ድርጅቱ የተመሠረተው በወ/ሮ አይናለም ሀብትህ ይመር እና ሦስት ጓደኞቻቸው በ2007 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች በሦስት ዘርፎች ሲሆኑ እነሱም ዕደ ጥበብ፣ የፈርኒቸር ሥራ እና የብረት ሥራዎች ናቸው።
- በዕደ ጥበብ ሥራ ላይ የሕጻናት የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን ማለትም እንደ ፊደል፣ ቁጥሮች፣ የሚገጣጠሙ ፓዝሎች እና የተለያዩ ቅርጻ ቅርጾችን ይሠራል።
- በፈርኒቸር ሥራ ደግሞ በዋናነት የኪችን ካቢኔት፣ የምግብ ጠረጴዛ እሰከ ወንበሩ እያመረተ የሚገኝ ሲሆን ሌሎችም አጠቃላይ የእንጨት ሥራዎችን ይሠራል።
- በብረት ሥራ ደግሞ የውጪ በሮችን በጥራት እያመረተ ይገኛል።
- ድርጅቱ ከነዚህ በተጨማሪ የተለየ እገዛ ለሚያስፈልጋቸው (special needs) ሰዎች እንደ አባከስ፣ ብሬይል ቦርድ፣ መስማት ለተሳናቸው ደግሞ የምልክት ቋንቋ መግባቢያ መሣሪያዎችን ይሠራል።
ምሥረታ እና ማስፋፋት
ወ/ሮ ዐይናለም ይህን ድርጅት ከመመሥረታቸው በፊት የምሥራች ማዕከል በሚባል ግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ በዕደ ጥበብ ሙያ ሠልጥነዋል፤ ይህ ድርጅት አካል ጉዳተኞችን በተለያየ ሙያ የሚያሠለጥን ድርጅት ነው። ወ/ሮ ዐይናለም እዚህ ድርጅት ውስጥ ከሠለጠኑ በኋላ ጎበዝ ስለነበሩ በድርጅቱ ውስጥ አንድ ዘርፍ ላይ አሠልጣኝ ሆነው ሲሠሩ ቆይተዋል። ከተወነሰ ጊዜ በኋላ በራሳችን ብንሠራ ይጠቅመናል፤ አንደኛ የራሳችን ሥራ ይታወቃል፣ እኛም ማደግ እንችላለን፣ ያለን ሙያ ዘርፈ ብዙ ስለሆነ የተሻለ ውጤታማ መሆን እንችላለን፣ ራሳችንንም እንረዳለን፣ ለሌሎችም መድረስ እንችላለን በማለት ነው ድርጅቱን የመሠረቱት።
የድርጅቱ የማምረት አቅሙ ውስን ነው፤ ምክንያቱም በዚህ ዘርፍ ብዙ የተማረ የሰው ኃይል በበቂ ሁኔታ የለም። ይህ ደግሞ የድርጅቱን የማምረት አቅም ውስን አድርጎታል። ይህን ችግር ለመፍታት ድርጅቱ እየተጠቀመ ያለው መንገድ አጫጭር ሥልጠናዎችን በማዘጋጀት እና በማሠልጠን፣ ባለሙያዎችን በማውጣት ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ ነው። ይህም ጥሩ ውጤት አምጥቷል። ይህም እንዲሳካ በገንዘብ በኩል ለሠልጣኞች የኪስ እና ትራንስፖርት የሚያስፈልገውን ወጪ አንድ የተራድኦ ድርጅት ሸፍኖላቸው እነሱን አሠልጥነው በጥቂቱም ቢሆን የሰው ኃይል እጥረቱን ሊቀንሱ ችለዋል። ከሥልጠና በኋላ ደግሞ ያለው የሥራ ቦታ ሰፊ ስላልሆነ ባለሙያዎቹ የሚሠጣቸውን ሥራ በመቀበል በቤታቸው ሆነው በአግባቡ መሥራት የሚችሉበት መንገድ አመቻችቷል። ድርጅቱ በተለያዩ የቴሌቪዥን መስኮቶች ላይ የመተዋወቅ እድልንም አግኝቷል፤ ለምሳሌ ኢቲቪ፣ ፋና፣ ኢቢኤስ ተጠቃሾች ናቸው።
ድርጅቱ በአሁን ሰዓት ወደ ዐሥራ አምስት ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ከዚህም በተጨማሪ ሲመሠረት ሙያ እና ሦስት ሺህ ብር ብቻ ነበር የነበረው፤ ያለው ሙያ ላይ ጠንክሮ በመሥራቱ አሁን ላይ የካፒታል መጠኑን ወደ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ማሳደግ ችሏል። በተጨማሪም ዘመናዊ ማሽኖችንም ገዝቷል።
የድርጅቱ መሥራቾች ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ወይም አንዳንድ ነገሮች ሲፈልጉ የሚያማክሯቸው ድርጅቶች አሉ። ከዚህም በተጨማሪ ሒሳብ አያያዝ፣ የማሽኖች ጥገና እና ሌሎችም ሥራዎች ሲኖሩ ምስራቅ ፖሊቴክኒክ አጠቃላይ ኮሌጅ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርገላቸው ገልጸዋል።
የኮቪድ ተፅዕኖ
ኮቪድ ከባድ ተፅዕኖ ነበረው፤ ምክንያቱም ድርጅቱ ሥራ በብዛት ይሠራ የነበረው የክፍለ ከተማ ባዛር እና የጎልፍ ክለብ ባዛሮች ላይ በመሳተፍ እንዲሁም ትምህርት ቤቶች ላይ ነበር። ይሁንና በኮቪድ ይህ በመቆሙ በጣም ከባድ ችግር ነበር። የመጣውን ችግር የድርጅቱ በውስጡ ከያዛቸው አባላት ውስጥ የእንጨት እና የብረት ሙያ የነበራቸው ስለነበሩ ይህን ሙያ በመጠቀም የብረት እና የእንጨት ሥራዎች መሥራት በመጀመር ንዳንድ ምርቶችን በማምረት አሳልፈውታል።
ምክር እና ዕቅድ
በተለይ አካል ጉዳተኞች ሙያው ካለ ተደራጅተው መሥራት ቢችሉ ጥሩ ነው። ውጤቱ ለማየት ግን ብዙ መሥዋዕትነት ተከፍሎ የሚመጣ ነው። የገንዘብ ችግር ሊኖር ይችላል፤ የገበያ አለመኖር ሊኖር ይችላል። ስለዚህ ትዕግስት አስፈላጊ ነው። በተለይ ደግሞ አካል ጉዳተኛ ሲሆን አስቸጋሪ ነው። የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሊፍት ላይሠራ ይችላል፤ እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ እና ተግባብቶ ተነጋግሮ ተራሩጦ ነገሮችን ለማከናወን ከባድ ነው ለአካል ጉዳተኛ። ትዕግስት በጣም አስፈላጊ ነው፤ ድርጅቱ ራሱ ከተመሠረተ በኋላ ለስድስት ወር ምንም ዓይነት ሥራ ሳይሠራ ቆይቷል። በመታገሱ ነው አሁን ጥሩ ደረጃ ላይ የደረሰው።
ወ/ሮ ዓይናለም የግል ሥራ ያሉትን ጥቅሞች እንደሚከተለው ጠቅሰዋል “የአእምሮ እርካታ አለ፤ ለሌሎች የሥራ ዕድል መፍጠር ሌላው ነው። የራሳችን ሥራ ፈጠራ በራሳችን ስናስተዋውቅ (በሌላ ድርጅት ስም ሳይሆን) በጣም ጥሩ የሆነ የመንፈስ እርካታ አለው። የሥራው ባለቤት ራስ መሆን ትልቅ ጥቅም አለው” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ወደ ፊት ድርጅቱ ትልቅ ድርጅት የመሆን እና የራሱን የማሳያ ሱቅ የመክፈት እቅድ አለው። አንድንድ ሥራዎችን ወደ ዘመናዊነት ለመቀየር አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ነው። እንዲሁም ድርጅቱ ከተመሠረተ እንደመቆየቱ ቴክኖሎጂ አለመጠቀሙ በጣም እንደጎዳው ስላወቀ ወደ ፊት በደንብ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም እቅድ አለው።
የድርጅቱን አገልግሎት መጠቀም የሚፈልጉ የድርጅቱን ስልክ በዚህ ሊንክ በመግባት ዓይተው መደወል ይችላሉ።