ሶኒያ ኬ ላንዠሪ (Lingerie) የሴቶች የውስጥ አልባሳት ልብስ ስፌት የተመሠረተው በ ወ/ሮ ሶኒያ አሕመድ 2005 ዓ.ም ሲሆን በአንድ መሥራች አባል እና በአንድ የልብስ ስፌት ማሽን ነበር፡፡ወ/ሮ ሶኒያ የራሳቸውን ቢዝነስ የጀመሩት ራስን መቻል (self-sufficient መሆን) ስለሚፈልጉ ነው። ፈረንሳይ ሀገር በሊትሬቸር የተመረቁት ወ/ሮ ሶኒያ ቢዝነሱን ከመጀመራቸው በፊት በፈረንሳይ ቋንቋ ለሃያ ዓመታት በጅቡቲ እና ለስድስት ዓመታት በ ኢትዮጵያ በትምህርት ቤት አስተማሪነት አገልግለዋል።
ምሥረታና ዕድገት
ወ/ሮ ሶኒያ ወደ ላንዠሪ (Lingerie) የሴቶች የውስጥ አልባሳት ሊገቡ የቻሉት ሙያው በልጅነታችው በጣም ይስባቸው ስለነበር ነው። ለምሳሌ የዳንቴል አሰራር፣ ዳንቴሉ ላይ ላይ ያሉት ዲዛይኖች እንዲሁም የሴቶች የውስጥ አልባሳት መስራት ከልጅነታቸው ጀምሮ ያደጉበት ነው። ልጅ እያሉ ፈረንሳይ ሀገር ጨርቆችን በማዘጋጀት ከጎረቤት ወደ ጎረቤት በመሄድ እየሰፉ ማደጋቸው ወደ ፋሽን ዲዛይን እንዲገቡ ትልቅ አስተዋጽዖ አለው።
ሶኒያ ኬ ድርጅቱን ጅቡቲ ለመክፈት ሀሳቡ የነበረው ቢሆንም ነገር ግን በነበሩ ብዙ ችግሮች ለምሳሌ በቂ የሆነ የኤሌክትሪክ አቅርቦት አለመኖር እና የኑሮ ውድነት ምክንያት የጅቡቲውን ሀሳብ እንዲተዉ አድርጓቸዋል። ወደ ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜ ያለውን ገበያ ሁኔታ ሲመለከቱ ምንም አይነት የሴቶች አልባሳት ሱቅ አልነበረም። አንድ ሱቅ ብቻቦሌ ሩዋንዳ አካባቢ ነበር፤ በጣም የታወቀ ነው ዕቃ ከጣልያን ነበር የሚያስመጣው። የሚመጣው ዕቃም በአስራ አምስት ቀን ያልቃል ያውም ያለ ምርጫ ቀጥሎም ለሁለት ወር ዕቃ የለም ተብሎ ይዘጋል። በዚህ ምክንያት አዲስ አበባ ውስጥ ደግሞ ብዙ ሰው ነው ያለው በዚህ ሥራ ብጀምር ያዋጣል ብለው ሶኒያ ኬ ድርጅት ተመሠረተ። ድርጅቱ ሲጀምር ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ነበሩ ምክንያቱም ዕቃው እንዳለ ከውጭ ነው የሚመጣው ስለዚህ ይህ ደግሞ ጊዜ ይወስዳል። ቀጥሎ ደግሞ ወ/ሮ ሶኒያ ያሰቡት የመሸጫ ዋጋ ከገበያው ጋር ተመጣጣኝ አልነበረም ድርጅቱ ምርት ለመሸጥ ያሰበው ከመቶ እስከ መቶ ሀምሳ ብር ገደማ ሲሆን ገበያው ላይ የነበረው ዋጋ ግን አርባ ብር ነበር። ስለዚህ ሥራው በጣም አስቸጋሪ ስለነበር ሥራውን አቁመው ለሁለት ዓመት ወደ ፈረንሳይ ተመልሰው ሄደዋል።
ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት
ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የመጡት ወ/ሮ ሶኒያ ነገሮች በትንሹም ቢሆን ተለውጠዋል በሚል ሀሳብ 2008 ዓ.ም ላይ እንደገና ሊጀምሩ ችለዋል። ሥራው ከበፊቱ ይሻላል ነገር ግን ገና ነው በተለይ ሀገር ውስጥ ያለው ገበያ በጣም ይቀረዋል። ሶኒያ ኬ ድርጅት በቀን አንድ ሺህ ፓንት እና ሁለት ደርዘን ጡት ማስያዣ ያወጣል የጡት ማስያዣው ያነሰው ሲሰራ በጣም ጥንቃቄ ይፈልጋል ጥራቱ የጠበቀ ለመሆን ብዙ የሚገቡበት ጥሬ እቃዎች ስላሉ እና በፋሽን ስለሚሠራ ሁለት ወይም ሶስት ደርዘን ማምረት ይቻላል።
ሶኒያ ኬ ላንዠሪ(Lingerie) የሚያመርታቸው አገልግሎቶች ለሴቶች የሚሆኑ ሴቶችን የሚመለከቱ የውስጥ ልብስ አልባሳት ናቸው። ጥራታቸውን የጠበቁ የተለያዩ የሴቶች ጡት መያዣ እና የተለያየ ይዘት ያላቸው የሴቶች ፓንት እንዲሁም የውስጥ አልባሳት ለአዘቦት ቀን የሚሆኑ፣ ለተመረጡ ጊዜዎች ወይም ዝግጅቶች የሚመቹ በጥጥ፣ በዳንቴል፣ በፖሊስተር የዘመኑን ፋሽን በጠበቀ መልኩ የሚያመርት ድርጅት ነው። ሲጀመር በአንድ መሥራች አባል እና በአንድ ማሽን የተመሠረተው ድርጅት በአሁኑ ወቅት አራት ሠራተኞች እና ስድስት ማሽኖች አሉት። በኮቪድ ምክንያት ስምንት ሠራተኞች ተቀንሰዋል።
ሶኒያ ኬ ላንጀሪ የሚያመርታቸው ምርቶች
- የሴቶች የውስጥ ሱሪ (panties)
- የጡት መያዣ
- የሴቶች ፒጃማ
- የሴቶች ቶፕ
- የሴቶች ቦክሰር
- የሴቶች ቦይ ሾርት
- የሴቶች ኢታሊያን ፓንቲስ
- የሴቶች የቢች ዳር አልባሳት
- ቶንጋ
- የሴቶች ሱሪ
- በጣም የተራቀቁ ናይቲስ
- በጣም ዘመናዊ የሆነ የሴቶች ጋዋን
- ቢች ዌር እና ስዊም ዌር
ወ/ሮ ሶኒያ ልብስ ስፌት መሠረታዊ ክህሎቶች እራሳቸውን በራሳቸው ነው ያስተማሩት። በሥራው ዘርፍ በዚያ ዘመን አገር ውስጥ ምንም ዓይነት ድጋፍም ሆነ እርዳታ አልነበረም።በስራ ሂደት ላይ ተግዳሮቶች እና ጥረት የሚጠይቁ ጉዳዮች አሉ። ሠራተኛ ማሰልጠኑ፣ ግብዓት መግዛቱ፣ በቂ ዕቃ አቅርቦት አለመኖሩ፣ ጥራት መከተታተሉ እና የሀገር ውስጥ የገበያ እጥረት ከነበሩት መሰናክሎች ጥቂቶቹ ናቸው። ከሁሉም አስቸጋሪው ደግሞ ሥራ ለመሥራት የሚያስፈልጉ ጥሬ እቃዎች በሙሉ ከውጭ መምጣታቸው ነው። ይህ ማለት አንድ እቃ ታዞ እስከሚመጣ ድረስ ከስድስት እስከ ዐሥር ወር ይፈጃል ይህ ሁሉ ሥራውን በጣም ከባድ ያደርገዋል። ይህንን ችግር ለመፍታት በቂ ስቶክ መያዝ እና ተገቢ ዝግጅት ሊደረግ እንደሚገባ ልምዳቸውን አካፍለዋል።
የኮሮና ወረርኝኝ ተፅዕኖ
ኮቪድ በሶኒያ ኬ ቢዝነስ ላይ ጥሩም መጥፎም ተፅዕኖ ነበረው። ኮቪድ ኢንትዮጵያ እንደ ገባ ከአምስት እስከ ስድስት ወር ድረስ የማስክ ሥራ በጣም ጨምሮ ነበር። በማስክ ሥራም ለመቀጠል አስበው ነበር፤ ነገር ግን ከኢንዱስትሪ የሚመጡ ማስኮች ገበያውን ሲቆጣጠሩት ወደ በፊት ሥራቸው ተመልሰዋል። ነገር ግን ምንም አይነት እንቅስቃሴ ባለመኖሩ የታዘዘ እቃ በጣም ተጓቶ ስለሚደርስ ሥራ በጣም ቀዝቅዞ ነበር።
ምክር እና እቅድ
ሶኒያ ኬ ሥራ የሚያገኘው በኢንተርኔት ሊንክዲን (LinkedIn) በመጠቀም ነው። አንድ ደንበኛ ከኢንግሊዝ አገር አራት ሚሊየን ትእዛዝ ፈልጎ ነበር ግን እንኳን አራት ሚሊየን፤ መቶ ሺህ ራሱ ከባድ ስለሆነ ሳይሠሩት ቀርተዋል። ከዚህ በተጨማሪ የሚያስተዋውቁት በራሳቸው ዌብሳይት ቀጥሎ ደግሞ በሰው በሰው (word of mouth) ነው ሥራ የሚሰራው።
አዲስ ወደ ሙያው ለሚገቡ (አሁን ባለው ሁኔታ ባይገቡ ይመረጣል) ፈታኝ ሁኔታዎች አሉ። ከገቡ ግን በጣም ታጋሽ እና ጠንካራ ሊሆኑ ይገባል ሥራው በጣም አድካሚ እና ከባድ ስለሆነ።
ሶኒያ ኬ ወደፊት በኢትዮጵያ የልዩ ልዩ ሙያና አርአያነት ያለው አምባሳደር እንደሚባለው ለሴቶችም የታወቀ ድርጅትና አምባሳደር ለመሆን እቅድ አላቸው።