መነሻ / ፋይናንስ እና ኢንቨስትመንት / የግል ብድር እና ቁጠባ ተቋማት / ዳይናሚክ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም አክስዮን ማኅበር

ዳይናሚክ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም አክስዮን ማኅበር

ዳይናሚክ በአነስተኛና መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ገበሬዎች፣ በጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማትና ግለሰቦች ያለባቸውን የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ አለመሆን ችግር ለመቅረፍ ግልፅ እና ስትራተጂካዊ ራዕይ፣ ተልእኮና ዓላማ ቀርፆ ከግቡ የሚያደርሱትን የገንዘብ ቁጠባና ብድር አገልግሎቶች በመስጠት ላይ ይገኛል። የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ መሆን የተገለሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለማብቃት፣ የመበልፀግ እድላቸውን ለማስፋትና የተጠቂነታቸውን መጠን ለመቀነስ ያስችላል፡፡ እንዲሁም ገቢያቸው አናሳ ለሆኑ ቤተሰቦችና ሥራ ፈጣሪዎች በንግድ ዘርፍ የመሰማራት እድል ይሰጣል፣ ሥራ የመፍጠርና የድካማቸው ፍሬ ተጠቃሚ የመሆን በር ይከፍታል። ዳይናሚክ ማይክሮ ፋይናስ ተቋም አ.ማ. የኅብረተ ሰቡን ፍላጎት ያማከለ የፋይናንስ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል። ተቋሙ የደንበኞቹን ፍላጎት መነሻ በማድረግ በየጊዜው አሠራሩን በቴክኖሎጂ እያዘመነ የሚገኝ ሲሆን አገልግሎቱን ለበርካታ የኅብረተ ሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ ቅርንጫፎችን እና የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት ላይ ይገኛል። ተቋሙ ወጣቱን የኅ ብረተሰብ ክፍል ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ በአሁኑ ሰዓት ምሳሌ የተባለ የብድር አገልግሎት አዘጋጅቷል።

ዳይናሚክ፦ ምሥረታ፣ ዓላማ፣ ራዕይ፣ ተልእኮ

  • ዳይናሚክ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም አ.ማ. በአዋጅ ቁጥር 626/2001 እና የገንዘብ ተቋማትን የመቆጣጠር ሥልጣን በተሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በወጡ መመሪያዎች የተደነገጉ መስፈርቶች አሟልቶ እ.አ.አ. መጋቢት 12 ቀን 2001 ዓ.ም. በብሔራዊ ባንክ ተመዝግቦና ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ የተቋቋመ አክስዮን ማኅበር ነው። ማኅበሩ በመላው ሀገሪቱ ውስጥ የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን የሥራ ፈቃድ አውጥቶ በመንቀሳቀሰ ላይ ይገኛል።
  • ዳይናሚክ ቁጥራቸው ከ400 በላይ በሆኑ ባለአክስዮኖች ባለቤትነት የተመሠረተ የግል ኩባንያ ሲሆን ዓላማውም ቀልጣፋ የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎት በመስጠት የደንበኞቹን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ወደ ተሻለ ደረጃ ማሳደግ ነው፡፡ የዳይናሚክ ባለአክስዮኖች መዋዕለ-ነዋያቸውን በማሰባሰብ ለታላሚ ደንበኞቻችው ዘላቂ የፋይናንስ አገልግሎት ለመስጠት የተሰጡና የተነሳሱ የግል ባለሃብቶች ናቸው።
ዓላማ: የዳይናሚክ ዋና ዓላማዎች የሚከተሉት ናቸው።
    • ኅብረተ ሰቡ ውስጥ ቀጣይነት ያለው የቁጠባ ባህል ማዳበር፤
    • አዋጭ በሆነ የሥራ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ነጋዴዎች፣ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች፣ ህጋዊ ለሆኑ ድርጅቶች፣ ለገበሬዎች እንዲሁም ለሌሎች ተግባር የሚውል ብድር መስጠት፤
    • የብድር ስጋት ለመቀነስ የብድር ኢንሺራንስ አገልግሎት መስጠት፤
    • ትርፋማ ከሆኑ ድርጅቶች፣ ባንኮች፣ እንዲሁም ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ቦንዶችን ወይም አክሲዮኖችን መግዛት።
ራዕይ
    • ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም ግለሰቦች ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ማምጣት እንዲችሉ በማገዝ ዳይናሚክ ተመራጭ የፋይናንስ ተቋም አንዲሆን ማድረግ።
ተልዕኮ
    • የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም በገጠርና በከተማ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በኢኮኖሚ በልጽገው በኑሮአቸው ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያመጡ ቀልጣፋ፣ ተመራጭና አስተማማኝ የሆነ የፋይናንስ አገልግሎት መስጠት።

ዳይናሚክ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የከተማና የገጠር ነዋሪዎችን ፍላጎት ለማሟላት እና የቁጠባ ባህል ለማዳበር ተብለው የተዘጋጁ የቁጠባ ሂሳብ አገልግሎቶችን ይሰጣል። እነዚህ የቁጠባ ሂሳቦች ከተወዳዳሪዎቻችን የተሻለ ወለድ የሚከፍሉ ሲሆን ማንም ሰው በአቅራቢያው ወደሚገኝ ቅርንጫፍ በመሄድ ከዚህ በታች ከተዘረዘሩት የቁጠባ ዓይነቶች ተስማሚውን በመምረጥ አካውንት መክፈት ይችላል።

የቁጠባ ዓይነቶች

  • የልጆች ቁጠባ
  • የሴቶች ቁጠባ
  • ወለድ አልባ ቁጠባ
  • የጊዜ ገደብ ተቀማጭ
ዳይናሚክ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ከመደበኛ ባንክ የብድር አገልግሎት ማግኝት ለማይችሉ በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የገጠርና የከተማ ነዋሪዎች እንዲሁም በማኅበር ተደራጅተው በአነስተኛና ጥቃቅን የሥራ ፈጠራ ዘርፍ ለተሰማሩ ቡድኖች ከዚህ የሚከተሉትን የተለያዩ የብድር ዓይነቶች በግል ዋስትና፣ በቡድን ዋስትና፣ በተቋም ዋስትናና በንብረት ዋስትና ይሰጣል። የብድር ዓይነቶቹም እንደሚከተሉት ናቸው።
  1. የንግድ ብድር
  2. የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ ብድር
  3. የቋሚ ንብረት ማፍርያ ብድር
  4. የኮንስትራክሽን ብድር
  5. የግብርና ብድር
  6. የሠራተኞች ብድር
  7. የውሃና መፀዳጃ ቤት (ዋሽ) ብድር
  8. ልዩ ብድር
ዳይናሚክ ማይክሮ ፋይናንስ ከዚህ የሚከተሉትን ገንዘብ ነክ ያልሆኑ አገልግሎቶች ይሰጣል።
  1. የቢዝነስ ልማትና ማኔጅመንት ስልጠና
  2. የገንዘብ ማኔጅመንት እና አጠቃቀም ስልጠና
  3. ሌሎች የቴክኒክ እገዛዎች እና ምክሮች
የማይክሮ ፋይናንስ ሥራ በባህርዩ ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር አብሮ መሥራትን ይጠይቃል። በመሆኑም ዳይናሚክ ከዚህ በታች ከተገለፁት ድርጅቶች ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ሥራውን ጀምሯል።
  • አይሲፒ፦ INTERNATIONAL CENTER OF INSECT PHYSIOLOGY AND ECOLOGY (ICIPE) ከሚባል በአማራ ክልል ከሚሠራ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት ጋር አብሮ ለመሥራት የሚያስችለንን የትብብር ስምምነት የተፈራረምን ሲሆን ድርጅቱ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎች ላይ ድጋፍ ያደርጋል።
  • ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ፦ ከአገር በቀሉ ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ጋር የብድርና ሌሎች አገልግሎቶችን ማግኘት የሚያስችል ውል አለው።
  • ወተር ዶት ኦርግ (Water.org) ከተባለ በንፁህ የመጠጥ ውሃና የንፅህና አገልግሎት ላይ ከተሰማራ ዓለምአቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር አብሮ መሥራት የሚያስችለንን የመግባቢያ ሰነድ አለው።
  • ኒያላ ኢንሹራን ከኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያ ጋር በብድር ዋስትና ዙሪያ አብሮ ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ አለው።
ለተጨማሪ መረጃ ወደሚቀርብዎ የዳይናሚክ ማይክሮ ፋይናንስ ቅርንጫፍ ስልክ ይደውሉ ወይም በአካል ጎራ ይበሉ።
የቅርንጫፍ ስምስልክ ቁጥር
ዋና መ/ቤት ቸርችል 0115 177285
የካ ቅርንጫፍ 0118 787148
ጀሞ ቅርንጫፍ 0118 723873
ቸርችል ቅርንጫፍ 0118 723876
ገርጂ ቅርንጫፍ 0118 722490
ቃሊቲ ቅርንጫፍ 0118 263348
ጉለሌ ቅርንጫፍ 0118 625081
ቅዱስ ኡራኤል ቅርንጫፍ 0118 723453
ማስታወሻ፦ ይሄ መረጃ የተዘጋጀው ዳይናሚክ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም አክሲዮን ማኅበር በአካል ሄዶ በመጠየቅ በተገኘው መረጃ ላይ ተመሥርቶ ለጥቃቅን እና አነስተኛ ድርጅቶች በሚጠቅም መልኩ ተቀናብሮ ነው።

ይህንንም ይመልከቱ

ኒኦ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ.

ኒኦ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ. ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባገኘው ፈቃድ መሠረት በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ላይ …