የተመሠረተው በ 2012 ዓ.ም በሼፍ ብርሐኑ ረጋሳ ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የዳቦ እና የኬክ ምርቶችን የሚያመርት ድርጅት ሲሆን፤ የድርጅቱ መሥራች ከድርጅቱ ምሥረታ በፊት ለሃያ ሦስት ዓመታት በሙያቸው ከትልቅ ድርጅቶች ጋር ተቀጥረው ሲሠሩ ቆይተዋል። ድርጅቱ አጠቃላይ የቤከሪ (ዳቦ፣ ኩኪስ፣ ኬኮች፣ ወዘተ መጋገር) ሥራዎችን የሚሠራ ድርጅት ሲሆን በአሁን ጊዜ ግን የኬክ ሥራዎች ላይ በደንብ አተኩሮ እየሠራ ይገኛል። አንዲሁም እስከ አንድ መቶ የሚደርሱ ሰዎችን የሚይዙ ስብሰባዎች ወይም ዝግጅቶች ላይ የሻይ ሰዓት ሪፍሬሽመንት (tea break refreshment) አገልግሎት የመስጠት ዝግጅቱን አጠናቆ ይገኛል።
ድርጅቱ የሚያቀርባቸው አገልግሎቶች
- ለሠርግ
- ለልደት
- ለቤቢ ሻወር
- ለብራይዳል
- ለምርቃት
ጣፋጭ (ዲዘርት) ምግቦች እንዲሁም አጠቃላይ የቤከሪ ሥራዎችን በጥራት ይሠራል።
ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት
የድርጅቱ መሥራች ድርጅቱን ከመመሥረታቸው በፊት ለሃያ ሦስት ዓመታት በተለያዩ ትላልቅ ድርጅቶች ማለትም እንደ ራዲሰን ብሉ ሆቴል፣ ሸራተን ሆቴል እና ከሀገር ውጭ ደግሞ ዛምቢያ፣ ናይጄሪያ እና ታንዛንያ ሄደው የመሥራት እድል ነበራቸው፤ ይህም በዘርፉ ትልቅ ልምድ እንዲያካብቱ አድርጓቸዋል። ያካበቱትንም ዕውቀት የግላቸውን ድርጅት ሲመሠርቱ ነገሮችን እንዳቀለላቸው ገልጸዋል። ዘ ኬክ ኮርነር ምርቶቹን ከአዲስ አበባ ወጣ ያሉ እንደ ቡራዩ ያሉ ከተሞች ድረስ ያቀርባል። ድርጅቱ በዋናነት የሚያመርታቸው የኬክ ምርቶች ሁለት አይነት ሲሆኑ ክሬም እና ፎም ኬክ ናቸው። የሚቀበለው ትዕዛዝ ደግሞ ትንሹ ሁለት ኪሎ ነው። የሚሠራቸው ኬኮች ዋጋ እንደ ወቅቱ እና የኬኩ አይነት ቢለያይም ከ650 ብር ጀምሮ ይሠራል።
ድርጅቱ ሥራዎችን የሚሠራው በዋናነት በሰው በሰው ሲሆን፤ ቀጥሎም ሶሻል ሚዲያ በመጠቀም እንደ ቴሌግራም (waw.cake) እና (ኬክ Corner) ፌስቡክ ላይ ያስተዋውቃል። ከነዚህ በተጨማሪ የሥራ ምንጭ ደንበኞችን ማርካት እንደሆነ የድርጅቱ መሥራች ያምናሉ። ይህም የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም እያሳካ ይገኛል። ለምሳሌ አስር ኪሎ ኬክ ያዘዘ ሰው ካፕ ኬክ በነጻ ይሰጠዋል፣ የሠርግ ኬክ ያዘዘ ሰው ደግሞ የማድረሻ ዋጋ ሳይከፍል ይደርስለታል እንዲሁም ሻምፓኝ ከኬኩ ጋር አብሮ ይቀርብለታል። እንዲሁም በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ በመገኘት እንደ ዝግጅቱ መጠን የተለያዩ አይነት ስጦታዎችን ያቀርባል እንደ ርችት እና ሌሎችም የተለያዩ ነገሮች።
ድርጅቱ ምርቱን ለትልቅ ድርጅቶች በማቅረብ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል ለምሳሌ አዋሽ ባንክ፣ ንግድ ባንክ እና ኢሲኤ ላይ በሚዘጋጁ ዝግጅቶች ላይ በመሳተፍ ምርቱን ሲያቀርብ ቆይቷል ያቀርባልም።
የኮቪድ ተፅዕኖ
ኮቪድ ዘ ኬክ ኮርነር ላይ ትልቅ ጉዳት አድርሶ ነበር። ምክንያቱም ገበያ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ቀንሶ ስለነበር ኬክ የሚያሠራ ሠው አልነበረም። ይህም የሆነበት ምክንያት የሠው ገቢ መቀዝቀዝ እንዱ ሲሆን ሌላው ደግሞ ወረርሽኙ ቶሎ እና በቀላሉ ስለሚተላለፍ ሰው በጣም ፈርቶ ነበር። ይህንንም አስቸጋሪ ጊዜ ለማለፍ ሼፍ ብርሐኑ ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን በአዋሽ ባንክ በኩል ባመቻቸው የብድር አገልግሎት የአርባ ሺህ ብር ብድር መበደራቸው የኮቪድን ጊዜ ለማለፍ ረድቷቸዋል።
ሼፍ ብርሐኑ ድርጅቱን ሲመሠርቱ በአንድ ሺህ ብር መነሻ ካፒታል ሲሆን አሁን ላይ ሀምሻ ሺህ ብር ካፒታል እና ለአንድ ሰው ቋሚ የሥራ እድል መፍጠር ችለዋል። እንዲሁም የድርጅቱ አቅም አድጓል ትልልቅ ማሽኖችን ገዝተዋል ያረጁ ማሽኖችን በአዲስ መቀየር ችለዋል በተጨማሪም ብዙ ደንበኞችን ማፍራት ችለዋል የራሳቸውንም ህይወት አሻሽለዋል።
ምክር
አዲስ ወደ ዘርፉ የሚገቡ ሰዎች ሙያውን መማር ብቻ በቂ አይደለም። ተምረው ሲጨርሱ በዘርፉ ውጤታማ ለመሆን ግዴታ ልምድ መኖር አለበት፤ አዲስ የሚገቡ ሰዎች ከተማሩ በኋላ ልምድ ቢኖራቸው ጥሩ ነው ይላሉ ሼፍ ብርሐኑ።
ድርጅቱ ወደ ፊት ከሦስት ዓመት በኋላ ሙሉ ሬስቶራንት መክፈት ብሎም ኮክቴሎች እና የእራት አገልግሎች የሚሠጥ ድርጅት በመሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የምግብ ኢንዱስትሪ ትንሽ ወደ ፊት ለማንቀሳቀስ እቅዶ እየተንቀሳቀሰ ነው።
ሼፍ ብርሐኑ የሠሩባቸውን ሆቴሎች እንዲሁም ልምድ እና ተሞክሮ በማግኘት የተሳተፉባቸውን ዝግጅቶች እና አካላት በሙሉ አመስግነዋል።
ድርጅቱ ምርት እና አገልግሎቱን በከፍታ የቴሌራም ቻናል ላይ ለማስተዋወቅ እንደሚጠቀምም ሼፍ ብርሐኑ ተናግረዋል።