በኮቪድ ተፅዕኖ ተቀዛቅዞ የነበረውን የኢንተርፕራይዞችን የገበያ ትስስር ለማሳደግ ኤግዚብሽንና ባዛር ጠቃሚ መሆኑን የአዲስ አበባ የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ገለጸ።
በ2014 አዲስ ዓመት ዋዜማ ኤግዚብሽንና ባዛር በዐሥራ አንዱም ክፍለ ከተሞች አንድ ሺህ ዐሥር ኢንተርፕራይዞች መሳተፋቸውን በቢሮው የገበያ ልማትና ግብይት ዳይሬክቶሬት ገልጿል፡፡
ከነሐሴ 24 ቀን 2013 ዓ.ም እስከ ጷጉሜ 05 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በቆየው ኤግዚብሽንና ባዛር በዐሥራ አንዱም ክፍለ ከተሞች በተፈቀዱ አደባባዮችና የመንገድ ዳርቻዎች በደማቅ ሁኔታ የተካሄደ መሆኑን በቢሮው የገበያ ልማትና ግብይት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ደበላ ተናግረዋል፡፡
ከኮንስትራክሽን ዘርፍ ውጭ ያሉ ሁሉም ዘርፎች ምርትና አገልግሎታቸውን በኤግዚብሽንና ባዛሩ ለማስተዋወቅ፣ የገበያ ትስስር ለመፍጠርና እርስ በርስ ለመተዋወቅ ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ትልቅ ጥቅም እንዳለው ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
በኮቪድ ተፅዕኖ ተቀዛቅዞ የነበረውን የኢንተርፕራይዞች የገበያ ትስስር ለማሳደግ ኤግዚብሽንና ባዛር ጠቃሚ በመሆኑ በቀጣይ ተመሳሳይ መድረኮችን በመፍጠር ለኢንተርፕራይዞች የተጠናከረ ድጋፍ እንደሚደረግ አቶ ታምሩ ጠቁመዋል፡፡ ክፍለ ከተሞች ኤግዚብሽንና ባዛር ለማዘጋጀት ዕቅድ ይዘው ስኬታማ ሥራ መሥራታቸውንና የተወሰኑት ደግሞ አመቺ ቦታ ባለማግኘት በሚፈለገው ደረጃ አለመሳካቱን በመጥቀስ በቀጣይ የሚመለከታቸው ተቋማት ተባብረው ሊሰሩ ይገባል ሲሉ አቶ ታምሩ ጠቁመዋል፡፡
የአዲስ ዓመት ዋዜማ ኤግዚብሽንና ባዛር እንዲሳካ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ማኔጅመንት እና ሌሎች ተቋማት ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን በመወጣታቸው አመስግነው በቅርቡ ጉዳዩ ከሚመለካተቸው የመንግሥት አካላት ጋር መድረክ በመፍጠር ስራውን የጋራ ለማድረግ ከፌደራል ጋር ዕቅድ መያዙን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
የዜና እና የምስል ምንጭ፦ የአዲስ አበባ የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ የፊስቡክ ገጽ