መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ኤርታሌ ማኑፋክቸሪንግ ማሽነሪ እና ግንባታ ግብዓት አምራች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር

ኤርታሌ ማኑፋክቸሪንግ ማሽነሪ እና ግንባታ ግብዓት አምራች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር

ኤርታሌ ማኑፋክቸሪንግ ማሽነሪ እና ግንባታ ግብዓት አምራች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተመሠረተው በአቶ በፍርዱ ሠይፉ እና በዐሥራ አራት አባላት 1996 ዓ.ም መጨረሻ ነበር። ይህ ማኅበር የማኑፋክቸሪንግ እና የኮንስትራክሽን ሥራዎች የሚሠራ እንዲሁም ሰላሳ የወፍጮ ማሽን ሞልዶች ለወፍጮ ድንጋይ ማምረቻ እና በጣም ዘመናዊ የብረት ማቅለጫ ያለው ድርጅት ነው። 

አቶ በፍርዱ ወደ ድርጅቱ ምሥረታ የገቡበትን ገጠመኝ እንዲህ ሲሉ ያስረዳሉ። ለጉዳይ የሥራ ልብሳቸውን ለብሰው ከጓደኛቸው ጋር ጨርቆስ ወረዳ 10 ሲሄዱ የወረዳ ሠራተኞች አይተዋቸው ቦታ፣ ገንዘብ እና ኤሌክትሪክ ስሪ ፌዝ እንስጣችሁ እና ሥራ ጀምሩ አሉዋቸው። አቶ በፍርዱም አላመኑዋቸውም ነበር እየቀለዱ ነበር የመሰላቸው በመጀመሪያ ሲቆይም በነገሩ ተስማምተው ከጓደኞቻቸው ጋር በመደዋወል ተደራጅተው ድርጅቱን መሥርተዋል።

ማስተዋወቅ እና መስፋፋት

ድርጅቱ ሥራ ሲጀምር ብረታ ብረት እና ማሽነሪ ሥራዎችን በመሥራት ነው የጀመረው።  ቀስ በቀስ እያደገ የመጀመሪያ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክት ሲጀመር ኮንክሪት ቫይቭሬተር ቴብል በመጀመሪያ የሠራ ድርጅት ነው።  የድርጅቱ መሥራቾች ትኩረታቸው የፈጠራ ሥራ ላይ ስለነበር ብዙ የፈጠራ ሥራዎችን ሠርቷል። በዚህም አቅሙን አካብቶ አንድ የስድስት ሚሊዮን ብር ሥራ አሸንፎ  ነበር። ነገር ግን ሥራው ለሌላ ሲሰጥበት አብዛኞቹ አባላት ተስፋ በመቁረጥ እንደዚህማ ከሆነ ይቅርብን ብለው ድርጅቱን ለቀው የወጡበት አጋጣሚ ነበር። በዚህም ምክንያት የቀሩት አምስት አባላት ብቻ ተስፋ ባለመቁረጥ ከቤቶች ልማት ጋር በመሆን ሥራዎችን እየሠሩ ቀስ በቀስ እያደጉ ሲመጡ፣ የኮንስትራክሽን ፈቃድ በማውጣት የብሎኬት ሥራ በመጀመር አብረው የኮንስትራክሽን ሥራዎችንም እየሠሩ ቆይተው አጋጣሚ ሲፈጠር ደግሞ ከመንገዶች ባለሥልጣን ጋር የመንገድ ሥራ መሥራት ሲጀምሩ ነው የድርጅቱ አቅም በጣም ሊያድግ የቻለው። የድርጅቱ የፈጠራ ሥራ እና አቅም እየጠነከረ በመምጣቱ ከሜቴኬም ጋር የራሱን ዲዛየን በመንደፍ ሥራዎችን ሠርቶ አስረክቧል። ድርጅቱ ሌላ አማራጭ በመጠቀም ቃሊቲ አካባቢ ያሉትን ሁለት ባለ 600 ካሜ እና 340 ካሜ ቦታ መጋዘን በማጠናከር አንዱን መጋዘን በማከራየት በአንዱ መጋዘን የወፍጮ ድንጋይ ማምረት ሥራ አጥንቶ ጀምሯል።

ድርጅቱ  ከውጭ የሚገዙ ማሽኖችን ገዝቶ ካስገባ  በኋላ በሃገር ውስጥ መተካት የሚችሉ ማሽኖችን እና ጥሬ እቃዎችን በመተካት ሥራ ጀምሯል ። ነገር ግን በዚህም የገጠሙት ብዙ ችግሮች ነበሩ። ከውጭ ሃገር በስማቸው አሳትመው የሚያስመጡ ሰዎች ስለነበሩ እናንተም ለምን እንደዚህ አታደርጉም የሚል ግፊት፤ እንዲሁም ሥራውን ጀምሮ ምርት ሲጀምር የገበያ ትስስር እና አስመጭዎቹ በፈለጉት ዋጋ ሒሳብ መቁረጥ፣ ወዘተ ለድርጅቱ ፈታኝ ሆኖበታል። ገብያውን ሰብሮ መግባት ብዙ አቅም ይጠይቃል፤ በዚህም ላይ ደግሞ አሁን የተፈጠረው የዶላር እጥረት፣ የኮቪድ ወረርሽኝ ነገሮችን በጣም ስላከበዳቸው ድርጅቱ የወፍጮ ማሽን ሥራውን ለጊዜው በመተው ወደ ኮንስትራክሽን ሥራ ፊቱን አዙሮ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

ድርጅቱ በቀን ሠላሳ የወፍጮ ድንጋዮችን ማምረት ይችላል እንዲሁም የተለያዩ የብረት ዲዛይኖችን በሚፈለገው ዲዛይን በማቅለጥ ይሠራል። ድርጅቱ ባለው በቂ መጋዘን ፣ የኤሌክትሪክ እና የውሀ አቅርቦት አማካኝነት በተሟላ መልኩ የሚመጡትን ሥራዎችን በሚገባ የመሥራት አቅም አለው። በአሁን ወቅት ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ጋር እየሠራ ይገኛል። በኮንስትራክሽን ዘርፍ ደግሞ በደረጃ አምስት የሚገኙ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል።

የድርጅቱ መስራቾች እዚህ ደረጃ ሊደርሱ የቻሉት አንደኛ በማኑፋክቸሪንግ፣ ኤሌክትሪሻንነት በነበራቸው ልምድ  እና በእድሜ እንዲሁም በሥራ በመማር ነው ይህም የዐሥራ አምስት አመት ልምድ ትልቅ አስተዋጽዖ አንዳበረከተ ገልፀዋል።  በዚህም ሥራቸው በሚገባ በማከናወናቸው ብዙ ሽልማቶችን ከተለያዩ አካላት መቀበል ችለዋል። ድርጅቱ አሁን ለዘጠኝ ቋሚ እና ከመቶ እስከ መቶ ሀምሳ ለሚደርሱ ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ እድል መፍጠር ችላል። ይህ ድርጅት በሰባ ሺህ ብር ካፒታል ተጀምሮ አሁን ሀያ ሚሊዮን ብር ካፒታል ደርሶአል፤ ለሀገሩም ትልቅ ግብር ከፋይ ድርጅት ነው።

 

 

 

 

 

 

የኮቪድ ተፅዕኖ

ኮቪድ በጣም ሥራ እንዲጓተት አድርጓል። የእቃ ዋጋ ጨምሯል፤ እንደ ልብ ተዘዋውሮ ሥራ መሥራት አይቻልም፤ ገንዘብ ይዞ ራሱ እቃ መግዛት ያልተቻለበት ወቅት ነበር። ድርጅቱ የተጠቀመው መፍትኄ በፊት ተገዝተው የተቀመጡ እቃዎችን ከመጋዘን በማውጣት መጠቀም እና ከውጭ በሚመጡ እቃዎች የሚሠሩ ሥራዎችን ቆም በማድረግ በአገር ውስጥ አቅርቦት ብቻ መሠራት የሚችሉ ሥራዎችን በመሥራት የኮቪድን ጊዜ ሊያልፍ ችሏል።

ምክር እና እቅድ

አቶ በፍርዱ የግል ሥራ ለመሥራት ያስፈልጋሉ ያሏቸውን ሀሳቦች እንደሚከተለው ጠቅሰዋል በጣም ጠንካራ መሆን አለብህ፤ ብዙ ከባድ ውጥረቶች አስጨናቂ ነገሮች አሉ እነዚህ መቋቋም እና ዓላማ ሊኖር ይገባል፤ ለፍቼ እዚህ ጋር መድረስ አለብኝ የሚል ህልም እና ቆራጥነት ግዴታ ነው። እንዲሁም በጊዜ ብዙ ነገሮችን መማር ይቻላል።  ለምሳሌ ከመንግሥት ጋር በሚሠራ ሥራ ትልቅ ልምድ ይገኛል። እንዲሁም በመንግስታዊ አካላት የሚሠጡ ስልጠናዎች ለምሳሌ ከገቢዎች፣ ከወረዳ የሚሠጡ ስልጠናዎች ትልቅ ቦታ አላችው። እንዲሁም ሁሉም ነገር በኢንተርኔት ላይ ስላለ ቴክኖሎጂ በጣም በመጠቀም እና “There is always a capable person” ስለሚባል ማማከር በጣም አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ከተግባረ ዕድ ትምሕርት ቤቶች እና ሌሎች በዘርፉ ካሉ ሰዎች መመካከር በጣም አስፈላጊ ነው።

አዲስ ወደ ሥራ የሚገቡ ሰዎች ሃያ አራት ሰዓት መሥራት አለባቸው። ኤርታሌ ማኑፋክቸሪንግ ሲጀመር ጠዋት 12 ሰዓት ገብተው ሌሊት 9 ሰዓት የሚወጡበት ጊዜ ነበር። ስለዚህ የግሌ ብሎ አንድ ሰው ሥራ ከጀመረ ቀን እና ሌሊት መሥራት፣ እውቀት፣ ጊዜ እና ገንዘብ መስጠት፤ እንዲሁም ልምድ የሚያካፍሉ ሰዎች ጋር በመሄድ በመማር ችግሮችን ማለፍ ይቻላል። እንዲሁም በሕብረት የመሥራት ልምድ በሀገራችን የለም። በጣም አስፈላጊ ነው ለምሳሌ የተለያየ አይነት ፕሮፌሽን ያላቸው ሰዎች ከተደራጁ ሌላ የውጭ ሰው ሳያስፈልጋቸው ሙሉ ሥራ መሥራት ይችላሉ።  ዓላማቸው መሆን ያለበት ገንዘብ ላይ ሳይሆን ሥራ ላይ አድርገው መጀመር አለባቸው፤ ከጊዜ በኋላ በቂ ገንዘብ ይመጣል።

ድርጅቱ ወደ ፊት በኮንስትራክሽን ሥራ ከደረጃ አምስት ወደ ደረጃ ሶስት ለማደግ እቅድ አለው። እንዲሁም ትልቅ ድርጅት በመሆን ለሃገራቸው የሆነ ቀዳዳ በመድፈን እና ብቁ የሆነ የሰው ኃይል በማፍራት ትልቅ አሻራ የማሳረፍ እቅድ አለው። ጨረታዎችን በከፍታ ቴሌግራም ቻናል በኩል ለመከታተል እና ነገሮችን ሲያስተካክሉ የkefta.2merkato.com አገልግሎትን ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም አቅዷል ።

አቶ በፍርዱ በመጀመሪያ እግዚአብሔርን፣ ቀጥሎም መንግሥትን  እና የሥራ ባልደረቦቻቸውን እንዲሁም ከፍታን አመስግነዋል።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …