መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ግሬስ ኢንጂነሪንግ

ግሬስ ኢንጂነሪንግ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ተሾመ ደበሌ እና በአራት መሥራች አባላት በ2009 ዓ.ም ነው። ድርጅቱ የሚሠራቸው ሥራዎችን አጠቃላይ የማሽነሪ እና የብረታ ብረት ሥራዎች ናቸው።

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ማሽኖች

 • የሽንኩርት እና ቅመማ ቅመም መፍጫ ማሽን
 • የብሎኬት ማምረቻ ማሽን
  • የምግብ ማቀነባበሪያ ማሽኖች
  • ሀመር ሚል (መርቴሎ)
  • የመኖ መደባለቂያ
  • የሳር መፍጪያ
 • ስክሩ ኮንቬየር
 • ኢምፓክት የላይም ስቶን እና የጀሶ ድንጋይ መፍጫ
 • ፓሌት የእንስሳት መኖ ማምረቻ
 • ዊንች (የኮንስትራክሽን ግብዓት ማውጫ)
 • የእህል ማበጠሪያ ማሽን
 • ኮምቼ መፍጭያ
 • ወተት መናጫ
 • የዳቦ መጋገሪያ ማሽን፤ ሊጥ ማቡኪያ እና ማኮፈሻ
 • ከንፁህ ጋልቫናይዝድ ላሜራ የተመረተ ባለ 20 እሰከ ባለ200 ዲያሜትር ስፋት ያለው ክላምፕ
 • የፋብሪካ ገጠማ
 • የሳይት ላይ ወርክሾፕ ሥራዎች
 • ከንቾች
 • ሀይድሮሊክ ሥራዎች
 • የመጋዘን ግንባታ በብረት መገንባት
 • የደረቅ እና ፈሳሽ ሳሙና ማምረቻ ማሽኖች
 • የበረኪና ማሸጊያ ማሽን
 • የላርጎ መሳቢያ ፓምፕ

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

አቶ ተሾመ የግላቸውን ድርጅት ከመመሥረታቸው በፊት በብረታ ብረት ሥራ ተቀጥረው ለሦስት ዓመት ሰርተዋል። አስፈላጊውን ልምድ ካካበቱ በኋላ በግላቸው የሚያስቧቸው የፈጠራ ሥራዎች ስለነበሩ እነዛን ሀሳቦች ወደ ተጨባጭ አገልግሎት ሰጪ ማሽኖችን ለመቀየር በማሰብ ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ተሾመ ገላዬ እና ጓደኞቻቸው ብረታ ብረት ሥራ ድርጅት በአምስት ሺህ ብር ካፒታል ተመሠረተ። ይህ ድርጅት በአምስት መሥራች አባላት ቢመሠረትም አሁን ላይ ሦስት መሥራች አባላት ብቻ በውስጡ ይዟል ሁለቱ አባላት የራሳቸውን ድርጅት መሥርተዋል።

ድርጅቱ በአምስት ሺህ ብር ካፒታል ቢመሠረትም አሁን አጠቃላይ የካፒታል መጠኑን ማሽነሪዎች እና ጥሬ እቃ አካቶ ሦስት ሚሊዮን ብር አድርሷል። በተጨማሪም ለዐሥራ አንድ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ሲሆን ከዚህም ውስጥ ሦስቱ ቋሚ ሲሆኑ ስምንቱ ደግሞ ጊዜያዊ ሠራተኞች ናችው።

ድርጅቱ ትልቅ አቅም ያለው የሽንኩርት መፍጫ ማሽን በሦስት ቀን የማጠናቀቅ አቅም ያለው ሲሆን፤ ይህንንም ማሽን በሃያ ሰባት ሺህ ብር ለገበያ ያቀርባል። በተጨማሪም የመኖ ማቀነባበሪያ  ማሽን በአንድ ወር ማጠናቀቅ ይችላል። ከዚህም ጋር አያይዞ ለሚያመርታቸው ምርቶች የአንድ አመት ዋስትና እና ሙሉ የጥገና አገልግሎት ይሰጣል።

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች በአገር ውስጥ የማይመረቱ ነገር ግን መመረት የሚችሉ ማሽኖች ሲሆኑ እነዚህን ማሽኖች በመጠቀም የተለያዩ የምርት ውጤቶችን ማምረት ያስችላል። ለምሳሌ ክላምፕ የፒቪሲ ማሰሪያ ብረት ከውጭ አገር ነበር የሚገባው አሁን ማሽኑ በማምረት በአገር ውስጥ ክላምፖችን በማምረት ለገበያ አቅርቧል። ይሁንና አሁን ባለው የጥሬ እቃ እቅርቦት ችግር ምርቱ ለጊዜው ቆሟል። ሌላው ምርት ደግሞ ማኔላ የሚባለው የመስኮት መዝጊያ እና መክፈቻ እንዲሁም ሀመር መዶሻ ጠጠር መፍጫ በመሥራት ለገበያ አቅርቧል።

ድርጅቱ ለግሉ የሚጠቀምበት በጣም ጠቃሚ ሚሊንግ የሚባል ማሽን በመሥራት እየተገለገለበት ይገኛል፤ ለሽያጭ ግን አልቀረበም ምክንያቱም ጥሬ እቃ አቅርቦት እጥረት ችግር አለ። ድርጅቱም ማሽኑን የሠራው ከአሮጌ ማሽኖች የተለያዩ እቃዎችን በመሰብሰብ ነው። ወደ ፊት የጥሬ እቃ አቅርቦት ችግር ከተፈታ በብዛት አምርቶ ለገበያ የማቅረብ እቅድ አለው።

ድርጅቱ ልምድ እና ክህሎቶችን በጊዜ ሂደት እያካበተ የመጣ ሲሆን በተጨማሪም የአምስት ቀን ሥልጠና ከምስራቅ ጮራ ኮሌጅ  ወስዷል። ይህ ድርጅት ተማሪዎችን ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በመቀበል የፕረንቲስሺፕ አገልግሎት በመስጠት እና ኃላፊነት የሚሰማቸው ብቁ ዜጎች በመቅረፅ ሃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል፤ በዚህም ሥራው የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝቷል – ለአብነት ከአቢሲኒያ ድርጅት የበጎ ሥራ ሽልማት ተሸልሟል።

ድርጅቱ ሥራዎችን የሚሠራው በስልክ እና በሰው በሰው ሲሆን ይህም ከቀደሙ ደንበኞች ጥሩ ሥም ስላለው ይህን መንገድ በመጠቀም ሥራዎችን ይሠራል። ሌላ ምንም ዓይነት የማስታወቂያ መንገድ አልተጠቀመም። አሁን ግን በከፍታ በተዘጋጀው ሀሳብ መስጫ መድረክ ላይ የተገኙት አቶ ተሾመ ማስታወቂያ ያለውን ጥቅም በመገንዘባቸው የከፍታ 2merkato.com የማስታወቂያ ወይም የገበያ ትስስር አገልግሎትን በሚገባ ለመጠቀም ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።

የኮቪድ ተፅዕኖ

ኮቪድ የነበረው ተፅዕኖ ከባድ ነበር፤ እንደልብ መንቀሳቀስ አይቻልም መደበኛ ሥራዎችን ቀንሰው የነበረ ሲሆን ሥራ ቢቀዘቅዝም አንዳንድ ሥራዎችን መሥራት ችለው ነበር። እንዲሁም በእግር የሚረገጥ የእጅ መታጠቢያ ሠርተው ለጤና ጣቢያዎች በሽልማት አበርክተዋል።

ምክር እና እቅድ

ወደ ዘርፉ የሚገቡ ሰዎች የሥራው ፍላጎት ያላቸው እና ጥሩ የፈጠራ ችሎታ እና አቅም ያላቸው ቢሆኑ፤ በመቀጠል እውቀት እንዲሁም ትክክለኛ የሰዓት አጠቃቀም ኖራቸው ሥራውን ቢጀምሩ መልካም ነው ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

 

ድርጅቱ በሚቀጥሉት የሦስት አመት ጊዜዎች ውስጥ በግብርና ሥራ ብዙ ችግር ፊቺ ማሽኖች በማምረት በዘርፉ ያለውን ችግር መፍታት እና በግብርና ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ የማምጣት እቅድ አለው። ይህንንም ዕቅድ ለማሳካት ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።

እንደተጨማሪ መንግሥት ያለውን የቦታ ችግር ተረድቶ የመሥሪያ ቦታ ቢሰጣቸው እና የጥሬ እቃ አቅርቦት ችግር ቢቀርፍላቸው ድርጅቱ ለሀገር ጠቃሚ የሆኑ ብዙ ማሽኖችን በማምረት ብዙ የውጭ ምንዛሬ ወጪን ማስቀረት እንደሚችል የድርጅቱ መሥራች አባል ሀሳባቸውን ገልጸዋል።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …