መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ገነት ልብስ ስፌት
genet-garment

ገነት ልብስ ስፌት

ድርጅቱ የተመሠረተው በ2011 ዓ.ም. በወ/ሮ ገነት የግል ኢንተርፕራይዝ ሆኖ ነው። ይህ ድርጅት የሚያመርታቸው ምርቶች ባህላዊ እና ዘመናዊ ልብሶችን ሲሆን በይበልጥ ደግሞ የሴቶች እና የህጻናት ባህላዊ ልብሶችን ከዘመናዊ ልብሶች ጋር በማጣመር ያመርታል።

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች

  • ቲሸርት
  • ሱሪ
  • ቀሚስ
  • ጋዋን
  • ባህላዊ የቤቢ ሻወር ልብሶች
  • ዘመናዊ የሱፍ ሱሪዎች እና
  • ሀበሻ ቀሚሶች

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

ወ/ሮ ገነት ወደ ልብስ ስፌት ሥራ ዘርፍ ከመሠማራቻቸው በፊት የጥልፍ ሥራዎችን በመሥራት ለሁለት ዓመት ቆይተዋል። ይህም የልብስ ስፌት ሥራውን ሲጀምሩ የጨርቅ ኳሊቲ፣  የክር ዓይነት ምን አይነት ጥንካሬ ይኖረዋል እና ምን ዓይነት ጥልፍ ነው ለዘመናዊ የልብስ ስፌት ንድፍ የሚሆነው የሚሉትን እና ሌሎች ብዙ ጠቃሚ ነገሮችን እንዲያውቁ አድርጓቸዋል። የድርጅቱ መሥራች የጥልፍ ሥራን በመተው ወደ ልብስ ስፌት እንዲገቡ ያደረጓቸው ሁለት ዓበይት ምክንያቶች ሲሆኑ አንዱ የጥልፍ ሥራ ዐይን ያማል፤ ሁለተኛው ደግሞ ለጀርባ እና ወገብ አስቸጋሪ ነው። በእነዚህ ምክንያቶች ነው ወ/ሮ ገነት ወደ ልብስ ስፌት የሥራ ዘርፍ የተቀላቀሉት።

ገነት ልብስ ስፌት ሥራዎችን የሚሠራው ብዙ ጊዜ ከተጠቃሚ ደንበኞች በሚመጡለት ትዕዛዞች ሲሆን፤ ሌሎች ደግሞ ምርቶቹን ከኢንተርኔት ላይ በማየት እና ሰዎችን በመጠየቅ እንዲሁም ከባዛር ላይ በማየት እየመጡ ያሠራሉ።

ድርጅቱ በቀን ሰባት የሀበሻ ቀሚስ የማውጣት አቅም አለው። እንዲሁም ለሁለት ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ድርጅቱ ሲመሠረት መነሻ ካፒታል አምስት አሥር ሺህ ብር ነበር፤ ካፒታሉ አሁን ሃያ አምስት ሺህ ብር ደርሷል።

ድርጅቱ የሚያቀርባቸው ምርቶች ዋጋ በከፊል

  • ሀበሻ ቀሚስ – ከሰባት መቶ ብር እስከ አሥራ አምስት ሺህ ብር
  • የልጆች ቀሚስ – ከአራት መቶ ብር እስከ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር ለገበያ ያቀርባል።

በተጨማሪም ሌላ ምርት የሚፈልግ ተጠቃሚ የሚፈልገውን ልብስ በተመጣጣኝ ዋጋ ማሠራት ይችላል።
ወ/ሮ ገነት በልብስ ስፌት ሥራ ውስጥ በሂደት የተማሩት ነገር ጥራት ያለው እና በጣም ውድ የሆነ ምርት በብዛት ማኅበረሰቡ እንደማይገዛ ነው። በብዛት ተጠቃሚ የሚገዛው ረከስ ያለ ዋጋ ያለው ምርት ስለሆነ እሳቸውም ይህንን በመረዳት የጥራት ደረጃውን ከዋጋው ጋር በማመጣጠን ረከስ ያሉ ምርቶችን በማምረት ለገበያ ያቀርባሉ። ነገር ግን በጥራት እንዲሠራላቸው የሚፈልጉ ደንበኞች ከመጡ ድርጅቱ በጥራት ምርት ያመርታል።

የኮቪድ ተፅዕኖ

ድርጅቱ በኮቪድ ወቅት ሙሉ በሙሉ ሥራ አቁሞ ነበር። ትንሽ ሁኔታዎች ሲረጋጉ ማስክ መሥራት ጀምሮ ነበር ቢሆንም ወዲያው ከፋብሪካ የመጡት ማስኮች ገበያውን ስላጥለቀለቁት ሥራውን አቀዝቅዞታል። እናም አስቸጋሪ ጊዜ አሳልፏል።

ምክር እና እቅድ

ወ/ሮ ገነት 2merkato.com ለጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ያዘጋጀውን የከፍታ አገልግሎት  ልዩ የኮቪድ ጊዜ ፓኬጅ የነጻ እድል ተጠቃሚ ነበሩ። ነገር ግን ጨረታ አሸንፎ ለመሥራት በአንድ  እና በሁለት ማሽን ከባድ ሆኖባቸዋል። ስለዚህ እንደ እቅድ በሚመጡት ሦስት ዓመታት ውስጥ የህጻናት አልብሳት ሥራ ጥሩ ተሞክሮ ስላገኙበት በእሱ መቀጠል ነው የሚፈልጉት። እንዲሁም የከፍታ ድረ ገጽ ላይ ገብተው ያሉትን የብድር እና ቁጠባ ተቋማት በማየት እና በማጥናት፣ ከሚመቻቸው ጋር በመበደር፤ አቅማቸውን አሳድገው በቀን እስከ ዐሥር ሺህ የሚደርሱ የህጻናት አልባሳትን የሚያመርት ድርጅት የመሆን እቅድ አላቸው።በተጨማሪም የምርት ማሳያ ሱቅ ለመሥራት አቅደዋል።

ወደ ልብስ ስፌት ሥራ የሚገባ ሰው በዋናነት ደንበኛውን የሚያዳምጥ መሆን አለበት፤ የደንበኛውን ፍላጎት የሚቀበል እና የሚተገብር። ሁለተኛ ደግሞ ስልቹ መሆን የለበትም ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …