ታክስ / ግብርን በተመለከተ
የኢትዮጵያ የፌደራል የታክስ አስተዳደር አዋጅ (ቁጥር 983/2008)፣ በታክስ ከፋዩ ሊከፈል የሚገባ እንደሆነና የመክፈያ ጊዜው የደረሰ ታክስ ለመንግሥት የሚከፈል ዕዳ እንደሆነ ይደነግጋል (አንቀጽ 30(1))።
በዚህም መሠረት፡-
- ታክስ የመክፈል ኃላፊነት ያለበት ሰው በባለሥልጣኑ [በገቢዎች ሚኒስቴር ወይም በገቢዎች ቢሮ] ዘንድ ለመመዝገብ ማመልከት አለበት።
- ለመመዝገብ ያመለከተው ሰው በታክስ ሕግ መሠረት ታክስ የመክፈል ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ባለሥልጣኑ ሲያምንበት ይመዘግበዋል፣ ለዚህ ሰውም በፀደቀው ቅጽ መሠረት የምስክር ወረቀት አዘጋጅቶ ይሰጠዋል።
- ባለሥልጣኑ ለመመዝገብ ማመልከቻ ያቀረበውን ሰው ጥያቄ ያልተቀበለው ከሆነ የምዝገባውን ጥያቄ የማይቀበለው መሆኑን ማመልከቻው ከቀረበበት ቀን ጀምሮ ባሉት 04 (አሥራ አራት) ቀናት ውስጥ ለምዝገባ ላመለከተው ሰው በጽሁፍ ያሳውቀዋል።
- የአንድ ሰው ምዝገባ ተፈፃሚ የሚሆነው የዚህን ሰው ምዝገባ በሚያረጋግጠው የምስክር ወረቀት ላይ ከተመለከተው ቀን ጀምሮ ነው።
- ለውጦችን ስለማሳወቅ፡ ማንኛውም የተመዘገበ ሰው ከሚከተሉት ውስጥ ማንኛውንም ጉዳይ በተመለከተ ለውጥ ሲከሰት ለውጡ በተከሰተ በ30 ቀናት ውስጥ ለባለሥልጣኑ በጽሁፍ ማሳወቅ አለበት፦
- ስሙ፣ ቋሚ አድራሻው ወይም የፖስታ አድራሻው፣ የተቋቋመበት መተዳደሪያ ደንብ ወይም ዋንኛ የሥራ እንቅስቃሴው ወይም እንቅስቃሴዎቹ፤
- ከባለሥልጣኑ ጋር ግንኙነት የሚያደርግበት የባንክ አድራሻ፤
- ከባለሥልጣኑ ጋር ግንኙነት የሚያደርግበት የኤሌክትሮኒክ አድራሻ፤ [ኢሜይል]
- ባለሥልጣኑ በመመሪያ የሚወስናቸው ሌሎች ዝርዝሮች።
- ባለሥልጣኑ ለታክስ ሕጎች ዓላማ ሲባል ለተመዘገቡ ሰዎች የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር አዘጋጅቶ ይሰጣል።
- አንድ የታክስ ከፋይ ሊኖረው የሚችለው አንድ የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር ብቻ ይሆናል
- የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር የተሰጠው ሰው የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥሩን በማንኛውም የታክስ ማስታወቂያ፣ ማስታወቂያ ወይም ለታክስ ሕግ ዓላማ ሲባል በሚቀርብ ወይም ጥቅም ላይ በሚውል ሰነድ ወይም በታክስ ሕግ መሠረት በሚዘጋጅ ሰነድ ላይ መግለጽ ይኖርበታል፣ እንዲሁም ታክስ ከፋዩ ታክስ ቀንሶ የማስቀረት ግዴታ ባለበት ሰው ክፍያዎች በሚፈጽምለት ጊዜ የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥሩን መስጠት አለበት።
- የንግድ ሥራ ለመሥራት ፈቃድ ይሰጠው ዘንድ ማመልከቻ የሚያቀርብ ታክስ ከፋይ ፈቃድ ለሚሰጠው ባለሥልጣን የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥሩን መስጠት አለበት።
- ታክስ ከፋዩ ፈቃዱን በሚያድስበት ጊዜ የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር ማቅረብ የሚጠበቅበት የመጀመሪያው የፈቃድ ማመልከቻ ከቀረበ ወዲህ የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥሩ የተቀየረ እንደሆነ ብቻ ነው።
- የንግድ ወይም የሥራ ፈቃድ የሚሰጥ የመንግሥት አካል ወይም ተቋም ታክስ ከፋዩ የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥሩን ሳያቀርብ ፈቃድ መስጠት አይችልም።
- የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር ለተሰጠው ሰው ብቻ የሚያገለግል ስለሆነ በሌላ ሰው ጥቅም ላይ ሊውል አይችልም።
- የታክስ ወኪል የአንድን ሰው የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር በሚከተለው መልኩ ሊጠቀም ይችላል፦
- የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥሩ ባለቤት የሆነው ሰው የታክስ ወኪል የታክስ መለያ ቁጥሩን ለመጠቀም እንዲችል በጽሑፍ ሲፈቅድለት፤ እና
- የታክስ ወኪሉ የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥሩን ለታክስ ከፋይ መለያ ቁጥሩ ባለቤት የታክስ ጉዳዮች ብቻ ሲጠቀምበት ነው።
- በሚከተሉት ሁኔታዎች ውስጥ ባለሥልጣኑ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥርን ሊሰረዝ ይችላል
- የታክስ ከፋዩ ምዝገባ ሲሰረዝ፤
- የታክስ ከፋዩ እውነተኛ ማንነት ባልሆነ ማንነት የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥሩ የተሰጠ እንደሆነ፤
- ታክስ ከፋዩ ጥቅም ላይ ያለ ሌላ የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር ያለው እንደሆነ።
- ባለሥልጣኑ በማንኛውም ጊዜ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ በመስጠት የአንድን ሰው የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር በመሰረዝ አዲስ የታክስ መለያ ቁጥር ሊሰጠው ይችላል።
- ለታክስ ሕግ ዓላማ ሲባል አንድ ታክስ ከፋይ በታክስ ሕግ መያዝ ያለባቸውን ሰነዶች በኤሌክትሮኒክ መልክ ጨምሮ የመያዝ ግዴታ ያለበት ሲሆን እነዚህም ሰነዶች የሚያዙት፦
- በአማርኛ ወይም በእንግሊዝኛ፤
- በኢትዮጵያ ውስጥ፤ እና
- የታክስ ከፋዩን የታክስ ግዴታ በግልጽ ለማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ፤ መሆን አለበት።
- በታክስ ሕግ መሰረት ሰነዶችን እንዲይዝ የሚገደድ ታክስ ከፋይ በማንኛውም ምክንያታዊ ጊዜ ውስጥ ሰነዶቹን ለባለሥልጣኑ ምርመራ ዝግጁ የማድረግ ግዴታ አለበት።
- በአማርኛ ወይም በእንግሊዝኛ፤
- ደረሰኞችን በተመለከተ
- የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ ያለበት ታክስ ከፋይ ደረሰኞች ከማሳተሙ በፊት የእነዚህን ደረሰኞች ዓይነትና ብዛት በባለሥልጣኑ ማስመዝገብ አለበት።
- ማንኛውም የሂሣብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ ያለበት ታክስ ከፋይ ለሚያከናውነው ግብይት ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ አለበት።
የግብር ዓይነቶች
- የገቢ ግብር
የገቢ ግብር የቅጥር ገቢ፣ የንግድና የግል እንቅስቃሴዎች፣ ኗሪ ባልሆኑ ሰዎች አዳዲስ የፈጠራ እንቅስቃሴዎች፣ ተንቀሳቃሽ ንብረቶችንና የመሳሰሉትን ያጠቃልላል። ማንኛውም ተቀጣሪ ከደሞዙ ላይ ይህንን ግብር መክፈል አለበት። ከመቀጠር የሚገኝ ወርሃዊ ገቢ ላይ፣ እንደየገቢው መጠን የሚከተለው ግብር የሚከፈል ይሆናል፡-
በየወሩ በመቀጠር የሚገኝ ገቢ (በብር) | የግብር መጠን | ተቀናሽ የሚሆን መጠን |
0 – 600 | 0% | 0 |
601 – 1,650 | 10% | 60 |
1,651 – 3,200 | 15% | 142.50 |
3,201 – 5,250 | 20% | 302.50 |
5,251 – 7,800 | 25% | 565 |
7,801 – 10,900 | 30% | 955 |
ከ10,900 በላይ | 35% | 1,500 |
የሚከፈል ግብር = ደመወዝ X የግብር መጠን (%) – ተቀናሽ
የገቢ ግብር ስሌት
ምሳሌ፡-
ደመወዝ 2,000 ብር ቢሆን
የሚከፈል ግብር = 2,000 X 15% – 142.50 = 157.50
ደመወዝ 7,000 ብር ቢሆን
የሚከፈል ግብር = 7,000 X 25% – 565 = 1,185
- የኮርፖሬት ታክስ
የኮርፖሬት ታክስ ድርጅቶች ካገኙት የተጣራ ትርፍ ላይ የሚከፍሉት የታክስ ዓይነት ነው። የዚህ ታክስ መጠኑ ኮርፖሬቱ በሰራው ስራ ላይ ታክስ ከሚደረጉ የኮርፖሬቱ ኘሮጀክቶች 30% ነው። - የተርንኦቨር ታክስ
ይህ ታክስ ዓመታዊ ገቢያቸው ከ500,000 ብር በታች የሆኑ እና የተጨማሪ ዕሴት ታክስ የማይመለከታቸውን ያጠቃልላል። የሚሰላውም በአጠቃላይ ከተገኘው ገቢ 10 በመቶውን በመውሰድ ነው። - የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት)
የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) ዓመታዊ ገቢያቸው ከ500,000 ብር በላይ የሆኑ የግብር ከፋዮች በሚያደርጓቸው በእያንዳንዱ ታክስ ያስከፍላል ተብሎ የተደነገገ የንግድ ልውውጥ ከደንበኞቻቸው 15% ታክስ እየሰበሰቡ ለመንግስት ገቢ የሚያደርጉት የታክስ ዓይነት ነው። - ኤክሳይዝ ታክስ
ይህ አገር ውስጥ የተመረቱ ምርቶች ላይ የሚደረግ የታክስ አይነት ነው።
ከእነዚህ ሌላ ከውጪ የሚገቡ እቃዎች ላይ፣ የባለቤትነት እና የሼርሆልደሮች ላይ የሚደረግ ታክሶች ዊዝ ሆልዲንግ ታክስ፣ ሮያሊቲ ታክስና ዲቪደንድ ታክስ ናቸው።
የግብር ከፋይ ደረጃዎች
ግብር ከፋዮች፣ እንደሚከፍሉት ግብር መጠን በሦስት ደረጃዎች ይመደባሉ፡-
- ደረጃ “ሀ” ግብር ከፋይ
ጠቅላላ ዓመታዊ ገቢው 1 ሚሊዮን ብር ወይም ከዚያ በላይ የሆነ ድርጅት ወይም ግለሰብ
- ደረጃ “ለ” ግብር ከፋይ
ድርጅትን ሳይጨምር ዓመታዊ ጠቅላላ ገቢው ከ500,000 እስከ 1 ሚሊዮን ብር የሆነ
- ደረጃ “ሐ” ግብር ከፋይ
ድርጅትን ሳይጨምር ዓመታዊ ጠቅላላ ገቢው ከ500,000 ብር በታች የሆነ
መዝገብ አያያዝ
የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮች በፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃዎች መሠረት የተዘጋጁ የሂሳብ መዝገቦችን የመያዝ ግዴታ ያለባቸው ሲሆን፤ በተለይም የሚከተሉትን መዛግብት መያዝ አለባቸው፡-
- ቋሚ ሀብቶች የተገዙበትን ቀን፣ የተገዙበትን ዋጋ፣ ሀብቱን ለማሻሻል የወጣውን ወጪ እና የሀብቱን የወቅቱን የተጣራ የመዝገብ ዋጋ የሚያሳይ ሰነድን ጨምሮ የንግድ ሥራውን ሀብትና ዕዳ የሚያሳይ መዝገብ፤
- ከግብር ከፋዩ ንግድ ሥራ ጋር በተያያዘ በየቀኑ የተገኘውን ማናቸውንም ገቢ እና ወጪ የሚያሳይ ሰነድ፤
- ከንግድ ሥራው ጋር በተያያዘ የንግድ ዕቃዎችን ግዢና ሽያጭ እንዲሁም በግብር ከፋዩ የተሰጡ እና የተገኙ አገልግሎቶችን በተመለከተ የሚከተሉትን የሚያሳይ ሰነድ፤
- ለገበያ የዋሉትን ወይም የተቀበላቸውን የንግድ ዕቃዎች እና የተሰጠውን ወይም የተገኘውን አገልግሎት ዝርዝር፣
- ከግብር ከፋዩ ላይ የንግድ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን የገዙ ወይም ለግብር ከፋዩ ያቀረቡ ሰዎችን ስም እና የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር (እንደ ሁኔታው)፣
- የአቅራቢውን የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር የያዙ አስቀድሞ ቁጥር የተሰጣቸው ደረሰኞችን፣
- በግብር ዓመቱ መጨረሻ በግብር ከፋዩ እጅ የሚገኙ የንግድ ዕቃዎችን ዓይነት፣ መጠንና ዋጋ እና የዋጋ መገመቻ ዘዴን የሚያሳይ ሰነድ፤
- የግብር ከፋዩን የግብር ኃላፊነት ለመወሰን የሚያስችል ሌላ ማንኛውምሰነድ።
የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች የሚከተሉትን ሰነዶች የመያዝ ግዴታ አለባቸው፡-
- የየቀኑን ገቢ እና ወጪ የሚያሳይ መዝገብ፤
- ሁሉንም ግዥዎችና ሽያጮችን የሚያሳይ መዝገብ፣
- የደመወዝንና የአበሎች መዝገብ፤
- የግብር ከፋዩን የግብር ኃላፊነት ለመወሰን የሚያስችል ሌላ ማንኛውም አግባብነት ያለው ሰነድ፤
የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ በሚወሰነው መሠረት ጠቅላላ የሽያጭ
ገቢያቸውን የሚያሳይ ወይም ሌላ አስፈላጊ መዝገብ ሊይዙ ይችላሉ።
በተጨማሪ፣ ከቤት ኪራይ ገቢ የሚያገኙ የደረጃ “ሀ” ወይም “ለ” ግብር ከፋዮች የሚከተሉትን ሰነዶች የመያዝ ግዴታ አለባቸው፡-
- ከኪራይ የተቀበለውን ገቢ የሚያሳይ ሰነድ፤
- ከቤቱ ጋር በተያያዘ ለመንግሥት ወይም ለከተማ አስተዳደር የተከፈሉትን ክፍያዎች የሚያሳይ ሰነድ፤
- ከቤቱ ጋር ተያይዞ የሚወጣውን ማንኛውንም ወጪ የሚያሳይ ሰነድ፤
- የሚከራየው ሕንፃ የተገኘበትን ቀን፣ ሕንፃው የተገኘበትን ዋጋ፣ ሕንፃውን ለማሻሻል የወጣውን ወጪ እና የህንፃውን የወቅቱን የተጣራ የመዝገብ ዋጋ የሚያሳይ ሰነድ፤
- ቤቱን በሚመለከት የተደረገ ማንኛውንም የተከራይ አከራይ ስምምነት የሚያሳይ ሰነድ፤