መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / መስከረም ክበበው የቤት እና የቢሮ እቃዎች
meslerem-furniture

መስከረም ክበበው የቤት እና የቢሮ እቃዎች

የተመሠረተው በ 2006 ዓ.ም በወ/ሮ መስከረም ክበበው ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የቤት እና የቢሮ እቃዎች የሚያመርት ድርጅት ሲሆን ይህ ድርጅት በአስራ አምስት ቀን ሶስት መቶ ወንበሮችን በጥራት የማምረት አቅም አለው። እንደ ወንበሮቹ ዲዛይን ቀኑ ሊለያይ ይችላል። ድርጅቱ በአሁን ጊዜ ለዐሥራ አራት ቋሚ እና ሁለት ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል።


ድርጅቱ ከሚያመርታቸው ምርቶች መካከል

  • ወንበሮች
  • ጠረጴዛዎች
  • ቁምሳጥን
  • የኪችን ካቢኔት
  • በር እና መስኮቶች
  • እንዲሁም አጠቃላይ የቤት እና የቢሮ እቃዎችን የሚያመርት ድርጅት ነው።

ማስተዋወቅ እና መስፋፋት

ወ/ሮ መስከረም ወደ እንጨት ሥራ የገቡት ከልጅነታቸው ጀምሮ ቤተሰባቸው ሥራውን ይሠራ ስለነበር ነው። እናም እሳቸው በፊት ከቤተሰብ ጋር አብረው በኮሚሽን ሥራውን እየሠሩ ነበር ያደጉት። ይህም ለሙያው ትልቅ አክብሮት እና ፍቅር እንዲኖራቸው አድርጓል። እሳቸውም በአይቲ ትምህርት ከተማሩ በኋላ ጓደኞቻቸው ሥራ ሲፈልጉ እሳቸው የራሳቸውን ሥራ ለመሥራት መርካቶ አመዴ ገበያ አካባቢ የቤተሰብ ቦታ ስለነበረ፤ እዛ ላይ ምን መሥራት እችላለሁ ብለው በማሰብ የእንጨት ሥራ ሙያ በልምድ በደንብ ስለሚያውቁት ወደ እንጨት ሥራ ተሰማርተዋል። ወ/ሮ መስከረም ሲጀምሩ ጥሬ እቃ(ጣውላ) በመግዛት፣ ለሥራው የሚያስፈልጋቸውን ሌሎች ቁሳቁሶች ከሰው በመዋስ ሥራቸውን ሲጨርሱ በመመለስ፣ ምርታቸውን እዛው ለገበያ በማቅረብ ነው የእንጨት ሥራውን የጀመሩት። ቀስ በቀስም አስፈላጊ መሳሪያዎችን እንደ ደረጃቸው ሊያሟሉ ችለዋል።

ድርጅቱ የሚያመርታቸውን ምርቶች የሚያቀርበው ለቀጥተኛ ተገልጋይ፣ ለነጋዴዎች፣ ለጅምላ ተረካቢዎች ሲሆን በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ላይ አገልግሎቱን ሲያደርስ ቆይቷአል። ለምሳሌ አዳማ (ናዝሬት)፣ ባህር ዳር እና ጅማ ከአዲስ አበባ ውጭ አንዲሁም በአዲስ አበባ ደግሞ ጉርድ ሾላ፣ መገናኛ ፣ ፒያሳ እና መርካቶ ለአከፋፋዮች በማቅረብ ላይ ይገኛል። የሚያመርታቸውን ምርቶችም በተመጣጣኝ ዋጋ ነው የሚያቀርበው። ለምሳሌ አንድ ደረጃውን የጠበቀ የሆቴል ወንበር በስድስት መቶ ሰማንያ ብር ሲሆን የሚያቀርበው ተመሳሳይ ይዘት ያለው ወንበር ግን ከውጭ የሚመጣ ከሆነ ከአንድ ሺህ ስምንት መቶ ብር እስከ ሶስት ሺህ ብር ነው ገበያ ላይ የሚሸጠው። እንዲሁም አልጋዎችን ከስድስት ሺህ ብር ጀምሮ ይሠራል ሌላ ቦታ ግን ትንሹ አልጋ መነሻ ዋጋ ዐሥር ሺህ ብር ነው።

ወ/ሮ መስከረም በጊዜ ሂደት ባለቤታቸውን ወደ እንጨት ሥራው እንዲገቡ ለብዙ ጊዜ ባለመታከት በመጠየቅ ባለቤታቸው የሚሠሩት የሹፍርና ሥራ በመተው አብረዋቸው እንዲሠሩ በማድረግ ወደ ሙያው በማስገባት ሥራቸው ይበልጥ ሊያድግ ችሏል። በኮቪድ ወረርሽኝ ጊዜም እሳቸው እርጉዝ ስለነበሩ ባለቤታቸው በደንብ ድርጅቱን ሲያንቀሳቅሱ እንደነበር ጠቅሰዋል።

ድርጅቱ ሥራ የሚበዛበት ጊዜ የበዓል ወቅት ሲሆን በዚህ ወቅት ደግሞ ሠራተኛ ማግኘት በጣም ከባድ እንደሆነ የድርጅቱ መሥራች ጠቅሰዋል። እንዳንድ የእንጨት ቤቶች የሠራተኞችን የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ከሌሎች ድርጅርቶች ሠራተኛ ይወስዳሉ። ከዛም የበዓል ወቅት ሲያልፍ ሥራ ይቀዘቅዛል ወይም ሌላ ቦታ ይጓዛሉ ሠራተኞቹ። ወ/ሮ መስከረም የተጠቀሙት መንገድ የድርጅቱ ሠራተኞቱ ሥራ እንዳይፈቱ እና ሥራ ሲመጣ ደግሞ ወደ ሌላ ቦታ እንዳይኮበልሉ ለማድረግ የተጠቀሙት መንገድ ለሠራተኞቹ በጣም ተፈላጊነት ያላቸውን ሥራዎችን ያለ ትዕዛዝ በመስጠት እንዲሠሩ ማድረግ ነበር። ይህ ደግሞ ጥሩ ተሞክሮ ሆኖ አግኝተውታል። ለምሳሌ አንደኛ ሠራተኛ ቦታውን ትቶ አይሄድም (ሥራ አይለቅም)።

ድርጅቱ ሥራዎችን የሚሠራው በሰው በሰው፣ ከጅምላ ነጋዴዎች እና ሆቴሎች ከሚያገኘው ትዕዛዝ እንዲሁም ጨረታ በመሳተፍ አሸንፈው ሥራውን ከሚያመጡ ሰዎች ነው። ስለዚህም ነው ድርጅቱ አቅሙ ፣ ገንዘቡ እና እውቀቱ እያለን እኛም ለምን ጨረታ አንሳተፍም በሚል  በ2merkato.com የቀረበውን የከፍታ አገልግሎት መጠቀም ጀምሯል። ጨረታዎች ላይ መሳተፍም ጀምሯል።  እንዲሁም በኢንተርኔት እና በቢዝነስ ካርድ የሚመጡ ሥራዎችን እየፈለገ ይሠራል።

የኮቪድ ተፅዕኖ

ኮድ በተከሰተበት ወቅት ድርጅቱ ከአንድ ሆቴል ጋር የወንበር ሥራ ኮንትራት ይዞ እየሠራ ስለነበር፤ ኮቪድ ድርጅቱን በጣም አልጎዳውም ግን አንደ ሀገር ያመጣው ችግር ድርጅቱም ላይ ተፅዕኖ ነበረው። ከሌሎቹ አንፃር ሲታይ ግን ጥሩ እንቅስቃሴ ላይ ነበር።

ዕቅድ እና ምክር

ወደ ፊት የማሳያ ሱቅ ለመክፈት እንዲሁም ብረት እና እንጨትን የሚያካትቱ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችል የሥራ ቦታ የማዘጋጀት እቅድ አለው።

ወደ አንጨት ሥራ የሚገባ ሰው ሥራውን ውጤቱን ማየት ፣ብቻ ሳይሆን በመሥራቱ ብቻ ደስ የሚለው ሰው መሆን መቻል አለበት፤ ይህም ውጤታማ እንዲሆን ያደርገዋል።

የድርጅቱ መሥራች ባለቤታቸውን፣ የወረዳውን ጥቃቅን እና አነስተኛ ቢሮ እንዲሁም kefta.2merkato.comን አመስግነዋል።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …