መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ታሪክ ዲተርጀንት

ታሪክ ዲተርጀንት

ድርጅቱ የተመሠረተው በ2012 ዓ.ም. በወ/ሮ የምሥራች የምሩ እና አራት መሥራች አባላት ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ ለንጽህና መጠበቂያ የሚያገለግሉ ፈሳሽ ሳሙናዎችን በጥራት እና በተመጣጣኝ ዋጋ አምርቶ ለገበያ ያቀርባል።

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች

  • የልብስ ፈሳሽ ሳሙና
  • የእቃ ማጠቢያ ፈሳሽ ሳሙና
  • የእጅ መታጠቢያ ፈሳሽ ሳሙና እና
  • በረኪናዎች

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

ወ/ሮ የምሥራች ይህን ድርጅት ከመመሥረታቸው በፊት በሆቴል እና ቱሪዝም ሥራ መስክ ተሰማርተው ሲሠሩ ነበር፤ ይሁና እና በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት በጣም ሥራ ስለቀዘቀዘ ምን ብንሠራ ያዋጣናል በአሁን ሰዓት ምን ተፈላጊ ነው የሚለውን በማጥናት ነው ወደ ዲተርጀንት ሥራ ዘርፍ የተሰማሩት። ወደ ዘርፉ ከመሰማራታቸው በፊት አስፈላጊውን ስልጠና ወስደው ሥራውን እንደጀመሩ የድርጅቱች መሥራች ገልጸዋል።

ድርጅቱ በአሁን ጊዜ በቀን ቢያንስ ዐሥር ሺህ ሊትር ፈሳሽ ሳሙና የማምረት አቅም ላይ ይገኛል። አሁን ላይ ያለው የጥሬ እቃ (ኪሜካል) አለመገኘት የድርጅቱ ምርት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል። ይህ ቢስተካከል የድርጅቱ የማምረት አቅም በደንብ እንደሚጨምር ወ/ሮ የምሥራች ገልጸዋል።

ይህ ድርጅት ፈሳሽ የልብስ ሳሙና በሁለት ሊትር እና በአምስት ሊትር እንዲሁም በረኪና በስምንት መቶ ሚሊ ሊትር እና በአምስት ሊትር ለገበያ እያመረተ ያቀርባል።

የምርቶቹ ዋጋ በከፊል

  • ሁለት ሊትር የልብስ ማጠቢያ ፈሳሽ ሳሙና – አንድ መቶ አርባ ብር
  • አምስት ሊትር ፈሳሽ የልብስ ማጠቢያ ሳሙና – ሁለት መቶ አርባ ብር
  • በረኪና አምስት ሊትር – አንድ መቶ ሰባ ብር
  • በረኪና ስምንት መቶ ሚሊ ሊትር – በሃያ ስምንት ብር ለገበያ ያቀርባል

እነኝህን ምርቶች የሚፈልጉ ተጠቃሚዎች በስልክ ደውለው ቢያዙ፣ ድርጅቱ ያሉበት ድረስ በመምጣት ያስረክባል።

ታሪክ ዲተርጀንት የሚያመርታቸውን ምርቶች ለሆቴሎች እና ለሱፐርማርኬቶች እያቀረበ ይገኛል። እንዲሁም ባዛር ሲኖር ባዛር ላይ በመሳተፍ ምርቱን ለተጠቃሚዎች በቀጥታ ያቀርባል።

ወ/ሮ የምሥራች ድርጅቱን ለማቀሳቀስ እና ለመምራት ልምድ እና መሠረታዊ ክህሎቶች ያዳበሩት፦ አንደኛ ከበፊቱ ሥራቸው ነው። የበፊቱ ሥራ ከአሁኑ የሥራ ዘርፍ ጋር ቢለያይም ብዙ ልምዶች ተምረውበታል፤ ለምሳሌ ሠራተኞችን ማስተዳደር ብሎም ደንበኛ አያያዝ እና ሌሎችም። ሁለተኛው ደግሞ በወረዳ እና ክፍለ ከተማ በየጊዜው የሚሰጡ ሥልጠናዎችን በመውሰድ እና የልምድ ልውውጥ መርሓ ግብሮችን በሚገባ በመሳተፍ ከዚያም እነዚህን ሥልጠናዎችና ትምህርቶች በመተግበር ነው።

ታሪክ ዲተርጀንት ሥራዎችን የሚሠራው ሱቆች፣ ሆቴሎች እና ሱፕር ማርኬቶች ጋር በመሄድ እና እነሱን በማናገር ነው። በዚህ መንገድ ሱቆች ላይ ትንሽ ችግር አለ ምርቱ አዲስ ነው፣ አናውቀውም ሰው ላይገዛው ይችላል እያሉ አስቸግረዋል። ድርጅቱ አሁን 2merkato.com ለጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ያዘጋጀውን የከፍታ አገልግሎት የጨረታ እና የማስታወቂያ አገልግሎት እየተጠቀመ ይገኛል። ድርጅቱ የተጨማሪ ዕሴት ታክስ (ቫት) ተመዝጋቢ እንደመሆኑ መጠን ጨረታዎችን በደንብ እየተከታተለ ይገኛል።

