የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኤግዚብሽን እና ባዛር በአዲስ አበባ በሚገኙ ክፍለ ከተሞች ከታኅሣሥ 21፣ 2013 ዓ.ም ተከፍቷል ። ኤግዚቢሽን እና ባዛሩ እስከ የገና በዓል ዋዜማ ረቡዕ ታህሳስ 28 ድረስ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ታውቋል።
አቶ ታምሩ ደበላ፣ የአዲስ አበባ ሥራ ዕድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዞችል ልማት ቢሮ የገበያና ግብይት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ለከፍታ እንደገለጹት፣ ከታኅሣሥ 21 እስከ 28 የሚቆየው የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽን እና ባዛር ኢንተርፕራይዞች በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ የደረሰባቸውን ጉዳት በማካካስ ምርታቸውን እንዲያስተዋውቁ እና እንዲሸጡ ለማገዝ የታለመ ነው።
አቶ ታምሩ ኤግዚቢሽን እና ባዛሩ በአዲስ አበባ ዘጠኝ ክፍለ ከተሞች ከታኅሣሥ 21 አንሥቶ ክፍት መደረጉን ገልጸው፣ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ብቻ በቦታ ችግር ምክንያት እስከ አሁን ድረስ ኤግዚቢሽን እና ባዛሩን ማስጀመር እንዳልተቻለ ጨምረው ገልጸዋል። ኤግዚቢሽን እና ባዛሩ ከአገር አቀፍ የአነስተኛ እና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ኤግዚቢሽን እና ባዛር ጋር አብሮ የሚካሄድ መሆኑንም አብረው ገልፀዋል ። አገር አቀፉ የአነስተኛ እና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሬዎች ኤግዚቢሽን እና ባዛር “ሀገራዊ ጥሪ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት’’ በሚል መሪ ቃል እንደዚሁ ከታኅሣሥ 21 እስከ 28 በመላው ኢትዮጵያ የሚካሄድ ይሆናል።