መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ይትባረክ ላቀው ልብስ ስፌት

ይትባረክ ላቀው ልብስ ስፌት

ይትባረክ ላቀው ልብስ ስፌት የተመሠረተው የግል ኢንተርፕራይዝ ሆኖ በአቶ ይትባረክ ላቀው በ2009 ዓ.ም ነው። ድርጅቱ በዋናነት የሚያመርታቸው ምርቶች የሴቶች እና የህጻናት አልባሳት ሲሆኑ ለህጻናት ከአንድ ዓመት አስከ ስምንት ዓመት ለሚደርሱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ምርቱን በብዛት ያመርታል። ከዚህ በተጨማሪ አጠቃላይ የአልባሳት ሥራዎችን ይሠራል።

ድርጅቱ ከሚያመርታቸው ምርቶች መካከል ጥቂቶቹ

  • የህፃናት አልባሳት
  • የተማሪ ዩኒፎርሞች
  • ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ የሠራተኛ አልባሳት
  • የሴት ቀሚሶች፣ ሸሚዞች፣ ቱታዎች እና በደንበኛ ትዕዛዝ የሚመጡ አጠቃላይ የአልባሳት ሥራዎችን ይሠራል።

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

አቶ ይትባረክ ወደ ልብስ ስፌት የሥራ መስክ የገቡት ካለው ሰፊ የሥራ እድል አንጻር እንደሆነ ገልፀዋል። “ሁሉ ነገር ከውጭ አገር ነው የሚመጣው ይህ ማለት ደግሞ በቂ ገበያ በአገር ውስጥ አለ፤ ስለዚህ በተቻለ አቅም በመሞከር እና ለሌሎች ተምሳሌት ለመሆን እየሠራን እንገኛለን።” ድርጅቱ በቀን እንደ ሥራው አይነት ቢለያይም ከሁለት መቶ እስከ አምስት መቶ ልብሶችን ያመርታል።

አቶ ይትባረክ ድርጅቱን ከመመሥረታቸው በፊት በእንጨት ፍልፍል ሥራ ሥራ ተቀጥረው ለሃያ አመት ሠርተዋል። የልብስ ስፌት ሙያን ለስድስት አመት በቴክስታይል፤ በጋርመንት እና በሌዘር ዲዛይን ተምረዋል። የድርጅቱ መሥራች ሥራ ሲጀምሩ በሁለት ማሽን ነበር አሁን ወደ ስድስት ማሽን ማደግ ችሏል። እንዲሁም ለሰባት ሠራተኞች የሥራ እድል ፈጥሯል።

 

ድርጅቱ ሥራዎችን የሚሠራው በዋናነት በሰው በሰው ሲሆን በመቀጠል ደግሞ ነጋዴዎች ማምረቻ ቦታ በመምጣት በሚሰጧቸው የሥራ ትዕዛዞች ነው። በተጨማሪም በባዛሮች ላይ ይሳተፋሉ። ጨረታ ላይ ለመሳተፍ ሞክረው ነበር፤ ነገር ግን የገጠማቸው ችግር በአቅራቢነት የተመዘገበ የሚለው እና ቲኦቲ ወይም ቫት ተመዝጋቢ የሚባል መስፈርት ብዙ ጨረታ ላይ እንዳይሳተፉ አድርጓቸዋል።

የኮቪድ ተፅዕኖ

ኮቪድ በጣም አስቸጋሪ ነበር። ምንም ሥራ አልነበረም። ከነበረው ችግርም የተነሳ ማሽኖችን በመሸጥ ለሠራተኞች ደምወዝ እየከፈሉ ነው ያሳለፉት አሁን ትንሽ ሥራ እየጨመረ ነው፤ ጥሩ ወደሚባል ደረጃ እየመጣ ይገኛል።

የድርጅቱ መሥራች ሥራዎችን ለማስኬድ የተለያዩ ጠቃሚ ሥልጠናዎችን ከተለያዩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ወስደዋል።

ድርጅቱ ሲመሠረት በአርባ አምስት ሺህ ብር ካፒታል ሲሆን ካፒታሉ አሁን ሦስት መቶ ሰማንያ ሺህ ብር ደርሷል። በተጨማሪም ድርጅቱ ያገኛቸው ልምዶች እና ያልፋቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎች ጥሩ ትምህርት ሆነውታል። ለምሳሌ በምሥረታ ወቅት ባለማወቅ ድርጅቱ ለገበያ ይሆናል ብሎ የሚያስበውን ነገር ማቅረብ ነበር፤ ይህ ስህተት ነበር። ገበያው ምን ይፈልጋል? የሚለውን በማጥናት መሥራት ነበረባቸው። ይህን ካስተካከሉ በኋላ የሚታይ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ችለዋል።

ድርጅቱ የሚያቀርባቸው ምርቶች ዋጋ ዝርዝር በጥቅሉ እንደሚከተለው ነው

  • የህጻን ልጅ ልብስ ከሁለት መቶ ብር ጀምሮ እስከ ስምንት መቶ ብር
  • የሴት ልብሶች ከሱቅ አምስት መቶ ብር የሚያወጣ ልብስ ድርጅቱ ጋር በመቶ ሃያ ብር መነሻ ዋጋ ማግኘት ይቻላል።

ምክር እና እቅድ

አዲስ ወደ ሥራ የሚገቡ ሰዎች የሚገቡበትን ሥራ አጥንተው አቅደው ቢገቡ ጥሩ ነው፤ ዝም ብለው ከገቡ ውጤታማ አይሆኑም። ለምሳሌ የሁለት እና የሦስት ወር ሥልጠና ወስደው ወደ ሥራ ከገቡ በጊዜ የሚመጣው እውቀቱ እና ልምዱ ስለማይኖራቸው ውጤታማ መሆን ይከብዳቸዋል።

ወደ ልብስ ስፌት ዘርፍ ለሚገቡ ሰዎች በዘርፉ በጣም በጣም ብዙ ፍላጎት አለ። ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን ነው ማኅበረሰቡ እየተጠቀመ የሚገኘው። ይህ ደግሞ ጥሩ አይደለም አንደኛ ለሃገር የውጭ ምንዛሪ ያስወጣል፤ በተጨማሪ ደግሞ ዕቃው ላይ የትራንስፖርት ዋጋ በመጨመር የምርቱ ወይም የሸቀጡ ዋጋ እንዲወደድ ያደርጋል። የአገር ምርትን ማኅበረሰቡ መጠቀም ቢጀምር ጥሩ ነው። መንግሥትም ትኩረት ቢያደርግበት ጥሩ ነው። በመጨረሻ እንደ ማሳሰቢያ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሃገር ምርት ላይ ያለው አመለካከት ቢስተካከል ጥሩ ነው ብለዋል።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …