መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ሂሳሊስ ጋርመንት
Sewing Machine

ሂሳሊስ ጋርመንት

ሂሳሊስ ጋርመንት የተመሠረተው በ 2010 ዓ.ም በወ/ሮ መሠረት ዳዱ ነው። ድርጅቱ የሚያመርታቸው የአልባሳት ምርቶች ከአንድ ዓመት እስከ አስራ ሦስት ዓመት ክልል ውስጥ ለሚገኙ ሕጻናት ነው። የአልባሳቶቹም ዋጋ የማኅበረሰቡን አቅም ያገናዘበ ነው። የአልባሳቶቹ ዋጋዎች ቢለያዩም ከዝቅተኛው ዋጋ መቶ ሰማንያ ብር (ብር 180) ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ዋጋ አራት መቶ ብር (ብር 400) በሚደርስ ዋጋ ለተጠቃሚዎች ያቀርባል።

ምሥረታና ዕድገት

ወ/ሮ መሠረት የልብስ ስፌት ሙያ ከመጀራቸው በፊት የተለያዩ ሥራዎችን ሞክረው ነበር ነበር፤ ለምሳሴ የሆቴል ሥራ እንዲሁም የጌጣ ጌጥ ሥራ የአበባ ቫዝ በሸክላ ሠርተው ቀለም በመቀባት እና በመንከር እያስጌጡ ይሸጡም ነበር። ነገር ግን ሥራው ውጤታማ አልነበረም። ከድካሙ አንጻር እና የሚያመጣው ትርፍ ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። የሸክላ እቃም ቶሎ ተሰባሪ ነው፤ በዚህ ምክንያት ብዙ ሰው አይፈልገውም። ስለዚህ ይህን ሥራ ትተው ወደ አረብ አገር ሄዱ። እዛም ይሠሩበት የነበረው ሥራ ከልብስ ጋር የተያያዘ በመሆኑ እና እሳቸውም ቀድሞውኑም የልብስ ሥራ ፍላጎት ስለነበራቸው ይሄ አጋጣሚ በልብስ ስፌት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት አሳደረባቸው። በዚህ ፍላጎት ምክንያት የልብስ ስፌት ትምሕርት ተምረው በመኖሪያ ቤታቸው በዐሥራ አንድ ሺህ ብር (ብር 11,000) ካፒታል የልብስ ስፌት ሥራን ጀምረዋል። በዐሥር ሺህ ብር (ብር 10,000) ማሽን ገዝተው እና በቀሪው አንድ ሺህ ብር (ብር 1,000) ጨርቅ በመግዛት ነው የልብስ ስፌት ሥራ የጀመሩት።

ወ/ሮ መሠረት በቤታቸው እየሠሩ እግረ መንገድ የመሥሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው ወረዳውን ይጠይቁ ነበር። በጠየቁት ጥያቄ መሠረት በ2010 ዓ.ም የመሥሪያ ቦታ ሲሰጣቸው በደንብ በዘርፉ መሥራት ጀምረዋል። ለሥራቸው ውጤታማነት መሆን በመደጋገም ያለ መለመታከት መሥራታቸው እና ከስህተታቸው በመማር አዳዲስ ነገሮችን መሞከራቸው፣ ሥራቸው ቀስ በቀስ እየተሻሻለ ሊመጣ ችሏል። ነገር ግን የልብስ ስፌት ሥራ ቀላል አይደለም በተለይ ደግሞ በመጀመሪያዎቹ ወቅቶች ምክንያቱም ተጠቃሚ እና ገበያ ማግኘት፣ ለሥራው የሚውል ግብዓት የሚገኝበትን ቦታ ማወቅ በተለይ ሥራው ሲጀመር በጣም ከባድ ነው፤  ከተጀመረም በኋላ ቀላል እንዳልሆነ ወ/ሮ መሠረት ያስረዳሉ። ጥሬ እቃ ማግኝት የልብስ ሥፌት ትልቁ ሥራ እንደሆነም አክለዋል።

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

የድርጅቱ የማምረት አቅም እንደ ሥራው አይነት ቢለያይም በቀን በአማካኝ ሀምሳ የጨርቅ አልባሳት እና ሰላሣ የሕፃናት ቬሎ የማምረት አቅም አለው። ዋጋቸውም አንደ አልባሳቱ ቢለያይም ከመቶ ሰማንያ ብር (ብር 180) ጀምሮ እስከ አራት መቶ ብር (ብር 400)  ድረስ አምርቶ ለተጠቃሚ ያቀርባል። ድርጅቱ በአሁን ጊዜ አሥራ ሦስት ቋሚ እና አምስት ጊዜያዊ ሠራተኞች ቀጥሮ እየሠራ ይገኛል። እንዲሁም አምስት ምርቱን በመውሰድ ለባለሱቆች የሚያስረክቡ የጅምላ ተረካቢ ደንበኞች አሉት።

ድርጅቱ ሲጀመር በአንድ ማሽን እና በአንድ ሰው ነበር፤ በአሁኑ ጊዜ የዐሥራ አምስት ማሽኖች ባለቤት ሲሆን እንዲሁም ካፒታሉን ወደ ስምንት መቶ ሺህ ብር (ብር 800,000) ማሳደግ ችሏል። ሥራ ሲጀምር ከነበረው የምርት ጥራት ደረጃ አሁን ያለበት የጥራት ደረጃ በጣም የተሻሻለ ነው።

የኮቪድ ተፅዕኖ

የኮቪድ ተፀዕኖ ለሂሳሊስ ጋርመንት ጥሩ ነበር፤ ምክንያቱም ህብረተሰቡ የሚጠቀመው አልባሳት ከውጭ የሚመጡ ልብሶችን ነበር። ጥራታቸውም የተሻለ ስለነበር ያንን ገበያ ሰብሮ ለመግባት በጣም ከባድ ነበር ነገር ግን ኮቪድ ሲመጣ ከውጭ የሚመጡ ልብሶች መምጣት ስላቆሙ ሰው የሀገር ውስጥ ምርት መጠቀም ጀምሯል። ይህም የድርጅቱ ምርት በደንብ አንዲታወቅ እና እንዲስፋፋ አድርጓል። የማስክ ሥራን ግን ዘግይተው ስለነበር የጀመሩት ብዙም ተጠቃሚ አልነበሩም ።

ድርጅቱ ምርቱን የሚያስተዋውቀው በባዛር እና በሰው በሰው ነው እንዲሁም ቢዝነስ ካርድ ይጠቀም ነበር። በቅርብ ጊዜ ግን ባዛር ስለቀነሰ እና ሥራውም በደንብ ስለታወቀ ቢዝነስ ካርድ መጠቀም አቁሟል። ድርጅቱን እያስቸገረው ያለው በቂ ጥሬ እቃ አቅርቦት አለመኖር ብቻ ነው።

ምክር እና እቅድ

ወ/ሮ መሠረት ድርጅቱን ለማማሻል የተለያዩ መንገዶችን ይጠቀማሉ። ቴክኖሎጂ በመጠቀም ዲዛይን ይመለከታሉ። እንዲሁም ከወረዳው በተለያየ ጊዜ የሚወስዷቸው አጫጭር ኮርሶች፣ የካይዘን ሥልጠና እና የሂሳብ አያያዝ ሥልጠናዎች ሥራቸውን ለማሳደግ ረድተዋቸዋል። የማምረቻ ቦታ ጥበት አለ፤ ይህንንም ለማስተካከል ከሚመለተከው አካል ጋር በመነገጋር የማስፋፊያ ቦታ ለማግኘት እና አዳዲስ ማሽኖችን ለማስገባት በሂደት ላይ ይገኛሉ።

ወ/ሮ መሠረት ድርጅቱን ከመሠረቱ በሁዋላ ብዙ ሰው ያማክሩ ነበር ይህም ብዙ ሀሳብ ስለሚያመጣ ውጤታማ አልነበረም። ስለዚህ ጥቂት ሰዎችን ብቻ ማማከር መጀምራቸው እንደ ጠቀማቸው ገልጸዋል። ሌላው ነገር ደግሞ እራሳቸው ስለወደዱት ብቻ ብዙ እቃ ይገዙና በብዛት ያመርቱ ነበር ነገር ግን ይህም አሠራር ኪሳራ አስከትሎባቸው ነበር። ስለዚህ በቅድሚያ ሳምፕል በማዘጋጀት ምርቱ ተፈላጊ ከሆነ በብዛት ይሠራል ካልሆነ ግን ብዙ ኪሳራ ሳያስከትል አይመረትም ሲሉ ገልጸዋል።

አዲስ ወደ ልብስ ስፌት ለሚገቡ ሰዎች አለመሰልቸት፣ ታጋሽ መሆን፣ ተስፋ አለመቁረጥ፣ ዛሬ ባይሳካ ነገ ይሳካል የሚል አሥተሳሰብ ቢኖራቸው፣  ሠራተኞችን እንደ ባሕሪያቸው መያዝ፣ እንዲሁም በጣም ቻይ መሆን እንደሚገባ – ያለበለዚያ ሠራተኛ አይቀመጥም ደንበኛም አይመጣም እና የመፍጠር አቅምም ሁሌ አዲስ ነገር የመሥራት ችሎታ ሊኖር ያስፈልጋል። ዘርፉ ሰፊ የሥራ እድል አለው፤ በተለያየ ዘርፍ ትንሽ የማቴሪያል እቃ ችግር አለ እንጂ ሥራው ብዙ ነው። የጥሬ እቃ አቅርቦት ችግር ደግሞ ሥራው ሲበዛ ነጋዴዎች የእቃውን ተፈላጊነት አይተው ማምጣት ይጀምራሉ። ይህም የጥሬ እቃ ምርት ችግርን ያስተካላል ብለዋል።

ለወደፊት ድርጅቱ ከሶስት እስከ አምስት ዓመት ድረስ ውስጥ የራሱን የአልባሳት መሸጫ ሱቆች የመክፈት ሀሳብ አላቸው። እንዲሁም ምርታቸውን ከፍታ ቴሌግራም ቻናል ላይ ለማስተዋወቅ አቅደዋል።

የድርጅቱ መሥራች ወ/ሮ መሠረት ለዚህ ደረጃ ለመድረስ የረዷቸውን ቤተሰባቸውን፣ ጓደኞቻቸውን እና ደንበኞቻቸውን በሙሉ አመስግነዋል ።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …