መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ተዋበ እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ተዋበ እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ተዋበ ምኔነህ በ2004 ዓ.ም. የግል ኢንተርፕራይዝ ሆኖ ነው። ይህ ድርጅት አጠቃላይ የእንጨት እና የብረታ ብረት ሥራዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ይሠራል።

ከሚያመርታቸው ምርቶች ውስጥ ጥቂቶቹ

  • የውስጥ እና የውጭ በሮች
  • ኪችን ካቢኔት
  • አልጋ
  • ወንበር እና ጠረጴዛ
  • ቁምሳጥን
  • የደረጃ እጀታ በብረት እና በእንጨት
  • የውስጥ እና የውጭ በሮች
  • አጠቃላይ የፎቅ በር እና መስኮት ሥራ
  • አጠቃላይ የእንጨት እና የብረት ሥራዎች
  • በተጨማሪ ደግሞ ከተለመደው ወጣ ያሉ ሥራዎችን ለምሳሌ አሁን እየሠራ የሚገኘው ሜዠሪንግ ስቲክ ተጠቃሽ ነው

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

አቶ ተዋበ ይህን ድርጅት ከመመሥረታቸው በፊት በረዳትነት በመቀጠር ከዛም ሙያውን በማዳበር እና በመማር በሙያው ውስጥ በማደግ በቂ እውቀት በመያዝ ለስምንት ዓመታት ሠርተዋል። ይህም የሥራ ልምድ የግል ሥራቸውን ሲጀምሩ ነገሮችን እንዳቀለለላቸው ተናግረዋል። ተዋበ እንጨት እና ብረታ ብረት ድርጅት ሲመሠረት በአሥራ ሰባት ሺህ ብር ካፒታል እና በአንድ ሠራተኛ ነበር፤ አሁን የድርጅቱ ሠራተኞች ቁጥር ወደ ስምንት ያደገ ሲሆን የካፒታል መጠኑም ሁለት ሚሊዮን ብር ደርሷል።

አቶ ተዋበ እዚህ ስኬት ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት ግን በጣም ታጋሽ እና ታታሪ በመሆን ነው። እሳቸው ሲጀምሩ የነበሩ ብዙ አስቸጋሪ ነገሮች ነበሩ። ዋናው እና ዓበይቱ ግን ደንበኛ ማግኘት እና የሥራ ቦታውን እንዲለመድ ማድረግ በጣም ከባድ እንደነበረ ተናግረዋል። ይህንንም ችግር ለመፍታት አንዳንዴ ያመረቱትን ምርት በኪሣራ ለነጋዴዎች እስከ መሸጥ ድረስ ደርሰው ነበር። ይህም ገቢ ለቤት ኪራይ እና ለሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ማሟያ እና ሥራዎችን ለማከናወን እንዲውል በማድረግ ተጠቅመውበታል። ሌላው መፍትኂ ደግሞ ምንም አይነት ሥራ ቢመጣ አልሠራውም ተብሎ የሚመለስ ሥራ አልነበረም፤ አሁንም የለም። ምናልባት ሥራው ትልቅ ከሆነ የሥራው ቀጠሮ ረዘም ይደረጋል እንጂ የሚመለስ ሥራ በፍጹም የለም። እነዚህን መንገዶች በመጠቀም ነው ድርጅቱ ውጤታማ ሊሆን የቻለው።

 

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች ዋጋ

  • ኖርማል 80 ሴንቲሜትር (80 cm)  በር እንደ ዲዛይኑ እና መጠኑ ቢለያይም አንድ በር ከነቁልፉ ገጥሞ ለማስረከብ በአሥራ ሁለት ሺህ ብር
  • ኪችን ካቢኔት በአንድ ካሬ ሰባት ሺህ ብር
  • ቁም ሳጥን በአንድ ካሬ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ብር እየሠራ ይገኛል።

ድርጅቱ የሚቀበላቸውን ሥራዎች እንደ ብዛታቸው እና መጠናቸው ቁምሳጥን እና ኪችን ካቢኔት ከሁለት ቀን እስከ ሳምንት በሚፈጅ ጊዜ ያደርሳል። በዛ ያለ ሥራ ከሆነ ደግሞ ለምሳሌ አምስት ሺህ በሮችን ሠርቶ ገጥሞ ለማስረከብ እስከ አንድ ዓመት ጊዜ ይፈጅበታል።

ድርጅቱ ሥራዎችን የሚሠራው 2merkato.com ለጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ያዘጋጀውን የከፍታ አገልግሎት በመጠቀም ጨረታዎች ላይ በመሳተፍ ነው፣ በሰው በሰው እና አፍሮ ታይ የሚባል የመሸጫ እና መገበያያ መተግበሪያ በመጠቀም ነው። ወጣ ያሉ በሃገራችን ያልተለመዱ ሥራዎችን ከኢንተርኔት በማየት እና እነዛን ሥራዎች ከእኛ ሀገር ጋር በሚጣጣም መልኩ በመሥራት መተግበሪያው ላይ በመለጠፍ ብዙ ሥራዎች አግኝተዋል። እንዲሁም ከዚህ በፊት በሠሯቸው ሥራዎች የሚመጡ ሥራዎች ይሠራሉ። የ2merkato.com ጨረታ በመጠቀምም ሁለት ጨረታ አሸንፈዋል አንድ ከኤንጂኦዎች (NGO’s) ጋር ሌላው ደግሞ የጤና ጣቢያ ጨረታ አሸንፈዋል። አሁን ደግሞ አንድ ሰፊ ጨረታ በሂደት ላይ እንደሆነ አክለዋል።

አቶ ተዋበ ለቢዝነስ የሚያስፈልጉ መሠረታዊ እውቅት እና ክህሎት ያካበቱት በዋናነት በልምድ ነው። እሳቸው ሠራተኛ በነበሩበት ወቅት ያሳዛናቸውን ነገር ለሠራተኞቻቸው አያደርጉም፤ ይህ በጣም ወሳኝ ነው ሠራተኛ በታታሪነት እንዲሠራ ያደርጋል። ሁለተኛ ደግሞ ተካፍሎ መብላት አስፈላጊ ነው እሳቸውም እንዲሁም ያደርጋሉ። ሌላው ደግሞ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ስለሚገናኙ ከነሱ ጋር በመነጋገር ልምድ በመለዋወጥ ጥሩ የቢዝነስ ክህሎት አዳብረዋል።

የኮቪድ ተፅዕኖ

በኮቪድ ወቅት የድርጅቱ ሥራ ቀዝቅዞ ነበር። የመጡ ሥራዎች እናኳን ተጠናቀው ሲያልቁ ደንበኞች ጋር ለመግጠም በሚሄዱበት ጊዜ አለማስገባት፣ እዛ ይቀመጥ ብሎ የመሥሪያ ቦታ ማጣበብ እንዲሁም ዋጋ ካለቀ በኋላ ይቆይልን በማለት ሥራዎችን አጓቶ ነበር። ቢሆንም ድርጅቱ ከሰው ጋር ንክኪ የሌላቸው የኮንትራት ሥራዎችን ፈልጎ አግኝቶ በመሥራት አሳልፏል።

ምክር እና እቅድ

የግል ሥራ ትልቅ ኃላፊነት አለው፤ እንቅልፍ ይነሳል። አንድ ቢዝነስ እንዲያድግ ከሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮች መካከል ሠራተኛን በፍቅር መያዝ፣ ደንበኛን በአክብሮት መያዝ እና ሥራን በተባለው ጊዜ ማድረስ ናቸው። አድቫንስ ክፍያ ተቀብሎ የሌላ ሰው ሥራ አለመሥራት፣ አድቫንስ ተቀብሎ የተቀበሉትን ደንበኛ ሥራ ቀጥታ መሥራት አስፈላጊ እንደሆነ ይመክራሉ።

ወደ ዘርፉ ለሚሠማሩ አዲስ ጀማሪዎች አውቀት በጣም አስፈላጊ ነው። “ገንዘብ ኖሮ ተቀጣሪው ብቻ ባለሙያ ከሆነ እሱ ባለው ነው ሥራው የሚሄደው፤ ደንበኛ ማሳመን አይችልም። ሥራው ላይ ችግር ሲፈጠር ይሄ የሆነው እንዲህ ስለሆነ ነው በዚህ አስተካክለዋለሁ ማለት አይችልም። ሁሌ በሠራተኛ ላይ ጥገኛ ይሆናል። ስለዚህ ሙያውን አውቆ መግባት ተገቢ ነው። ገንዘብ ስላለ ብቻ መግባት አይመከርም። ወይም ደግሞ እውቀት እና ሙያው ካለው ተማምኖ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ተስማምተው መሥራት ይቻላል። ይህ ጥሩ መንገድ ነው” ሲሉ ምክራቸውን ሰጥተዋል።

ድርጅቱ ወደ ፊት የጨረታ አገልግሎቱን በደንብ ለመጠቀም የጨረታ ማስከበሪያ ሲፒኦ እየተባለ ስለተቸገሩ አሁን ባንኮች ጋር አካውንት ከፍተው የባንክ የድጋፍ ደብዳቤ በማጻፍ ጨረታ ላይ አሁን ከሚሳተፉት በላይ ለመሳተፍ አቅድ አለው።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …