ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ዋሲሁን ድጋፉ እና በጓደኛቸው በ2005 ዓ.ም. ነው። ሰንፔር ኮምፒዩተር ሶሉሽንስ የሚሠራው በቴክኖሎጂ ላይ ሲሆን ይህም ኮምፒዩተር ጥገና፣ ኔትወርኪንግ፣ እና የተለያዩ ሶፍትዌሮች እና ዌብሳይቶችን በማልማት (develop በማድረግ) ለሚፈልገው ተጠቃሚ ያቀርባል።
ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት
ድርጅቱ ለረጅም ዓመታት በኮምፒዩተር እና የቢሮ እቃዎች ጥገና እንዲሁም የኅትመት ሥራ ላይ ተሰማርቶ ቆይቷል። በዚህም በቂ ልምድ እና ተሞክሮ በማዳበሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ ዌብሳይቶች፣ ሶፍትዌሮች እና አፕሌኬሽኖች ማልማት (develop ማድረግ) ጀምሯል።
አቶ ዋሲሁን በግል ሥራ ከመሠማራታቸው በፊት የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ምሩቅ ስለነበሩ በጋራዥ ውስጥ ተቀጥረው ሲሠሩ ቆይተዋል። ይሁን እና በጋራዥ ሥራ ውስጥ እንዳሉ አዲስ እና ዘመናዊ ኮምፒዩተራይዝድ የሆኑ መኪኖች ገበያ ላይ መዋል ሲጀምሩ እሳቸውም ይህን ትምህርት ብጀምር ከሥራዬ ጋር አብሮ ይሄዳል በማለት የኮምፒዩተር ሳይንስ ትምህርት ቀን ቀን እየሠሩ ማታ ማታ ተማሩ። ሆኖም ቴክኖሎጂው እንዳሰቡት ወደ ሀገራችን ማምጣት እና መሥራት ቀላል አልነበረም፤ ብዙ ችግሮች ነበሩ። ሆኖም ግን ትምህርቱን ስለወደዱት እና አንዳንድ ሥራዎችን በተጓዳኝ በመሥራት ትንሽ ጊዜ ካሳለፉ በኋላ በሙሉ ወደ ኮምፒዩተር ሥራ ገብተዋል።
ድርጅቱ አሁን በአዲስ አበባ ውስጥ አሉ ከሚባሉ የኮምፒዩተር ጥገና እና ቴክኖሎጂ ሥራ ከሚሠሩ ድርጅቶች የተሻለ አቅም እና ተሞክሮ አለው። የድርጅቱ መሥራቾች ድርጅቱን ሲመሠርቱ ሁለት በመሆን እና በዐሥራ አምስት ሺህ ብር ካፒታል ነበር። አሁን ለሦስት ሴቶች እና ሦስት ወንዶች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ከዚህ በተጨማሪም በተጫረታቸው እና ባሸነፋቸው ጨረታዎች መጠን አሁን ለአራት ሠራተኞች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል።
ድርጅቱ ሥራዎችን የሚሠራው ጨረታ እና ጨረታ በመጫረት ብቻ ነው። ይህንንም 2merkato.com ለጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ያዘጋጀውን የከፍታ አገልግሎት ፓኬጅ በመጠቀም ጨረታዎችን ይከተታተል ከዛም ለዓመት ዐሥር ጨረታዎችን ከተጫረተ ስድስቱን ያሸንፋል፤ ያሸነፈውን ጨረታ በጥራት ሠርቶ ያስረክባል። በዚህም ብዙ ጨረታዎችን ማሸነፍ ችሏል። ከጨረታው ውጪ ምንም አይነት የማስታወቂያ ወይም ሌላ የሥራ ማግኛ መንገድ አይጠቀምም። አንዳንዴ ጨረታ ተሸንፈው ራሱ አሸናፊው የሆነ ችግር ሲኖርበት እነሱ በነበራቸው የአፈጻፀም ብቃት ሥራዎችን የሠሩባቸው አጋጣሚዎች አልፈዋል።
ድርጅቱ ጨረታ አሸንፎ በሚገባ ሥራውን ሠርቶ ካስረከባቸው መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ጥቂቶቹ
- ኮልፌ ክፍለ ከተማ ሁሉም ወረዳዎች
- አራዳ ክፍለ ከተማ ግማሽ ወረዳዎች
- የካ ክፍለ ከተማ ግማሽ ወረዳዎች
- ጉለሌ ክፍለ ከተማ ግማሽ ወረዳዎች
- በፊደራል ደረጃ ደግሞ ቤተ መንግሥት፣ ጠቅላይ ፍድር ቤት እና ፌደራል ማረሚያ ቤት ጨረታ አሸንፎ ከሠራባቸው መካከል ተጠቃሾች ናቸው።
እንዲሁም
- የካ፣ አራዳ እና ኮልፌ ክፍለ ከተሞች ለረጅም አመታት ሠርቷል።
- በአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ አዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ፣ አዲስ አበባ ጤና ቢሮ እና አዲስ አበባ ስፖርት ቢሮ ረዘም ላሉ ዓመታት ሠርቷል።
የኮቪድ ተፅዕኖ
የኮቪድ ተፅዕኖ በጣም ከባድ ነበር፤ ሁለት ዓመት ምንም ሥራ አልነበረም። በጣም ኪሣራ ነበር። ለዚህም ከዳሽን ባንክ ብድር ተበድረው የነበረ ቢሆንም ይህንንም ለመክፈል የነበራቸውን አንድ መኪና መኪና በመሸጥ ነው የኮቪድን ጊዜ ያለፉት። ይህም የነበራቸውን ካፒታል ከአንድ ሚሊዮን አሁን የተሠራቸው ሥራዎች ተደምረው ወደ አምስት መቶ ሺህ አውርዶታል።
ምክር እና እቅድ
ድርጅቱ ወደ ፊት ወደ ሥራ ለመግባት ጥናት ሠርቶ ጨርሶ ያቀደው እቅድ የሰርኪዩት ቦርድ ፋብሪካ ለመክፈት ነው። ቦርድ ዋጋው በጣም ውድ ነው፤ እንዳንድ ጊዜ ከእቃው(ከኤሌክትሮኒክሱ) ሊበልጥ ይችላል። የድርጅቱ መሥራቾች ቻይና እና ዱባይ ሄደው በነበር ጊዜ እዛ የሰርኪዩትቦርድ አሠራር እንዴት እንደሆነ በመረዳት እና ልምድ በመቅሰም ያንን በሃገር ቤት ለመሥራት እና ፋብሪካ ለመክፈት ሃሳብ ይዘው መጡ። የጥናት እቃዎችንም አስመጥተዋል፤ ይህንን ሥራ በትንሹ ጀምረዋል።
አሁን ደግሞ አንድ ኢኮሜርስት የሚሠራ ድረ ገጽ ሰርተው ጨረሰዋል፤ ዶሜን ገዝተዋል፤ ሆስቲንግ ደግሞ ለመግዛት ከኢቲዮ ቴሌኮም ጋር እየተነጋገሩ ይገኛሉ። ይህን ደግሞ በከፍታ ፓኬጅ የማስታወቂያ አገልግሎት ለመጠቀም ዕቅድ አላቸው።
“አዲስ ወደዚህ ዘርፍ ለሚገቡ ሰዎች በጣም የሚያስፈልገው ልምድ ነው። ቀጥሎ ደግሞ ትምህርት ያስፈልጋል። ስለዚህ በትምህርት የተደገፈ ልምድ በጣም አስፈላጊ ነው። ገንዘብ ይህን ያህል አስፈላጊ አይደለም። ድርጅቱ ከመስከረም ሲጀምር በዜሮ ነው ነገር ግን ያለው ተግባቦት እና ልምድ በጣም የዳበረ ስለሆነ በዚህ መልኩ ነው ሥራችንን እያከናወንን የምንገኘው” ብለዋል አቶ ዋሲሁን። አቶ ዋሲሁን ይበልጥ ብዙ ነገሮችን ለመሥራት የሦስተኛ ዲግሪ (PHD) ትምህርታቸውን በዚሁ ዘርፍ እየሠሩ ይገኛሉ።
የድርጅቱን አገልግሎት መጠቀም የሚፈልጉ የድርጅቱን ስልክ በዚህ ሊንክ በመግባት ዓይተው መደወል ይችላሉ።