ድርጅቱ ላይ ካገጠሙት ችግሮች አንዱ የጥሬ እቃ አቅርቦ ዋጋ መናር ነው። አንድ በርሜል ኬሚካል ለመግዛት ከዘጠና ሺህ እስከ መቶ ሺህ ብር ድረስ ነው። ይህ በጣም አስቸጋሪ ነው፤ በተለይ ደግሞ ድርጅቱ በሚያቀርበው ጥራት እና ዋጋ። ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች ችግሮች ሲከሰቱ ወ/ሮ የምሥራች ከቤተሰባቸው እና በሥራው ላይ ካሉ ሰዎች ጋር በመሆን በመመካከር ችግሮችን እየፈቱ እንደመጡ ተናገረዋል።

ድርጅቱ ሲመሠረት በአሥራ አምስት ሺህ ብር ካፒታል ሲሆን አሁን ሦስት መቶ ሺህ ብር ካፒታል ኖሮት ለሦስት ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል። እንዲሁም የማምረት አቅሙ በድርጅቱ ምሥረታ ወቅት የሚመረተው ምርት በቀን ከሃምሳ እስከ መቶ ሊትር ፈሳሽ ሳሙና ሲሆን አሁን ግን የምርት መጠኑ በቀን አስር ሺህ ሊትር ደርሷል። በተጨማሪም የሌመን እና የስትሮበሪ መዓዛ  ያላቸውን ምርቶችን እያመረተ ይገኛል።

የኮቪድ ተፅዕኖ

ኮቪድ በድርጅቱ ላይ ያስከተለው ችግር ሥራውን መሥራት በሚገባው ልክ መሥራት አለመቻል ነው ይህም ማለት የነበሩ ሠራተኞች ለቀው ወደ ክፍለ ሀገር ስለሄዱ የሰው ሃይል በመቀነሱ የሚፈገውን ያህል ምርት አምርቶ ተጠቃሚ መሆን አልተቻለም።

ምክር እና እቅድ

አንድ ሰው ሥራ ሲጀምር ሥራውን ማክበር አለበት፤ ምንም ነገር ሲያከብሩት ነው የሚያከብረው። በመቀጠል ዛሬ መጠናቀቅ ያለበትን ሥራ ዛሬ ማጠናቀቅ በጣም አስፈላጊ ልማድ መሆን ያለባቸው ነገሮች ናቸው ሲሉ የድርጅቱ መሥራች መክረዋል።

ወደ ዲተርጀንት የሥራ ዘርፍ ለሚገቡ ሰዎች ዕውቀት በጣም አስፈላጊ ነው። ቢያንስ ኮርስ ወስደው መግባት አለባቸው። ምክንያቱም ምርቱ የሚመረትበት ኬሚካል በጣም ጥንቃቄ ስለሚፈልግ፤ ያለጥንቃቄ ከተሠራ በጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ስለሚያስከትል ዕውቀት ለሥራው በጣም አስፈላጊ ነው። በተጨማሪ አዲስ ምርት ለመጀመር ወይም የጥራት መጠን ለመጨመር ዕውቀት በጣም አስፈላጊ ነው ሲሉ የድርጅቱ መሥራች ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

“ድርጅቱ የሚያቀርባቸው ምርቶች በጥራታቸው አሁን አሉ ከሚባሉ ምርቶች አኩል ጥራት ያላቸው ናቸው። አሁን ካሉት ትልቅ ስም ካላቸው ፈሳሽ ሳሙናዎች በጥራት አንድ ዓይነት ነው። ይሁና እና እነዛ ድርጅቶች ስለታወቁ ነው እንጂ ዋጋቸው በጣም ውድ የሆነው። የኛ ድርጅት ምርት ደረጃውን የጠበቀ ስለሆነ ማንኛውም ተጠቃሚ ምርቱን ዓይቶ ራሱ መመስከር ይችላል” ሲሉ የድርጅቱ መሥራች አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ወደ ፊት ታሪክ ዲተርጀነት በሰፊው ወደ ገበያ ለመግባት እና ወደ ክልል ከተሞች ለመስፋፋት፤ እንዲሁም ተፈላጊነት ያላቸውን ምርቶች በማጥናት አስፈላጊውን ማሽን አስገብቶ ሥራወን ለማሳደግ እቅድ አለው።

የድርጅቱን አገልግሎት ለማግኘት በዚህ ስልክ ቁጥር ይደውሉ፦ +251 901  18 33 90

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …