መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ጎዳዳ፣ መርጊያ እና ጓደኞቻቸው የሻማ ውጤቶች ማምረቻ

ጎዳዳ፣ መርጊያ እና ጓደኞቻቸው የሻማ ውጤቶች ማምረቻ

ድርጅቱ የተመሠረተው በ 2006 ዓ.ም በዐሥራ ዘጠኝ መሥራች አባላት ሲሆን አሁን ላይ ግን በዘጠኝ መሥራች አባላት እየሠራ ይገኛል። ከአባላቱም መካከል ሴቶችና አካል ጉዳተኞች ይገኙበታል፡፡ ድርጅቱ የተለያዩ ሻማዎች በተለያየ ዲዛይን ያመርታል እንዲሁም የጧፍ ምርቶችን ያመርታል።

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

ወ/ሮ ጎዳዳ ወደዚህ የሥራ መስክ ከመግባቸው በፊት በግላቸው ጧፍ በማምረት ለገበያ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። በዚህ ሥራ ላይ እያሉ SDDC የሚባል ተራድኦ ድርጅት ከሌሎች አባላት ጋር በሻማ ማምረት ያለውን ሰፊ ገበያ በመመልከት በመስኩ እየሠሩ ያሉትን አሠልጥኖ ወደ ምርት እንዲገቡ አድርጓቸዋል።

 

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ሻማዎች

  • ለልደት
  • ለሰርግ
  • ለሀዘን
  • ለሆቴሎች እና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ የተለያዩ ሻማዎችን ያመርታል።

ድርጅቱ በአዲስ አበባ በሻማ ሥራ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ደረጃ የመጀመሪያ ሲሆን በቀን አምስት መቶ ሻማ እና አራት ሺህ ጧፍ የማምረት አቅም አለው። ድርጅቱ ሲመሠረት በአንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ብር ካፒታል ሲሆን በአሁኑ ወቅት የድርጅቱ ካፒታል ሰባት መቶ ሺህ ብር ደርሷል።

ድርጅቱ የሚያቀርባቸውን ሻማዎች ከዐሥር ብር አስከ ሦስት መቶ ብር ገደማ በሆነ ያቀርባል። ለምሳሌ፦

    • ትንሿን የኬክ ሻማ በዐሥር ብር ያቀርባል።
    • ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ የተለያየ ቀለም እና መዓዛ ያላቸው ሻማዎችን ደግሞ በሰማንያ ብር ገደማ ያቀርባል።
    • በጣም ትልቅ የሚባለውን ሻማ ደግሞ ሁለት መቶ ሰባ አምስት ብር ያቀርባል።

ድርጅቱ ከመመሥረቱ በፊት አባላቱ  የአራት ወር ሥልጠና ወስደዋል፤ እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት ለጥቃቅን እና አነስተኛ ድርጅቶች የሚሰጡ፣ ከአንድ እስከ አራት ቀናት የሚቆዩ ሥልጠናዎችን ወስደዋል። በአሁን ጊዜ በቂ ሥልጠና ስለወሰዱ ለሌሎች ተማሪዎች በልምምድ (apprenticeship) መልክ ሥልጠናዎችን ይሰጣሉ። እንዲሁም በክፍያ ሌላ ቦታ በመሄድ የሻማ ሥራ ሙያን ለሌሎች እያስተማሩ ይገኛሉ። ከተለያዩ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጆች ጋር በ University and Industry Link አማካኝነት ተሞክሮ በመለዋወጥ እየሠሩ ይገኛሉ።

ድርጅቱ ሥራ በጀመረበት ወቅት ጥሩ የምርት ፍላጎት ነበር። ወ/ሮ ጎዳዳ በጧፍ ሥራ ያላቸው ልምድ እንዲሁም የሚያውቋቸው ደንበኞችን ወደ ድርጅቱ በማምጣት ብዙ ሥራዎች ሠርተዋል። ምርታቸውንም መኪና በመከራየት ከቀጥተኛ ተገልጋዮች ጀምሮ እስከ ጅምላ ተረካቢዎች እና ለቤተክርስቲያኖች እና ለሃይማኖት ተቋማት ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

ድርጅቱ ሥራ የሚሠራው በሰው በሰው እንዲሁም ሄሎ ማርኬት ጋር በገባው ውል መሠረት እቃውን ሄሎ ማርኬት ተረክቦ የራሱን ኮሚሽን በመጨመር ይሸጠዋል። በተጨማሪ ደግሞ አፍሪካ የሚባል ዌብሳይ ላይ ስምንት ሺህ ብር ከፍለው እያስተዋወቁ ነው፤ ግን የሚጠበቀውን ያህል ውጤት አላገኙበትም እንደነሱ በሰው በሰው መሥራት የተሻለ ነው ባይ ናቸው።

አሁን ድርጅቱ ላይ ትልቅ ፈተና የሆነበት ነገር የጥሬ እቃ አቅርቦት ነው። ከሦስት አመት በፊት እቃ ይቀርብ የነበረው ከግብፅ ሲሆን በአባይ ግድብ ምክንያት የሰም ግብዓት ግብፅ መላክ አቁማለች። ቱርክ እና ኢራን ዋጋ በጣም አስወድደዋል፤ ለሻማ ሥራ ደግሞ ሰም ዋና ግብዓት ነው። እሱ ከሌለ ምንም መሥራት አይቻልም በዘርፉ ትልቅ ገበያ አለ፤ ስለዚህ መንግሥት ይህንን ችግር ቢፈታው ጥሩ ነው ይላሉ ወይዘሮ ጎዳዳ። ሌላው ችግር ደግሞ ድርጅቱ በዘርፉ ቀዳሚ እንደመሆኑ ለሥራው ያዘጋጃቸው ሞልዶች መጠናቸው ትልቅ ነው። አሁን ላይ የድርጅቱ አንድ ሻማ ሌላ ቦታ ሁለት ሊያወጣ ይችላል። በዚህ ደግሞ ጥሬ እቃ ሲጠፋ በጣም አስቸጋሪ ያደርገዋል ብለዋል ወ/ሮ ጎዳዳ።

ድርጅቱ ከተመሠረተ ጊዜ አንስቶ የሚሠራቸው ሥራዎች በይበልጥ ጨምሯል። የገበያ ውድድር ላይ ያላቸውን አቅጣጫ አስተካክለዋል፤ ይህም ማለት የተለያዩ የሻማ ዲዛየኖችን በማዘጋጀት የተለያዩ የሻማ ቅርጾች ማምረት ጀምረዋል፡፡

የኮቪድ ተፅዕኖ

በኮቪድ ምክንያት የሚመጣ የግብዓት እቃ ከፍተኛ እጥረት ነበር። በድርጅቱ ውስጥ ያለው እቃም ነጋዴም መግዛት በማቆሙ ደመወዝም መክፈል አልተቻለም ነበር። በተጨማሪም ለአንዳንድ አካል ጉዳተኛ የድርጅቱ አባላት የመንገዱ ሁኔታ ስለማይመች ሥራውን ለአንድ አመት በማቆም በቤታቸው እንዲቀመጡ ተገደው ነበር።

ምክር እና እቅድ

ወደ ሻማ ሥራ አዲስ ለሚገቡ ሰዎች ገበያ ማወቅ አለባቸው፤ ጥሬ እቃ እንዴት ማግኘት እንዳለባቸው ማወቅ እና በቂ ሥልጠና ሊኖራቸው ይገባል። ጥሬ እቃ ካለ በዘርፉ ሰፊ የሥራ እድል አለ ብለዋል ወ/ሮ ጎዳዳ።

ምርቱን በማሳደግና በማጥራት ሂደት በሀገር ውስጥ ጥሬ እቃ የሚመረትበትን እድል ቢፈጠር ከፍተኛ ውጤት ያስከትላል። ይህ ከተቻለ ከውጭ የሚመጣውን ሻማ በማስቀረት የውጭ ምንዛሬ ከማዳን በተጨማሪም ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ያስችላል ሲሉ የድርጅቱ መሥራች ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …