨስተሮች) እና ተጠቃሚዎች ለማግኘት የተለያዩ ኤክስፖዎች ላይ ይሳተፋል። ከዚህም በተጨማሪ ድረ ገጹን (brightmanufacturing.net) እና ማኅበራዊ ሚዲያ (በቴሌግራም ቻናል እና ፌስቡክ ገጽ) በመጠቀም ምርቱን ያስተዋውቃል። ድርጅቱ ለሦስት ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ሲሆን ስድስት ለሚደርሱ ዜጎች ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ድርጅቱ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር ለዐሥራ ሁለት ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ።
አቶ ሰለሞን ቴክኖሎጂ መጠቀም በአሁን ጊዜ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራሉ። ድርጅቱ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባም 2merkato.com ለጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ያዘጋጀውን የከፍታ አገልግሎት መጠቀም እንደሚጀምሩ ጠቅሰዋል። የሥራ ዘርፉ ምንም ዓይነት ቢሆን ቴክኖሎጂን መጠቀም እንዳለበት ይናገራሉ። እንደምሳሌ የራሳቸውን ድርጅት አንስተው የድርጅታቸው ዌብሳይት በማየት ብቻ ደንበኛ ቀጥታ መምጣት እንደሚችል ተናግረዋል። በመቀጠል ደግሞ ደንበኛው የሚፈልገውን ምርት ማዘዝ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ለድርጅቱ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን የሚያቀርቡ ሰዎች እንዲገናኙ እድል ይፈጥራል። ሌላው ድርጅቱ ያመረተውን ምርት ሲልክ የት እንደ ደረሰ ለማወቅ እና ሌሎች ነገሮችን መከታተል ያስችላል። ቴክኖሎጂ አንድ ቢዝነስ ብዙ ሠራተኛ ሳይቀጥር እና ብዙ ወጪ ሳያወጣ ገበያ ውስጥ ለመቆየት ብሎም ተወዳዳሪ ሆኖ እና የነጠረ ሆኖ ለመውጣት ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለው እንደሚያምኑ የድርጅቱ መሥራች ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂ ለብራይት ማኑፋክቸሪንግ ድርጅት ትልቅ አስፈላጊ ግብዓት እንደሆነ ነው የሚያምኑት። እነሱም ይህን ስለተረዱ ነው ማምረት ከመጀመራቸው በፊት ዌብሳይት ያዘጋጁት። ይህም ደግሞ በጣም ጥሩ ውጤት አምጥቷል፤ ከዌብሳይቱ ዕያዩ የሚደውሉ እና በኢሜይል መልእክት የሚልኩ ደንበኞች በሀገር ውስጥ እና ውጭ ሀገር ማግኘት እንዲችል አስችሎታል። ለምሳሌ ጀርመን 53 (ሃምሳ ሦስት) ሱቅ ካለው ድርጅት (supermarket chain) ጋር ግንኙነት መፍጠር ችሏል።
አሁን ላይ የድርጅቱ የካፒታል አቅም ሁለት ሚሊዮን ብር ደርሷል።
የኮቪድ ተፅዕኖ
ኮቪድ በድርጅቱ ላይ ቀጥተኛ ጉዳት ባይኖረውም በተዘዋዋሪ ድርጅቱ ያስቀመጠውን የዐምስት ዓመት ዕቅድ አዘግይቶታል። ምክንያቱ ደግሞ ብዙ መሥሪያ ቤቶች ዝግ ስለነበሩ ብዙ አጋር አብረው መሥራት የሚችሉ ድርጅቶችን ማግኘት እንዳይችል አድርጎታል። ሌላው ደግሞ በሀገራችን በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት መንገዶች በተደጋጋሚ ይዘጉ ስለነበር የጥሬ እቃ አቅርቦት እንደልብ ገበሬዎች ጋር ሄዶ ማግኘት እንዳይችል አድርጎታል።
ምክር እና ዕቅድ
ድርጅቱ የእንሰትን ምግብ ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ ላይ ተደራሽ ለማድረግ የረጅም ጊዜ ዕቅድ አለው። በዐጭር ጊዜ ዕቅድ ደግሞ፦
- የሚያመርታቸውን ምርቶች መጠን ምርጫ በማብዛት መቶ እና ሃምሳ ግራም ምርት ማቅረብ፣
- እንዲሁም እንሰትን በተጠቃሚ ዋጋ በመግዛት ማኅበረ ሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ፣
- ብዙ ኅይል የሚፈጀውን ሥራ ዘመናዊ ማሽን ሠርቶ በማቅረብ ገበሬ ማኅበራትን በማደራጀት እንዲጠቀሙ ማድረግ፣
- እንዲሁም የድርጅቱን ምርት ለመግዛት የጠየቁ ጀርመን እና ኦስትሪያ ላሉ ገዢዎች ምርቱን በመላክ (export በማድረግ) እና ያላቸውን የገበያ ትስስር በመፍጠር ሰፊ ሥራ የመሥራት ዕቅድ አለው።
አዲስ ማንኛውንም ሥራ ለሚጀምሩ ሰዎች “ሀሳባቸው ከራሳቸው አልፎ ሌሎችን መጥቀም እንደሚችል ማወቅ፣ ባላቸው ነገር መንቀሳቀስ፣ እንዲሁም በሚሠሩት ሥራ ላይ በጣም በቂ እና መጠነ ሰፊ የሆነ ጥልቅ መረጃ መሰብሰብ አለባቸው። እነሱ ይህን ሲያደርጉ የሚረዳ ሰው ወይም ድርጅት ይመጣል” ሲሉ ምክራቸውን አካፍለዋል። እንደ ምሳሌም ብራይት ማኑክቸሪንግ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የነበረውን ተሞክሮ አውስተዋል። “ከነበሩ ጀማሪ ሰማንያ ዐምስት የፈጠራ ድርጅቶች ውስጥ ብራይት ማኑፋክቸሪንግ ሊመረጥ የቻለው ሳይሰለች እና ሳይታክት በመሥራቱ ነው። ስለዚህ ጠንክረው ሲሠሩ ሥራቸውን ያየ ሰው ደግሞ ራሱ ይመጣል፤ የራስ ጥረት ማድረግ ሥራቸው እንዲከፍላቸው ያደርጋል” ሲሉ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።