መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ሌዘር ፕላስ ኢትዮጵያ
plus-leather-ethiopia-logo

ሌዘር ፕላስ ኢትዮጵያ

ሌዘር ፕላስ ኢትዮጵያ የተመሠረተው በአቶ ተመስገን አባተ 2015 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ የቆዳ ቦርሳዎችን በጥራት በማምረት ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ሀገር ገበያ የሚያቀርብ ድርጅት ነው።

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች

  • ቦርሳ እና ቀበቶ
  • ለተለያየ አክሰሰሪ የሚውሉ ኬዞች
  • የታብሌት ኬዞች
  • ባይንደር
  • ሆልደር ባግ

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

አቶ ተመስገን ወደ ቆዳ ሥራ ለመግባት ያነሳሳቸው ከድሮም ጀምሮ ለሥራው ያላቸው ፍላጎት፣ ሥራው በቀላሉ በሀገር ውስጥ ያለ ውጭ ምንዛሪ ፍላጎት መሠራት መቻሉ እና ሀገር ውስጥ ከበቂ በላይ ጥሬ እቃ እና እምቅ ሀብት በመኖሩ ነው። በደንብ ከተሠራበት ደግሞ ከሀገር አልፎ ኤክስፖርት በመደረግ የውጭ ምንዛሪ ያመጣል የሚለውን በማጥናት ወደ ሥራው ገብተዋል።

አቶ ተመስገን የቆዳ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት በአርክቴክቸር ሙያ ለሰባት ዓመታት በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በማስተማር እና እንዳንድ የዲዛይን ሥራዎችን በግል ሲሠሩ ቆይተዋል። የቆዳ ሥራ ወስጥ ለመግባት ከነበራቸው ፍላጎት የተነሳ በሚያገኙት ትርፍ ጊዜ ስለቆዳ ጥናቶችን ሲያጠኑ በሀገራችን ያለው የቆዳ ሥራ ዲዛይን ተመሳሳይ መሆኑን ሌላው ደግሞ  የጥራት ጉድለት መኖሩን ዐወቁ። ይህንንም ካወቁ በኋላ የዲዛይን ዕውቀት ስላላቸው ዩቲዩብን በመጠቀም ስለ ስፌት፣ ስለ ቆዳ አቆራረጥ እና አጠቃቀም እንዲሁም ተያያዥ ነገሮችን ከተማሩ በኋላ በሦስት መቶ ሺሕ ብር (ብር 300,000) መነሻ ካፒታል አምስት ማሽኖችን በመያዝ ወደ ሥራው ገብተዋል።

ድርጅቱ አሁን ባለው ምርት የማምረት አቅም በአንድ ቀን ዐሥራ ዐምስት ትልቅ ተብለው የሚመደቡ የሴት ቦርሳዎችን የማምረት አቅም አለው። ለዚህም ምክንያቱ የድርጅቱ የሥራ ባሕል እንደሆነ የድርጅቱ መሥራች ጠቅሰዋል። ይህም ባሕል ከጠዋት ዐሥራ ሁለት ሠዓት ጀምሮ እስከ ማታ ሁለት ሠዓት ድረስ ለስድስት ወር በተከታታይ መሥራቱ ለድርጅቱ አጠቃላይ እድገት ጉልህ ሚና እንዳለው የድርጅቱ መሥራች ጠቅሰዋል።

ድርጅቱ ከሌሎች ደርጅቶች ልዩ የሚያደርገው ሌላው ነገር የራሱ የሆነ ሃምሳ የዲዛየን ፓተንት ያለው ሲሆን ሌሎች ደግሞ ወቅቱን የጠበቁ ፋሽኖች ሲመጡም በጥራት በማምረት ጊዜውን የሚመጥን ምርት ለገበያ ማቅረብ መቻሉ ሌላው ተጠቃሽ ነገር እንደሆነ የድርጅቱ መሥራች አክለዋል። ድርጅቱ በአሁን ሰዓት ለሦስት ቋሚ እና እንደ ሥራው ሁኔታ ለሚጨመሩ ሁለት ጊዜያዊ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል።

የምርቶቹ ዋጋ

  • የሴት ቦርሳ ከብር 800 (ስምንት መቶ ብር) እስከ ብር 1,000 (አንድ ሺሕ ብር)
  • የወንድ ቦርሳ ከብር 600 (ስድስት መቶ ብር) እስከ 1,000 ብር (አንድ ሺሕ ብር)
  • ቀበቶ ደግሞ ከብር 250 (ሁለት መቶ ሃምሳ ብር) እስከ ብር 300 (ሦስት መቶ ብር) ድረስ ለገበያ ያቀርባል።

ድርጅቱ ሥራዎችን የሚሠራው በዋናነት ከሶሻል ሚዲያ ፌስ ቡክ እና ቴሌግራምን በመጠቀም ነው። በተጨማሪም ደግሞ ትዊተር እና ቲክቶክ የመሳሰሉትን ይጠቀማል። በተጨማሪ ደግሞ ባዛሮች ላይ በመሳተፍ ምርቱን በማስተዋወቅ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። አሁን ደግሞ 2merkato.com ለጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ያዘጋጀውን የከፍታ አገልግሎት በመረዳት የከፍታ ፓኬጅ ተጠቃሚ በመሆን ሥራውን የበለጠ እያሳደገ ይገኛል።

አቶ ተመስገን እንደሚሉት የሥራው በአሁን ጊዜ ያለው የገበያ ሁኔታ ጥሩ ነው፤ ጥሩ ደንበኛ አለ። ግን አሁንም ይቀራል፤ ምክንያቱም ከሶሻል ሚዲያ ውጪ ያለው ገበያ ውስጥም ገና ስላልገቡ። “ከሶሻል ሚዲያ ውጪ ያለው ገበያ ውስጥም የመግባት ሀሳብ አለን” ብለው አክለዋል። የድርጅቱ ምርቶች ከሌሎች ምርቶች የሚለዩት ዲዛይናቸው የተለየ ነው፤ ድግምግሞሽ የላቸውም፤ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ጥራታቸው የተጠበቀ በመሆኑ ነው። ዋናው አቶ ተመስገንም ወደ ሥራው ሲገቡ በጥራት ለመሥራት ሲሉ ነው ድርጅቱን የመሠረቱት፤ እናም በቦርሳ ላይ ብቻ አተኩረው በደንብ በጥራት እየሠሩ የሚገኙት። ሌላው ደግሞ ድርጅቱ እንደየጊዜው የሚለዋወጡ ፋሽኖችን በመከተል ምርት ያመርታል። ከውጪ የሚመጡ አዳዲስ ፋሽኖች ትክክለኛ ቆዳ አይደሉም፤ ሌዘር ፕላስ የሚያመርተው ምርት ግን በንጹህ ቆዳ፣ በጥራት ፋሽኑን ተከትሎ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚመረት ነው ይላሉ የድርጅቱ መሥራች።

ምክር እና ዕቅድ

የድርጅቱ መሥራች ድርጅቱ ሲመሠርቱ ከነበረው ሁኔታ በመማር ጥልቅ የሆነ የቆዳ ዕውቀት ማዳበር ችለዋል። ለምሳሌ የቆዳ ስም፣ ዓይነት፣ ወዘተ በደንብ ዐውቀዋል፤ በተጨማሪ ደግሞ ቢዝነስ እንዴት ማስኬድ አንዳለባቸው እንዲሁም የገንዘብ ማኔጅመንት ልምድ አዳብረዋል። ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ሰዎች ቢያውቁ ጥሩ ነው ብለው ይመክራሉ።

ሌዘር ፕላስ ኢትዮጵያ በቀጣይ ሁለት ዓመታት ውስጥ በፋብሪካ ደረጃ ምርቶቹን ለማምረት፤ ቢያንስ ለሃያ ሠራተኞች የሥራ እድል ለመፍጠር እና በጥራቱ የበለጠ የታወቀ ድርጅት ለመሆን ዕቅድ አለው።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …