መነሻ / የጥቃቅን እና አነስተኛ መረጃ / ወቅታዊ መረጃ / ከስጋ እና ወተት ምርት 68.13 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኘ
meat_slaughterhouse

ከስጋ እና ወተት ምርት 68.13 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኘ

በ2012 በጀት ዓመት 11 ወራት ውስጥ ወደ ውጪ ከተላከ የስጋና ወተት ምርት 68.13 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒቴር ገለጸ፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የስጋና ወተት ኢንስቲትዩት የ2012 በጀት ዓመት የ11 ወራት የኤክስፖርት አፈፃፀምን በዘርፉ ከተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ጋር ገምግሟል፡፡

በበጀት ዓመቱ 11 ወራት ከስጋና ወተት 113.81 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 68.13 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን ከበግና ፍየል ስጋ 61.31 ሚሊዮን ዶላር፣ ከዳልጋ ከብት 1.3 ሚሊዮን ዶላር፣ ከእንስሳት ተረፈ ምርት 2.93 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ከማር፣ ከሰም፣ ከዓሳ ምርት እና ከወተት 2.60 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡

የእርድ እንስሳት አቅርቦት ጥራት ችግር፣ የእንስሳት ማቆያ እጥረት፣ የብድር አቅርቦት እጥረት፣ ህገ ወጥ የቁም እንስሳት ንግድ እና የመብራት መቆራረጥ ምክንያት የተያዘውን እቅድ ሙሉ በሙሉ መፈጸም አልተቻለም ሲሉ የስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲቱት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ጋሹ ተናግረዋል፡፡

በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድ ማስፋፊያ ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በበኩላቸው ከሚፈለገው አካል ያለመድረስ እንጅ የአቅርቦት ችግር የለም ያሉ ሲሆን በአቅራቢዎች እና በቄራዎች መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት እንዲኖር እና የአቅርቦት ሰንሰለቱን ለማሳጠር እንሰራለን በማለት ተናግረዋል፡፡

ዘርፉ አትራፊ ሆኖ አርብቶ አደሩ ተጠቃሚ የሚሆንበትን አሰራር በመዘርጋት የኤክስፖርት ስታንዳርድ ዋጋ በማዘጋጀት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እንሰራለን ሲሉም አምባሳደሩ አክለዋል፡፡

ምንጭ፦  የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የፌስቡክ ገጽ  – ዘገባው የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ነው

 

ይህንንም ይመልከቱ

kefta-care-training-2

ከፍታ ለ20 ኢንተርፕራይዞች ሥልጠና ሰጠ

ከፍታ ከኬር ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ለ20 በሴቶች ለሚተዳደሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ሥልጠና ሰጠ። ሥልጠናው ያተኮረው …