መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ደነቀ፣ ሠናይት እና ቀለሙ የተለያዩ አበቦች፣ ችግኞች ማምረት እና መሸጥ እንዲሁም የገጸ-ምድር ማስዋብ አገልግሎት

ደነቀ፣ ሠናይት እና ቀለሙ የተለያዩ አበቦች፣ ችግኞች ማምረት እና መሸጥ እንዲሁም የገጸ-ምድር ማስዋብ አገልግሎት

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ደነቀ ጃንጉሌ እና በጓደኞቻቸው በ2006 ዓ.ም ነው። ይህ ድርጅት በገጸ-ምድር ማስዋብ እና በችግኝ አቅርቦት ሥራ የዐሥራ ሦስት ዓመት ልምድ አለው።
ድርጅቱ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች

  • የጋርደን ሥራ
  • የዲዛይን ንድፍ ሥራ
  • ገጸ-ምድር ማስዋብ ሥራ
  • የቤት ለቤት የዕፅዋት ማስዋብ አገልግሎት
  • ተያያዥ የማማከር አገልግሎት
  • የተለያየ መጠን ያላቸው አበቦች ማቅረብ
  • አገር በቀል እና አገር በቀል ያልሆኑ ዛፎች ማቅረብ
  • መድሐኒትነት ያላቸው ዕፅዋቶችን ማቅረብ

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

ድርጅቱ ለሚመጣ ትዕዛዝ ምንም ዐይነት የአቅርቦት ችግር የለበትም። ይህንም ሦስት ሄክታር በሚደርስ እርሻ ላይ ችግኞች፣ አትክልት እና ፍራፍሬ (አፕል፣ ማንጎ፣ አቮካዶ)፣ ቡና፣ የአገር ውስጥ እና የውጪ አገር የተለያዩ ዕፅዋት ያሉት ሲሆን በተጨማሪም በደቡብ ክልል ብርቱካን፣ ሎሚ እና የሙዝ ምርቶችን ያመርታል። ድርጅቱ የሚያቀርባቸው ምርቶች ዋጋ ከዐሥር ብር ጀምሮ እስከ አንድ ሺህ ብር ድረስ ነው። እነዚህን ምርቶች አስፈላጊ ሲሆን ቦታው ድረስ በመሄድ ለደንበኞች ያደርሳል።

ይህ ድርጅት ከተለያዩ ትላልቅ ተቋማት ጋር አብሮ ሠርቷል። ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የቤተ መንግሥት ግቢ የማስዋብ እና የዲዛይን ሥራ ብሎም ዕፅዋትን በማቅረብ ተሳትፏል። እንዲሁም በኦሮሚያ ህጻናት እና ልጆች ጉዳይ ቢሮ፣ አዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የውስጥ ዲዛይን እንዲሁም ምርት በማቅረብ ሥራዎች ተሳትፏል። በአሁን ጊዜም በደቡብ ክልል በሰባ አምስት ሺህ ካሬ ላይ የሚገኝ ሪዞርት የማስዋብ ሥራ እየሠራ ይገኛል።

ድርጅቱ ሲመሠረት በሦስት አባላት ሲሆን በአሁን ጊዜ ለሠላሳ ቋሚ ሠራተኞች እና ሥራ ሲበዛ ለሚመጡ ሃምሳ ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ይህ ድርጅት ሥራዎችን የሚሠራው በትውውቅ እና ሰው በሰው ሲሆን፣ እንደ ተጨማሪ አንድ ጥሩ ቦታ ላይ የተተከለ ማስታወቂያ እያየ እግረ መንገዱን በሚመጣ ደንበኛ ነው።

አቶ ደነቀ ይህን ሥራ ከመጀመራቸው በፊት የኮንስትራክሽን ሥራ ላይ ተሠማርተው የነበረ ሲሆን በሆነ የሥራ አጋጣሚ የገጸ-ምድር ማስዋብ ዲዛይን ሥራ ይመጣና ይሠራሉ፤ በሂደትም ሥራውን እያዩት ሲመጡ ቀስ በቀስ እየወደዱት ስለመጡ ሙሉ ሥራቸውን ወደ ገጸ-ምድር ማስዋብ እና የአትክልት አቅርቦት አዙረው በመሥራት ላይ ይገኛሉ። ስለ ሥራውም የሚከተለውን ብለዋል “ሥራው በጣም ደስ ይላል፤ አካባቢን አረንጓዴ ማድረግ እና ማስዋብ የአገርን ገጽታ ለመቀየር ያስቻላል። የኮስትራክሽን ሥራ ግን ጨረታ በመከታተል ነው፤ ይህ ግን (ገጸ-ምድር ማስዋብ) ቦታ ካለ እዛ ቦታ ላይ በጥራት መሥራት ከተቻለ ብዙ ደንበኞች ይመጣሉ። ድርጅቱንም አሁን ብዙ ደንበኞቹን ሱቅ በመምጣት ነው ሥራ የሚያሠሩት።”

የኮቪድ ተፅዕኖ

ኮቪድ እና የነበሩ አለመረጋጋቶች የድርጅቱን ሥራ በጣም ጎድተውት ነበር። በዚህም ድርጅቱ ሥራ አቁሞ ነበር። አንዳንድ ትንንሽ የላንድ ስኬፕ ሥራዎችን በመሥራት ነው ያሳለፈው። በሁለቱም ችግሮች ምክንያት ክልሎች እና አዲስ አበባ መስተዳደር የሥራ ማስታወቂያ ማውጣት ካቆሙ ሦስት ዓመት ሊሞላቸው ነው። በዚህም ምክንያት አሁን ሱቅ ግጥም ብሎ ነው ያለው። ምርቱ ወደ ገንዘብ ቢቀየር ወደ አራት ሚሊዮን ብር ሊሆን እንደሚችል አቶ ደነቀ ጠቅሰዋል።

ምክር እና እቅድ

ወደ ገጸ-ምድር ማስዋብ ዘርፍ የሚገባ ሰው ግብርና የሚወድ፣ ከአፈር ጋር፤ ከዕፅዋት ጋር ማውራት የሚችል ሰው መሆን አለበት። በመቀጠል ትዕግስት ያለው ሰው መሆን ይኖርበታል፤ ምክንያቱም አንድ አትክልት አምስት ሳንቲሜትር ጨምሮ ለማደግ አንድ አመት ሊፈጅ ይችላል፤ ስለዚህ ይህ ማለት ዓመቱን ሙሉ አስፈላጊውን እንክብካቤ መስጠት፤ ይቺን እድገት ለማየት ሳይታከት በየቀኑ መንከባከብ አለበት።

ድርጅቱ የከፍታን አገልግሎት በቂ ግንዛቤ ባለመኖሩ በበቂ ሁኔታ እየተጠቀመበት አልነበረም፤ ይሁን እና አሁን ላይ ቢሮ በመምጣት አስፈላጊውን ግንዛቤ ስለጨበጠ 2merkato.com ለጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ያዘጋጀውን የከፍታ አገልግሎት በሚገባ እየተከታተለ ይገኛል።

ድርጅቱ ወደ ፊት በሌላ ዘርፍ  የራሱን ሪዞርት ለመገንባት፣ የቅመማ ቅመም እርሻ ለመጀመር እና ኤክስፖርት ለማድረግ እንዲሁም ይህንን ሥራ ለማስፋፋት እቅድ አለው።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …