የኋላ እሸት መኮንን የባልትና ውጤቶች ድርጅት የተመሠረተው በወ/ሮ የኋላ እሸት መኮንን መጋቢት 2012 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የባልትና ውጤቶች እና ቅመማ ቅመሞችን በጥራት የሚያቀርብ ድርጅት ነው።
ድርጅቱ የሚያቀርባቸው የባልትና ውጤቶች
- በርበሬ
- በሶ
- የአጥሚት እህል
- የገንፎ እህል
- ሚጥሚጣ እና
- ጤፍን ጨምሮ አጠቃላይ የባልትና ውጤቶች
ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት
ወ/ሮ የኋላ እሸት ይህን ድርጅት ከመመሥረታቸው በፊት በአንድ የቆዳ ውጤቶች ኤክስፖርት የሚያደርግ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው ለስምንት ዓመት ሠርተዋል። ይሁን እና የሥራው ደመወዝ ትንሽ ስለሆነ እና ተጨማሪ ክፍያቸው ከሚያመርቱት ምርት መጠን ጋር የተያያዘ ስለነበረ እና በነበረው የቆዳ ዕጥረት ምክንያት ሠራተኞች ምርት ባለማምረታቸው ክፍያው ይቀንስ ነበር። ወ/ሮ የኋላ እሸት እናታቸው የባልትና ውጤቶች ሥራ ይሠሩ ስለነበር ሙያውን ስለሚያውቁት፣ ተቀጥረው በትንሽ ክፍያ ይሠሩ የነበሩትን ሥራ ትተው ወደ የባልትና ውጤቶች ሥራ የገቡት።
ድርጅቱ ሲመሠረት ከመንግሥት ብር 140,000 (አንድ መቶ አርባ ሺሕ ብር) በመበደር ነበር ሥራ የጀመሩት። አሁን ላይ የተበደሩትን ብድር ሙሉ በሙሉ መልሰዋል፤ የድርጅቱን አቅም በማሳደግ ለዐሥራ ሦስት ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል። የድርጅቱ የካፒታል አቅም ወደ ብር 450,000 (አራት መቶ ሃምሳ ሺሕ ብር) ማደግ ችሏል። ባልው የሰው ኅይል ምርት የማምረት አቅሙ በአንድ ሳምንት እስከ አምስት መቶ ኪሎ ሲሆን ከዚህ በላይ ከታዘዘም አስፈጊውን የሰው ኅይል በመጨመር የማምረት አቅም አለው።
ድርጅቱ የሚያመርታቸውን ምርቶች በብዛት ለሱቆች ያከፋፍላል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ኤግዚቢሽን እና ባዛሮች ላይ በመሳተፍ ከሩብ ኪሎ ጀምሮ ምርቶችን አምርቶ በማዘጋጀት ይሸጣል። በባዛሮቹ ላይ ቢዝነስ ካርድ በመስጠት ምርቱን ያስተዋውቃል፤ ቢዝነስ ካርዱን ተጠቅመው ስልክ በመደወል ልደታ ፀበሉ አካባቢ በሚገኘው ሱቅ በመምጣት ሰዎች ይድርጅቱን ምርት ይገዛሉ።
የድርጅቱ መሥራች ድርጅቱን ለማሳደግ የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅመዋል። ለምሳሌ በቴክኒክ እና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት የሚዘጋጁ ሥልጠናዎችን በሚገባ ይሳተፋሉ፤ በተግባርም ይተገብራሉ። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በሥራው ላይ የብዙ ዓመት (ከ20 – 25 ዓመት) ልምድ ካላቸው ሰዎች ጋር ሃሳብ ይለዋወጣሉ፣ ልምድ ይቀስማሉ። በተጨማሪ ደግሞ ዋቤ ሸበሌ አካባቢ በሚዘጋጀው መደበኛ ባዛር በመገናኘት ብዙ ጠቃሚ መረጃዎችን እና ልምዶችን ይለዋወጣሉ። ከዚህ መካከል ቅምሻ ማዘጋጀት፣ እና ምርቱን በሩብ ኪሎ ማዘጋጀት የነኝህ ምክክሮች ውጤት ነው። ከዚህም የተነሳ አንዳንድ ሰዎች ሳምፕል በመግዛት ወደውት ስለነበር ምርቶቻቸውን ወደ ዱባይ፣ ጀርመን እና ካናዳ ድረስ የመላክ ዕድል እንዳጋጠማቸው ጠቅሰዋል።
ድርጅቱ ከተመሠረተ በኋላ ብዙ ነገሮችን በሥልጠና እና በልምድ ማሻሻል ችሏል ከነዚህም ውስጥ ተጠቃሾቹ
- ስቲከር አልነበረም አሁን ግን በሁሉም የቅመም እቃዎች ስቲከር ማዘጋጀት ጀምረዋል
- የራሱ የሆነ የፕላስቲክ መያዣ ማዘጋጀት
- የምርት አቀራረብ ላይ ያለውን ክፍተት በማጥበብ ሁሉም ምርት ጥሬ፣ የታጠበ፣ የተፈጨ፣ የተቆላ እና ሙሉ በሙሉ ሁሉንም የሂደት ደረጃ ጨርሶ የታሸገ የእህል ዓይነት በማዘጋጀት ደንበኛው የሚፈልገውን በመምረጥ መውሰድ እንዲችል ማድረግ
- ትዕዛዞችን ተጠቃሚዎች በሚፍልጉት ቦታ (ቤታቸውም ድረስ ቢሆን) ማድረስ
- ምርቶቹ በሩብ ኪሎ መጠን መዘ ጋጀታቸውብዙ ትዕዛዞችን ማግኘት እንዲችል አድርጎታል
የኮቪድ ተፅዕኖ
ድርጅቱ ወደ ሥራ እንደገባ ወዲያው ኮቪድ የገባ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ለድርጅቱ በጣም ጥሩ አጋጣሚ ነበር። ምክንያቱም ሰው እንደ ልቡ ወፍጮ ቤት ወይም ገበያ በመሄድ አይገዛም ወይም አያስፈጭም። ስለዚህ ወ/ሮ የኋላ እሸት ይህንን ክፍተት በመተካት ገዝቶ በማዘገጃት እንደ ደንበኛው ፍላጎት እቤት ድረስ ምርቱን በማቅረብ ብዙ ሥራዎችን ሠርተዋል፤ በጣም ጥሩ ገቢም አግኝተዋል። እንደውም ከኮቪድ በኋላ በዚው አሠራር የቀጠሉ ደንበኞች አሉ። “እንደውም ከነበረው አንጻር ከኮቪድ በኋላ ሥራ ቀንሷል” ሲሉ የድርጅቱ መሥራች ተናግረዋል።
ምክር እና ዕቅድ
ድርጅቱ ወደፊት ከዐምስት ዓመት በኋላ ምርቶቹን በጥሩ ሁኔታ ኤክስፖርት ማድረግ እንደሚጀምር እርግጠኛ ናቸው፤ አሁንም ከተለያዩ የውጭ አካላት ጋር አብረው ለመሥራት መነጋገር ጀምረዋል።
ወደ ባልትና ሥራ የሚገባ ሰው ከምንም በላይ ጥራት ላይ ማተኮር አለበት። ምክንያቱም አንደኛ ምግብ ስለሆነ ከሥነ ምግባር አንጻር ብትክክል መዘጋጀት አለበት፤ ሁለተኛ ደግሞ ጥራት ካለው ሰው የትም ቢሆን ራሱ ይመጣል። ምርቱ ምግብ ስለሆነ ሁሌም ይፈለጋል፤ ስለዚህ በጥራት ከተዘጋጀ ሰው ራሱ የእከሌ ምርት እኮ በጣም ጥሩ ነው እያለ ሥራ ራሱ ያመጣል። በሌላ በኩል ደግም ሥራውን ካላወቁት ይበላሽ እና ኪሣራ ያመጣል ስለዚህ ሥራውን ማወቅ እና በጥራት መሥራት አስፈላጊ ነው ሲሉ የድርጅቱ መሥራች ምክራቸውን አስተላፈዋል።