መነሻ / የቢዝነስ ዜና / የማምረቻ ተቋማት የሚያጋጥማቸውን የኃይል አቅርቦት ችግር ሊፈታ የሚያስችል የስምምነት ሰነድ ተፈረመ
electric-power

የማምረቻ ተቋማት የሚያጋጥማቸውን የኃይል አቅርቦት ችግር ሊፈታ የሚያስችል የስምምነት ሰነድ ተፈረመ

በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መካከል የማምረቻ ተቋማት የሚያጋጥማቸውን የኃይል አቅርቦት ችግር ሊፈታ የሚያስችል የስምምነት ሰነድ ተፈረመ። የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት የማምረቻ ኢንዱስትሪ ተቋማት የሚያጋጥማቸውን የኃይል አቅርቦት ችግር ሊፈታ የሚያስችልና ሁለቱ ተቋማት ሀገራዊና ተቋማዊ ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ነው።

ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን ወክለው ስምምነቱን የፈረሙት የአግሮ-ፕሮሰሲንግና ፋርማሲዩቲካል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረየሱስ ካሁን ቀደም የኃይል አቅርቦት እጥረትና መቆራረጥ አብዛኛዎቹ የአምራች ኢንዱስትሪ ተቋማት ከሚያነሷቸው ችግሮች ውስጥ ዋነኛው መሆኑን ተናግረዋል። ችግሮቹ አብዛኞቹን የማምረቻ ተቋማት በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ ትልቅ ተግዳሮት መሆኑን ገልጸው ስምምነቱ የዘርፉን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ ትልቅ አማራጭ ነው ብለዋል።

ካሁን ቀደም እንዲህ ያለ ስምምነት ባለመኖሩ ምክንያት የኃይል አቅርቦትን አስመልክቶ የማምረቻ ተቋማት የሚያነሷቸው በርካታ ችግሮች በተበጣጠሰ መልኩ ይቀርቡ የነበረ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ የመግባቢያ ስምምነቱ የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት ሁለቱ ተቋማት በቅንጅት እንዲሠሩ የሚያስችል እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን ወክለው ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ በበኩላቸው ስምምነቱ ሃገሪቱ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር የምታደርገውን መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ለመርዳትና ለማፋጠን ላቅ ያለ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡ መሥሪያ ቤታቸውም የማምረቻ ተቋማት በኅይል አቅርቦት ዙሪያ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት በቀጣይ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

ይህንንም ይመልከቱ

kefta-care-training-2

ከፍታ ለ20 ኢንተርፕራይዞች ሥልጠና ሰጠ

ከፍታ ከኬር ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ለ20 በሴቶች ለሚተዳደሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ሥልጠና ሰጠ። ሥልጠናው ያተኮረው …