ማቱት፣ ብዙነሽ እና ጓደኞቻቸው የሕብረት ሥራ ሽርክና ማኅበር በአቶ ማቱት ታይሉ እና በሁለት መስራች አባላት 2011 ዓ.ም ላይ ነው የተመሰረተው። የሚያምረተው ምርት የእንጀራ ምርት ነው። ማኅበሩ ሲመሰረት ከነበረው ሦስት አባላት ተነስቶ በአሁኑ ጊዜ ለስድስት ቋሚ እና ስድስት ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ እድል በመፍጠር እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
አቶ ማቱት ለምን ወደ እንጀራ ሥራ እንደገቡ ሲያስረዱ “ምግብ ሳይበላ ስለ ማይታደር” ነው። ስለዚህ የእንጀራ ሥራን አዋጭነት በማየት ወደዚህ ዘርፍ መግባታቸውን ተናግረዋል።
ምሥረታና ዕድገት
ወደዚህ ሥራ ሲገቡ አቶ ማቱት ምንም አይነት ተያያዥንነት ያለው ሙያ ወይም የሥራ ልምድ እንዳልነበራቸው ያስረዳሉ። ይሁን እንጂ ምርቱ በሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ተፈላጊ መሆኑ ወደ ሥራው በድፍረት ለመግባት እንዳስቻላቸው ጠቅሰዋል። ያለምንም የሥራ ልምድ እና መሰረታዊ ክህሎት የተጀመረው ቢዝነስ አሁን ሁለት አመት እየተጠጋ ነው። ሲጀመር በመቶ ሺህ ብር ብድር የተጀመረው ሥራ አሁን ሶስት መቶ ሺህ ብር ካፒታል እና ዐሥራ አምስት ቋሚ ደንበኞች አሉት። በወረዳው ግቢ ውስጥም ትንሽ ክበብ መክፈት በመቻሉ ማኅበረሰቡን እያገለገለ ይገኛል። ለዚህ ያበቃው ደግሞ ጠንክሮ በመሥራቱ እና ድፍረት እንደሆነ አቶ ማቱት ታይሉ ገልጸዋል።
ይህን ቢዝነስ ከመጀመራቸው በፊት እንደ እቅድ ለመሥራት አስበው የነበረው በሁለት ዘርፍ በዳቦ እና በእንጀራ ነበር፤ ነገር ግን ከጠየቁት ብድር የተፈቀደላቸው ገንዘብ አነስተኛ በመሆኑ የማኅበሩ አባላት ተሰብስበው በመነጋገር ከዳቦ እና ከእንጀራ የቱ የተሻለ (ተፈላጊ) ነው እንዲሁም የትኛው ደግሞ ብዙ ወጪ ይጠይቃል የሚለውን በመመካከር የእንጀራውን ምርት ቅድሚያ በመስጠት ቀጥሎ ደግሞ ወደ ዳቦ ለመሄድ በመስማማታቸው የእንጀራውን ሥራ ሊጀምሩ ችለዋል።
ማቱት ብዙነሽ እና ጓደኞቻቸው የሕብረት ሥራ ሽርክና ማኅበር የሚያመርተውን እንጀራ ለተለያዩ ተረካቢዎች ያቀርባል። ለምሳሌ፡- ለሱቆች፣ ለሆቴሎች ፣ ለምግብ ቤቶች እንዲሁም ለማንኛውም ተጠቃሚ ምርቱን ያቀርባል። ማኅበሩ በቀን አንድ ሺህ ሁለት መቶ እንጀራ የማምረት አቅም አለው። የአንድ እንጀራ ዋጋ ደግሞ በሰባት ብር ለደንበኛ ያቀርባል። አሁን ባለው ሁኔታ ማቱት፣ ብዙነሽ እና ጓደኖቻቸው ሕብረት ሽርክና ማኅበር ምንም አይነት የገበያ ችግር የለበትም። ከዐሥራ አምስት በላይ የጅምላ ተረካቢዎች አሉት።
ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት፣ የኮቪድ ተፅዕኖ፣ ምክር
ሥራውን ሲጀምሩ ገበያ አልነበረም ለዚህም መፍትሔ የቢዝነስ ካርድ በማዘጋጀት ለተለያዩ ተጠቃሚዎች በመበተን በአሁን ሰአት ብዙ የደንበኛ ትስስር መፍጠር ችለዋል። ሌላ ችግር የነበረው የእንጀራ አመጣጠን ማለትም ድርጅቱ ከተመሰረተ ጀምሮ እስከ ሶስት ወር ደረስ ያስቸግር ነበር ይህም ወደ ኪሳራ አምርቷቸው ነበር። መፍትሔ ብለው የውሰዱት ከነሱ በፊት በሙያው ልምድ ያላቸው ማኅበሮችን በማማከር የሚገቡትን ግብዓቶች አመጣጠን ባለማወቅ የተፈጠረውን ስህተት በማስተካከል፣ ከአሠራር ጋር የሚመጡ ችግሮችን በማረም ከሌሎች በተወሰደ ምክር ችግሩን ሊቀርፉት ችለዋል። ወደፊት የእንጀራውን ምርት አስፋፍተው የዳቦ ምርትም ለመጀመር አቅደዋል።
ኮሮና ምንም ተፅዕኖ እንዳልነበረው ገልፅው አሁን ላይ ያለው ችግር የቤት ኪራይ ብቻ ነው፤ የመሥሪያ ቦታ ችግር የሚቀረፍበት መንገድ ቢዘጋጅ ለአንድ ወር የቤት ኪራይ የሚከፈለው ሀያ ሺህ ብር ለድርጅቱ ማስፋፊያ እና ሠራተኛ በመጨመር ምርት ማሳደግ ያስችላል። ከዚህም በተጨማሪ የዋጋ ንረት በጣም አስቸጋሪ ነው።
ዘመናዊ ቴክኖጂ መጠቀም የሰው ጉልበትን ከመቀነስ እና ከጥራት ጭማሪ አንፃር የተሻለ እንደሆነ አቶ ማቶት ቢገነዘቡም ዋጋው ውድ ስለሆነ ቀስ ብለን እንገዛለን ሲሉ ገልጸዋል።
አንድ ሥራ ፈላጊ ሠራተኛ ውጤታማ ነው የሚባለው ከሥራ አጥነት ወቶ ሥራ መሥራት ሲጀምር ነው። ከዚህም ቀጥሎ በሳምንት እስከ አምስት ሺህ ብር እቁብ መጣል መቻል፣ እንዲሁም ለሌሎች ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር፣ አለፍ ሲል ደግሞ የሆነ ገንዘብ መቆጠብ ሲችል ሠራተኛው ውጤታማ ነው ማለት ይቻላል።
አንድ ቢዝነስ ውጤታማ እንዲሆን ሠራተኛ እና አሠሪ ተናቦ መሄድ አለበት፤ ያለበለዚያ አንድ ስህተት ተሰርቶ ትልቅ ኪሳራ ሊያስከትል ይችላል። ታጋሽ መሆንም እንደሚያስፈልግ አቶ ማቱት አክለዋል። አዲስ በምግብ ዝግጅት መስክ አገልግሎት ዘርፍ ለሚሰማሩ ወጣቶች ያቀረቡት ምክርም እህል የት፣ እንዴት ማግኘት እንደሚቻል፤ ሥራው የሚሠራበት ቦታ በቂ የውሃ እና የመብራት አቅርቦት እንዳለው ማየት፣ እንዲሁም የአሠራሩን አመጣጠን በደንብ አውቆ እና ተገንዝቦ ቢጀምር መልካም ነው ብለው ይመክራሉ።
በ2merkato.com የተሠራውን የ’ከፍታ’ አግልግሎት ያውቁታል በእንጀራ ብዙ ጨረታ ስለማይወጣ ወደፊት የዳቦ እና ኬክ ምርት ሲጀምሩ ለመጠቀም አቅደዋል።