መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ሳሙኤል ንጉሤ የቤት እና የቢሮ እቃዎች ማምረቻ

ሳሙኤል ንጉሤ የቤት እና የቢሮ እቃዎች ማምረቻ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ሳሙኤል ንጉሤ  በ2010 ዓ.ም. ሲሆን አጠቃላይ የቤት እና የቢሮ እቃዎችን ያመርታል።

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች ጥቂቶቹ

  • የተለያየ ዲዛይን ያላቸው ወንበሮች እና ጠረጴዛዎች
  • ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ የፋይል ካቢኔቶች
  • የተለያዩ የላተራል ሥራዎች
  • አልጋ
  • ቁምሣጥን
  • ኪችን ካቢኔት
  • በር እና መስኮቶች

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

አቶ ሳሙኤል ድርጅቱን ከመመሥረታቸው በፊት የእንጨት ሥራ በጣም ያስደስታቸው ነበር። ከፍ እያሉ ሲመጡ ሥራውን ማወቅ እንዲሁም መሥራት ይፈልጉ ነበር። በአንድ አጋጣሚም እቃዎችን ማቀበል እና አንዳንድ ቀለል ያሉ ሥራዎችን የመሥራት እድል አገኙ። ይህንንም የጀመሩትን ሥራ ቀስ በቀስ እያሳደጉ አስፈላጊውን የሥራ ልምድ በማዳበር አሥር ዓመት አሳልፈዋል። ቀጥሎም በግላቸው መሥራት የሚያስችል ደረጃ ላይ ሲደርሱ በግላቸው “ሙያዬን ሸጬ ልብላ በማለት” በዐሥር ሺህ ብር ካፒታል ሳሙኤል ንጉሤ የቤት እና የቢሮ እቃዎች አቅራቢ ድርጅትን መሥርተዋል።

ድርጅቱ በአሁን ሰዓት ለዐሥር ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ሲሆን፤ እንዲሁም የካፒታል መጠኑን ወደ ሶስት ሚሊዮን ብር ማሳደግ ችሏል። ይህም የተለያዩ ዘመናዊ ማሽኖች እና ትልልቅ ሥራዎችን መሥራት እንዳስቻለው የድርጅቱ መሥራች ተናግረዋል።

ድርጅቱ አሁን ባለው የማምረት አቅም በአንድ ሳምንት ሁለት መቶ ወንበሮች፣  በር በማምረት ደረጃ ክረምት እንደመሆኑ የሻሸመኔ እንጨት ለመድረቅ ጊዜ ስለሚፈጅ ከ 7 እስከ 10 የሚደርሱ በሮችን እና 2 ቁምሳጥኖችን በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ የማጠናቀቅ አቅም አለው።

ድርጅቱ ሥራዎችን የሚሠራው የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ሶሻል ሚዲያ ተጠቃሹ ነው። እንደ ፌስቡክ እና ቴሌግራም በመጠቀም እንዲሁም ደግሞ በሰው በሰው እና 2merkato.com ለጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ያዘጋጀውን የከፍታ አገልግሎት  በመጠቀም ጨረታ ላይ በመሳተፍ የተለያዩ ሥራዎችን መሥራት ችሏል፤ እየሠራም ይገኛል።

ከነዚህም ውስጥ፦

  • የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት
  • ሰሌክት ድርጅት
  • ጤና ሳይንስ
  • ጂሚ እና ዪኒ ለሚባሉ ድርጅቶች
  • አሁን ደግሞ ሆፕ ኢንተርፕራይዝ የሚባል ድርጅት የአንድ ሺህ አምስት መቶ ወንበሮች ጨረታ አሸንፎ እየሠራ ይገኛል።

የኮቪድ ተፅዕኖ

ድርጅቱ በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ሥራ በጣም ቀንሶ እንደነበር የድርጅቱ መሥራች ጠቅሰዋል። ለዚህም ተጠቃሹ ምክንያት አብዛኛው ሰው ቅድሚያ ይሠጥ የነበረው ለምግብ በመሆኑ እና የኑሮ መወደድ ሥራ እንዲቀንስ እንዳደረገው ጠቅሰዋል።

ምክር እና እቅድ

አቶ ሳሙኤል የግል ሥራ ላይ የሚከተለውን ተናግረዋል “የግል ሥራ ላይ የጊዜ ነጻነት የለም፤ የሥራ ትዕዛዝ የሠጠ ደንበኛ አለቃ ነው። ገንዘብ የከፈለ ሁሉ አለቃ ነው። የግል ሥራ ላይ ነገ መድረስ ያለበት ሥራ ካለ እንዴት አደርሰዋለሁ ብሎ ማሰብ፤ ማታም ወይም በእረፍት ቀን ገብቶ መሥራት እንጂ የጊዜ ነጻነት ምንም የለም። አንዳንዴ ሊሌትም አይተኛም፤ ሥራ ሊኖር ይችላል። ተቀጣሪ ከሆነ ግን የሚጠበቅበትን ሰዓት ይሠራል፤ ከዛ ወደ ራሱ ጉዳይ መሄድ ይችላል። ስለዚህ የግል ሥራ የሚጀመሩ ሰዎች  ሥራው ትልቅ ሃላፊነት እንዳለው አውቀው ቢገቡ ጥሩ ነው” ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።

ድርጅቱ ወደ ፊት የራሱን ፋብሪካ በመገንባት እና ትንሽ የሚቀሩትን ዘመናዊ ማሽኖች በማሟሟላት በሀገሪቱ ውስጥ ታዋቂ ድርጅት ለመሆን አቅዶ እየሠራ ይገኛል።

የድርጅቱን አገልግሎት መጠቀም የሚፈልጉ የድርጅቱን ስልክ በዚህ ሊንክ በመግባት ዓይተው መደወል ይችላሉ

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …