መነሻ / ፋይናንስ እና ኢንቨስትመንት / የግል ብድር እና ቁጠባ ተቋማት / “ዛሬ የቆጠቡት አነስተኛ ገንዘብ ለነገው ሀብት የመሠረት ድንጋይ ነው።” የምሥራች ማይክሮ ፋይናንስ አ.ማ.
yemisrach-microfinance

“ዛሬ የቆጠቡት አነስተኛ ገንዘብ ለነገው ሀብት የመሠረት ድንጋይ ነው።” የምሥራች ማይክሮ ፋይናንስ አ.ማ.

የምሥራች ማይክሮ ፋይናንስ አ.ማ. ለማኅበረሰቡ በዋናነት የአክሲዮን ሽያጭ፣  የቁጠባ አገልግሎት እና የብድር አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ለጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ የሚሆኑ ብድሮችንም አዘጋጅቷል። አግልግሎቱንም አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ ስድስት ቅርንጫፎች ይሰጣል።

ምሥረታ

የምሥራች ማይክሮፋይናንስ አ.ማ. በኢትዮጵያ ወ/ቤ/ክ/መካነ ኢየሱስ አነሳሽነት ከ1900 በላይ በሚሆኑ ባለሀብቶች ተደራጀ። ሀምሌ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕጋዊ ፍቃድ አግኝቶ የቁጠባና ብድር አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ድርጅት ነው። ቀዳሚ ተልዕኮው ከባንክ የብድር አገልግሎት ማግኘት የማይችሉትን በኢትዮጵያ ሁሉም ክልሎች ውስጥ በከተማ እና በገጠር የሚኖሩ የኅብረተ ሰብ ክፍሎችን ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት ነው።

ራዕይ

ማይክሮ ፋይናንሱ ትልቅ ተፅዕኖ ፈጣሪ የለውጥ ኃይል በመሆን በገጠር እና ከተማ የሚኖሩ ሴቶችን፣ ወጣቶችን እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙትን አምራች ዜጎችን የፋይናንስ ተደራሽነት በማስፋት ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ነው።

የምሥራች ማይክሮፋይናንስ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች

 1. የአክሲዮን ሽያጭ
 2. የቁጠባ አገልግሎት
 3. የብድር አገልግሎት
 4. የሦስተኛ ወገን ገንዘብ የማስተዳደር አገልግሎት
 5. ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ተቀናጅቶ መሥራት
 6. የአነስተኛ ኢንሹራንስ አገልግሎት እና
 7. የፋይናንስ ነክ ያልሆኑ የቢዝነስ ልማት ትምህርቶችና ሥልጠና መስጠት
 • የሼር ሽያጭ በሁሉም ክልሎች የኢት/ወ/ቤ/ክ/ሲኖዶሶች አማካኝነት ሽያጩ ይከናወናል።
 • ሌሎች አገልግሎቶች በአሁን ወቅት በአራት ክልሎች ውስጥ ስድስት ቅርንጫፎችን ማለትም በአዲስ አበባ፣ ዱራሜ፣ ኢጃጅ፣ ሀዋሳ እና ነቀምት ከተሞች በከፈታቸው ቅርንጫፎች ለማኅበር ሰቡ የቁጠባና የብድር አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
 • አክሲዮኑ በዋና መሥሪያ ቤት እና በሁሉም ቅርንጫፎች እየተሸጠ ይገኛል። አክሲዮኑም ለመግዛት ህጋዊ እና የታደሰ የቀበሌ መታወቂያ ማቅረብ ይጠበቃል።
 • የአንድ አክሲዮን ዋጋ ብር 1000.00 ሲሆን የአገልግሎት 5% ይከፈላል። አ
 • አንድ ሰው የሚገዛው ዝቅተኛ አክሲዮን 5 ሲሆን የሚከፍለው የአክሲዮን ዋጋ 5,000.00 ብር የአገልግሎት ዋጋ 250.00 ብር አንድ ላይ 5,250.00 ብር ይከፍላል።
 • አንድ ሰው የሚፈልገውን የአክሲዮን ዋጋ በማመልከት መግዛት ይችላል።
 • አክሲዮን ሲገዙ ገንዘብ በድርጅቱ ሂሳብ ቁጥር ብቻ ገቢ በማድረግ ደረሰኙን ይዞ ለተወከሉ ሰዎች ማቅረብ ያስፈልጋል።
የምሥራች ማይክሮ ፋይናንስ ኅብረተ ሰቡ ከድህነት ሊላቀቅ የሚችለው በሚያገኘው ብድር ብቻ ሳይሆን በየጊዜው ከሚያገኘው የዕለት ገቢ እየቀነሰ በሚያስቀምጠው ቁጠባ እንደሆነ ያምናል። በመሆኑም ለኅብረተ ሰቡ ሦስት ዓይነት የቁጠባ አገልግሎቶችን አዘጋጅቶ አጓጊ ወለድ በመክፈል እያገለገለ ይገኛል።

የፈቃደኝነት ቁጠባ (Pass Book Saving)

ይህ የቁጠባ ዓይነት ተበዳሪ የሆኑና ያልሆኑ ደንበኞች በማናቸውም ጊዜ ገንዘባቸውን ለማጠራቀምና ያጠራቀሙትን ገንዘብ በከፊልም ሆነ በሙሉ ወጪ ለማድረግ የሚችሉበት የቁጠባ አገልግሎት ሲሆን የሚያስገኘውም ወለድ ባንኮች ከሚከፍሉት ወለድ ከፍ ያለና ከ8 በመቶ እስከ 10 በመቶ ነው። ይሄውም
 1. እስከ 10,000 ለሚቆጥቡ - 8 %
 2. ከ 10,001-100,000 ለሚቆጥቡ - 9 %
 3. ከ 100,001 በላይ ለሚቆጥቡ - 10 % የሚከፍል ይሆናል።

የጊዜ ገደብ ቁጠባ (Time Deposit)

የጊዜ ገደብ ቁጠባ ከ100,000 ብር ጀምሮ ገንዘብ በድርጅቱ በማስቀመጥ የሚከፈት የቁጠባ ሂሳብ ሆኖ ጠቀም ያለ ወለድ የሚያስገኝ ቁጠባ ነው። አሠራሩም በሦስት ይከፈላል።
 1. ለአንድ ዓመት በውል ለሚያስቀምጡ - 12.5%
 2. ለሁለት ዓመት እና ከዚያ በላይ ለሚያስቀምጡ - 13%
 3. ገንዘቡ ለአንድ ዓመት እና ከዚያ በላይ በማስቀመጥ ወለዱን በየወሩ መውሰድ ለሚፈልጉ - 12% ወለድ ያስገኛል።

በየጊዜው እያደገ የሚሄድ የጊዜ ገደብ ቁጠባ (Growth Term Deposit)

ይሄኛው የቁጠባ ዓይነት በየጊዜው ተመሳሳይ አይነት የብድር መጠን በዕቁብ መልክ በየጊዜው ማስቀመጥ ሲሆን ቢያንስ ለአንድ ዓመት ማስቀመጥ ይኖርበታል። ይህ የቁጠባ ዓይነት ጠቀም ያለ ወለድ የሚያስገኝ ቁጠባ ነው። ወለዱም 8-10 በመቶ እንደ ገንዘቡ መጠን ይሆናል።
የምሥራች ማይክሮ ፋይናንስ ተመጣጣኝ በሆነ ወለድ ስድስት ዓይነት የብድር አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል።

የጥቃቅን ንግድ ሥራ የቡድን ብድር (Micro Enterprise Loan)

በጥቃቅን ንግድ ሥራዎች ላይ ለተሰማሩ የኅብረተ ሰብ ክፍሎች ሥራዎቻቸውን ለማጠናከርና ለማስፋፋት የሚያስችል የብድር አገልግሎት የሚያቀርብ ሲሆን ለሥራው የሚያስፈልገው መስፈርት ለሚያሟሉ ደንበኞች በቡድን እስከ ብር 15,000.00 የሚደርስ ብድር ከ12-24 ወራት ተከፍሎ የሚያልቅ ይፈቀድላቸዋል።

የአነስተኛ ንግድ ሥራ የግል ብድር (Individual Business Loan)

የዚህ ብድር ተጠቃሚዎች በልዩ ልዩ ንግድ፣ አገልግሎት ሰጪና የማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩና ሥራቸውን ለማስፋፋት የሚፈልጉ ደንበኞች ሲሆኑ በግል ዋስትና እንዲያቀርቡ በማድረግ ከብር 10,000.00 በላይ ብድር ይፈቀድላቸዋል። ከፍተኛው የብድር መጠን ብር 100,000.00 የሚደርስ ሲሆን ደንበኞች የብድሩን ገንዘብ ለታሰበው ዓላማ ብቻ ማዋል ይጠበቅባቸዋል።

የፍጆታ ብድር (Consumption Loan)

ይህ ብድር ለጊዜያዊ የገንዘብ እጥረት ማቃለያ፣ ለቤት ቁሳቁስ መግዣ እና ለመሳሰሉት የሚሰጥ ብድር ሲሆን፣ በታወቁ ድርጅቶች ውስጥ በቋሚነት ለሚሠሩ ተቀጣሪዎች፣ ነዋሪ ሆኖ አስተማማኝ ዋስትና እና ከሚሠሩበት መ/ቤት ጋር ተጨማሪ ስምምነት በማድረግ የሚሰጥ የብድር መጠኑ የሚወሰነው በደመወዛቸው መጠን ሆኖ ከ10,000.00 እስከ 100,000.00 ድረስ ይሆናል።

የግንባታ ሥራ ብድር

ይህ የብድር ዓይነት ለቤቶች ሥራ እና ጥገና፣ እንዲሁም ለተጀመሩ ቤቶች ማስጨረሻ የሚውል ሲሆን የብድር መጠኑ ከ10,000.00 እስከ 100,000.00 ድረስ ይሆናል።

የእርሻ ሥራ ብድር (Agricultural Loan)

የእርሻ ሥራ ብድር የሚሠጠው በእርሻ ሥራ እንቅስቃሴ ላይ ለተሰማሩ ብድር ፈላጊዎች በቡድን የሚሰጥ ሲሆን የእርሻ ብድር መጠን ከብር 8,000.00 እስከ 15,0000.00 ድረስ በየዙሩ እያደገ የሚሄድ ይሆናል። ተበዳሪዎች መስፈርቱን በሙሉ ማሟላት ይጠበቅባቸዋል።

የእርሻ ንግድ ሥራ ብድር (Agricultural Business Loan)

የእርሻ ንግድ ሥራ ብድር የሚሰጠው ለእርሻ ነክ ንግድ ሥራዎች እንቅስቃሴ ላይ ለተሰማሩ ብድር ፈላጊዎች ሲሆን የእርሻ ነክ ንግዶች ማለትም (እህል ንግድ፣ ከብት ማደለብ እና የመሳሰሉትን ለሚሠሩ) የብድር መጠን ከብር 10,000.00 እስከ 16,000.00 ድረስ በየዙሩ እያደገ የሚሄድ ይሆናል።
ተበዳሪዎች መስፈርቱን ሙሉ በሙሉ ማሟላት ይጠበቅባቸዋል።
ቅርንጫፍስልክ
መካኒሳ ቅርንጫፍ (ዋና መ/ቤት)011 3689710, 011 3698674, 011 3698784
ዱራሜ ቅርንጫፍ046 5540180-83
እጃድ ቅርንጫፍ0913 645228
ሀዋሳ ቅርንጫፍ0916 161917
ሆሳዕና ቅርንጫፍ0911 004130
ነቀምት ቅርንጫፍ0916 088070

ማስታወሻ፦ ይሄ መረጃ የተዘጋጀው የምሥራች ማይክሮ ፋይናንስ በአካል ሄዶ በመጠየቅ በተገኘው መረጃ ላይ ተመሥርቶ ለጥቃቅን እና አነስተኛ ድርጅቶች በሚጠቅም መልኩ ተቀናብሮ ነው።

ይህንንም ይመልከቱ

ኒኦ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ.

ኒኦ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ. ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባገኘው ፈቃድ መሠረት በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ላይ …