መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ዓለም ልብስ ስፌት
alem-garment

ዓለም ልብስ ስፌት

ድርጅቱ የተመሠረተው በወይዘሪት ዓለም ዩሱፍ 2012 ዓ.ም. የግል ኢንተርፕራይዝ ሆኖ ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የልብስ ስፌት ሥራዎችን የሚሠራ ሲሆን በዋናነት ደግሞ የጅምላ ሥራዎችን ይሠራል።

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች

alem-garment-shirt

  • የህጻናት ጃኬት እና አላባሹ
  • የስፖርት ትጥቅ ማልያዎች
  • ቲሸርቶች
  • ዩኒፎርሞች
  • የጥበቃ ልብሶች
  • የተለያየ አገልግሎት የሚውሉ ጋዋኖች
  • የቱታ ሱሪዎች ሲሆኑ እንዲሁም አጠቃላይ ስፌት ነክ የሆኑ ሥራዎችን ይሠራል።

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

ወ/ት ዓለም ወደ ልብስ ስፌት ሥራ የገቡት እህታቸው የልብስ ሥራ ይሠሩ ነበር፤ ያንንም እያዩ ስላደጉ ወደ ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ ሲገቡ ከነበሩት አማራጮች የልብስ ስፌትን ትምህርት መረጡ። ሦስት አመት ከተማሩ በኋላ ነው ይህን ድርጅት ሊመሠርቱ የቻሉት። ሥራውን ስለሚወዱት እና ደስ ስለሚላቸው በዚህ ሙያ ሠርተው ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ብሎም ሀገር ለመለወጥ አስበው ነው የገቡት በዚህም ጥሩ ውጤት እንዳገኙበት ገልጸዋል።

ድርጅቱ የሚያመርታቸውን ቲሸርቶች ሦስቱን በመቶ ሃምሳ ብር የሚያቀርብ ሲሆን፣ አንድ ብቻ የሚፈልግ ደግሞ በሰባ ብር ወንጌላዊት ሕንጻ አራተኛ ፎቅ በመምጣት መግዛት ይችላል። ከዚህም ጋር አያይዞ በቲሸርቱ ላይ ኅትመት ለሚፈልጉ በተያያዥነት ይሠራል።Alem-Garment-TShirt

ዓለም ልብስ ስፌት ሲመሠረት በአምስት ሺህ ብር ካፒታል እና ሦስት ማሽኖችን በብድር በመግዛት ነበር። በአሁን ጊዜ ድርጅቱ የካፒታል አቅሙን ወደ መቶ ሃምሳ ሺህ ብር ያሳደገ ሲሆን ለአራት ቋሚ እና ስድስት ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል። የማምረት አቅሙንም በማሻሻል በቀን ሁለት ሺህ ቲሸርቶች ማምረት ይችላል። እንዲሁም ሥራ ሲበዛ ከሌሎች ኢንተርፕራይዞች ማሽን በመከራየት ምርት የማምረት ሂደቱን ያከናውናል። ሦስት የጅምላ ተረካቢ ደንበኞችንም አፍርቷል።

ወ/ት ዓለም በልብስ ስፌት ሥራ ላይ ያጋጠማቸው ችግር ገበያ ሲሄዱ ብዙ ሰዎች አምነው ሥራ አይሠጧቸውም። ብዙ ሞክ ዋል ግን የሚያምናቸው ሰው አላገኙም፤ አምኖ ሳምፕል የሚሰጣቸው ሰው (ነጋዴ) አልነበረም። ስለዚህ ይህን ችግር ለመፍታት እሳቸው ገበያወን በማጥናት፣ ተለቅ ያሉት ቤተሰቦቻቸው ደግሞ በጥናቱ ላይ ተመሥርተው ነጋዴዎቹን ሄደው እንዲያነጋግሩ በማድረግ ሥራዎችን እየሠሩ ይገኛሉ።

ወ/ት ዓለም ስለ ሥራው አጠቃላይ መረጃ በደንብ ያገኙት ኮልፌ አጣና ተራ የሚባል ቦታ ነው፤ ስለ ሥራው አሠራር እና እንዲሁም ለልብስ ስፌት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችንም እዛው ነው የሚያገኙት። በጅምላ የሚሠሩትን ሥራም የሚያስረክቡት እዛው ኮልፌ ነው።

የኮቪድ ተፅዕኖ

በኮቪድ ጊዜ ማስክ መሥራት ሞክረው ነበር፤ ነገር ግን አላዋጣቸውም ብዙ ከተሠራበት በኋላ ነው ማምረት የጀመሩት። ከኮቪድ ይልቅ ድርጅቱን የጎዳው የሀገሪቱ የነበረው አለመረጋጋት ነው። ምክንያቱም የድርጅቱ ዘጠና በመቶ ሥራ በክልሎች ስለሆነ በዚህ ምክንያት ሥራ ሙሉ በሙሉ ቀዝቅዟል።Alem-Garment-T-Shirt

ምክር እና እቅድ

ወ/ት ዓለም በጨረታ ለመሳተፍ ለሁለት ዓመት እየሞከሩ ቢገኙም የተጨማሪ ዕሴት ታክስ (VAT) ተመዝጋቢ ባለመሆናቸው ምክንያት መሳተፍ አልቻሉም። ያን ለማድረግ ደግሞ ዓመታዊ ገቢ ከአምስት መቶ ሺህ ብር በላይ መሆን አለበት ስለተባሉ መመዝገብ አልቻሉም ነበር። በሚቀጥለው የበጀት ዓመት ላይ ተ.ዕ.ታ. (VAT) ተመዝጋቢ በመሆን በጨረታዎች ላይ ለመሳተፍ ትልቅ ፍላጎት አላቸው። ለዚህም 2merkato.com በከፍታ ፖርታል በኩል ለጥቃቅን እና አነሰተኛ ኢንተርፕራይዞች ባዘጋጀው የጨረታ እና ማስታወቂያ ፓኬጅ ለመጠቀም አቅደዋል።

አንድ ሰው ወደ ልብስ ስፌት ሥራ ከመግባቱ በፊት ደንበኛ አያያዝ ማወቅ፣ ጥሬ እቃ የት እንደሚገዛ ማወቅ፣ ምርቱን ለማን እንደሚያቀርብ ማወቅ አለበት። ወደ ሙያው ከገባ በኋላ ደግሞ የታዘዘውን ምርት በተባለው ሰዓት ማስረከብ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ይህንን ልማድ መጀመር እና ማዳበር አለባቸው ሲሉ ይመክራሉ።

ይህንንም ይመልከቱ

ሀሌታው ሀ ኅትመት እና ማስታወቂያ

ድርጅት የተመሠረተው በአቶ ዮናታን ታደሰ እና ሦስት መሥራች አባላት በ2012 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የኅትመት …