ዘኪ ባግስ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ዘካርያስ እስጢፋኖስ በ2011 ዓ.ም. የግል ኢንተርፕራይዝ በመሆን ነው። ይህ ድርጅት የሚያመርታቸው ምርቶች አጠቃላይ የቆዳ ቦርሳዎችን ሲሆን ምርቶቹን በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚ እና ነጋዴ ያከፋፍላል።

የሚያመርታቸው ምርቶች

  • ቀበቶ
  • የወንዶች የኪስ ቦርሳ
  • የወንዶች ሳይድ ቦርሳ
  • ትልቅ እና ትንሽ የሴት ቦርሳዎች
  • የቁልፍ መያዣ

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

አቶ ዘካርያስ ወደ ቆዳ ዘርፍ የገቡት በአጋጣሚ የእድል ነገር ሆኖ ነው እንጂ እሳቸው በጊዜው የቆዳ ትምህርት እንኳን እንደነበረ እያውቁም ነበር። በአጋጣሚ ደረሳቸው፤ ገብተው ከተማሩ በኋላ ነው ወደ ቆዳ ዘርፍ የተቀላቀሉት። ትምህርታቸውን እንደጨረሱ በቆዳ ሥራ ተቀጥረው ለዐሥር ዓመታት ሠርተዋል። በዚህም የቆይታ ጊዜያቸው ምን ከምን ማድረግ እንደሚገባ እና ሥራው እንዴት እንደሚሠራ በቂ ዕውቀት ካካበቱ በኋላ የግል ሥራ ለመሥራት ማሰብ ጀመሩ። ለዚህም ሥራቸውን እየሠሩ አንድ ማሽን በመግዛት፣ በቤታቸው ውስጥ አንዳንድ ሥራዎችን ከሚሠሩበት ድርጅት በመውሰድ፣ ማታ እና ሌሊት በመሥራት ነበር የግል ሥራቸውን የጀመሩት።

አቶ ዘካርያስ በዘርፉ ረዘም ላለ ጊዜ መቆየታቸው በጣም ብዙ ጠቃሚ ነገሮችን አስተምሯቸዋል። ለምሳሌ በቆዳ ሥራ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ሥራዎች ራሳቸው እዲሠሩ አስችሏቸዋል። እንደ ቆረጣ እና ዲዛይን ሥራ የመሳሰሉ ሥራዎችን ሌሎች ድርጅቶች ከፍተኛ ዋጋ በማውጣት ነው የሚያሠሩት፤ እሳቸው ግን ራሳቸው ናቸው የሚሠሩት። ይህ ደግሞ አላስፈላጊ ወጪ እንዳያወጡ እና ለዛ ሥራ ይመደብ የነበረውን በጀት ወደ ሌላ ሥራ እንዲያዞሩ ጠቅሟቸዋል።

ድርጅቱ ሲመሠረት በአምስት ሺህ ብር ካፒታል ሲሆን አሁን ላይ ካፒታሉ ሦስት መቶ ሺህ ብር ደርሷል። የአቶ ዘካርያስ በዘርፉ ላይ የረጅም ጊዜ ልምድ መኖር ለምርቱ በጥራት መመረት እና ለሥራው ማደግ ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክቷል። እንዲሁም የማሽን ብዛት ከአንድ ማሽን ወደ አምስት ማሽኖች ያደገ ሲሆን፤ ከዚህም ጋር በተያያዘ ለአምስት ሠራተኞች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ድርጅቱ አሁን ባለው አቅም በቀን ሃያ አራት ትልቅ ቦርሳዎችን በጥራት ማምረት ይችላል። የሚያመርታቸውን ቦርሳዎች ከአራት መቶ ብር እስከ ዘጠኝ መቶ ብር ድረስ በሆነ ዋጋ ለገበያ እያቀረበ ይገኛል።

አቶ ዘካርያስ የቆዳን ሥራ በሚገባ ቢያውቁም ችግሮች ነበሩ። ለምሳሌ፦ ግብዓት ላይ ያለው ችግር፣ ገበያ፣ ሠራተኛ ማስተዳደር፣ ግዢ እንዲሁም አብዛኛው የሀገራችን አሠራር የክሬዲት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሥራ ማስኬጃ ካፒታል እጥረት፤ ወዘተ ሥራው ውስጥ የነበሩ እና ያሉ ፈተናዎች ናቸው። በተቃራኒው ደግሞ ለሌሎች ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻል እና የራስን ምርት ማምረት መቻል በጣም የሚያስደስት ነገር እንደሆነ ተናግረዋል። አቶ ዘካርያስ “እኔ ሥራ ስጀምር ብዙም ችግር አልነበረም፤ አሁን ላይ ነው በጣም አስቸጋሪ የሆነው። አሁን የጥሬ እቃ አለመገኘት (አንዳንዴ ሥራ ወስደህ እቃ የለም ትባላለህ) እና የጥሬ እቃ ዋጋ መጨመር ዋና ችግሮች ሆነዋል። የጥሬ እቃ ዋጋው ሲጨምር ያለው አማራጭ ደንበኛውን ላለማጣት በኪሳራ መሥራት ወይም ደግሞ ሥራውን መመለስ ነው።  ስለዚህ ገበያውን ለማረጋጋት መንግሥት የሆነ ነገር ቢያደርግ አንዲሁም የምርት ማሳያ ቦታ ቢያዘጋጅ መልካም ነው” ሲሉ ሀሳባቸውን አካፍለዋል።

ድርጅቱ ምርቶቹን የሚያስተዋውቀው በቀዳሚነት ባዛሮችን በመጠቀም እና ቢዝነስ ካርዶችን በመጠቀም ነው። በመቀጠል ደግሞ ስታዲየም እና መርካቶ አካባቢ ላሉ ነጋዴዎች በትዕዛዝ የሚመጡ ሥራዎችን በጥራት በመሥራት እነሱ እራሳቸው እንዲመጡ በማድረግ ነው።

አቶ ዘካርያስ በሥራ አንዳንድ ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ብዙ ግዜ ራሳቸው ናቸው የሚፈቱት፤ በቂ ልምድ ስላላቸው በብዛት የሚከሰቱትን ችግሮች ቀድመው ስለሚያውቁ ይጠነቀቃሉ። አንዳንዴ ደግሞ ከሠራተኞቻቸው ጋር በመወያየት ይፈታሉ፤ እሳቸው ከሠራተኞቻቸው ይማራሉ እንዲሁም ሠራተኞቻቸውን ያስተምራሉ። በዚህም ከሠራተኞቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት በጣም ጥሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

የኮቪድ ተፅዕኖ

በኮቪድ ጊዜ ድርጅቱ ሙሉ በሙሉ አልተዘጋም ነበር፤ በሳምንት ሦስት ቀን አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ተራ በተራ ሠራተኞች እየገቡ ይሠሩ ነበር። ይሁን እና ግን ሥራ በጣም ቀዝቅዞ የነበረ ሲሆን በተራረፉ ቆዳዎች አንዳንድ የፈጠራ ሥራዎችን በመሥራት፣ እንዲሁም ደግሞ በመሀልም እንዳንድ ትዕዛዞች ሲመጡ እነሱን በመሥራት እና የማስክ ሥራ በሰው በሰው መጥቶ እነዚህን ሥራዎች በመሥራት ነው የኮቪድን ጊዜ ያሳለፉት። በኮቪድ ጊዜ የማስተር ካርድ ፋውንዴሽንን ብድር የወሰዱ ሲሆን ይህም በጣም ተጠቅመውበታል።

ምክር እና እቅድ

ድርጅቱ ከሦስት ዓመት በኋላ የማሽን ቁጥር መጨመር እና ሠራተኛ የማብዛት እቅድ አለው። የረጅም ጊዜ እቅዱ ደግሞ ትልቅ ፋብሪካ በመሆን ዐሥር ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር የሚችል ድርጅት መሆን ነው።

አዲስ ጀማሪ ወደ ቆዳ ሥራ ለሚገቡ ሰዎች ሙያውን በሚገባ ማወቅ በጣም ወሳኝ ነገር ነው፤ በመቀጠል ደግሞ ገንዘብ አስፈላጊ ነው። በአሁን ሰዓት ጥሬ እቃ በጣም ነው የተወደደው፤ በዚህም ላይ ደግሞ አይገኝም ስለዚህ አቅራቢዎች ማግኘት ብቻ ሳይሆን ማወቅ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይመክራሉ።

አቶ ዘካርያስ  የከፍታ አገልግሎትን በሬዲዮ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ የሰሙት፣ በመቀጠልም ከኮል ሴንተር 6131 ተደውሎላቸው የኮቪድ ነጻ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተነግሮአቸው ነበር።

እንደ ማጠቃለያ ድርጅቱ አሁን ያለበት ችግር የማስታወቅያ ችግር ነው ይህንም ለማስተካከል የድርጅቱ መሥራች 2merkato.com ለጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ያዘጋጀውን የከፍታ አገልግሎት ለመጠቀም አዲስ ስልክ ገዝተው በዝግጅት ላይ ናቸው።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …