መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / አሰፋ የቆዳ ውጤቶች
assefa-leather

አሰፋ የቆዳ ውጤቶች

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ አሰፋ ሽምባጋ በ2009 ዓ.ም በግል ኢተርፕራይዝነት ነው። ይህ ድርጅት አጠቃላይ የቆዳ ውጤቶችን በጥራት በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያመርት ድርጅት ነው።

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች

  • የጀርባ ቦርሳዎች
  • የላፕቶፕ እና የዶክመንቶች መያዣ ቦርሳዎች
  • የልጆች የትምህርት ቤት ደብተር መያዣ ቦርሳዎች
  • ሳይድ ቦርሳዎች
  • ቀበቶ
  • የሴቶች ቦርሳዎች
  • የወንድ ነጠላ ጫማ

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

አቶ አሰፋ ይህን ድርጅት ከመመሥረታቸው በፊት ከሊስትሮ ሥራ ጀምሮ ብዙ ሥራዎችን ሰርተዋል። ወደ ቆዳ ሥራ የገቡበት ምክንያት ከልጅነታቸው ጀምሮ የቆዳ ሥራ ይስባቸው ስለነበር ነው፤ ይህንም ፍላታቸውን ቴክኒክ እና ሙያ ምርታማነት ኮሌጅ በመግባት አስፈላጊውን ሥልጠና ለሦስት ዓመት ሠለጠኑ። ሠልጥነው ሲጨርሱ ጎበዝ ተማሪ ስለነበሩ ከጣልያኖች ሳፍሮኮም ከሚባል ድርጅት ተጨማሪ ሥልጠና በመውሰድ ለአዲስ ተማሪዎች በአሠልጣኝነት ሥራ እየሠሩ ቆይተዋል። የሥልጠና ሥራው ሲጠናቀቅ ድርጅቱ አንድ የቆዳ ማሽን ሲገዛላቸው አሰፋ የቆዳ ውጤቶች ድርጅትን መሠረቱ።

አቶ አሰፋ ከቆዳ ሥራ ጋር በተያያዘ ራሳቸው በማስተማር አንዳንድ ሥራዎችን እና ዲዛይኖችን በመሞከር ራሳቸውን አሳድገዋል። ለሙያው ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ከተማሩት ትምህርት በተጨማሪ ራሳቸውን በራሳቸው ጥረት በማድረግ ብዙ ነገሮችን አዳብረዋል። አሁንም ባህል እና ቱሪዝም ስድስት ኪሎ እንጦጦ ኮሌጅ ጠዋት በመማር ከሰዓት ደግሞ በመሥራት ሥራቸውን ለማሳደግ እየተጉ ይገኛሉ። በተጨማሪም ለማስታወቂያ አገልግሎት አዲስ ሚዲያ፣ ብሥራት ሬድዮን ተጠቅመዋል።

ድርጅቱ ሲመሠረት በአምስት መቶ ብር መነሻ ካፒታል ሲሆን አሁን ለአራት ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል፤ ብሎም የካፒታል መጠኑን ወደ ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር በማሳደግ አሁን ላይ ያሉትን የማሽኖች ብዛት ቁጥር ወደ ሦስት አሳድጓል። ድርጅቱ በቀን ዐሥር ቦርሳዎች እና መቶ ቀበቶዎች የማምረት አቅም አለው።

ይህ ድርጅት ምርቶቹን ለገበያ የሚያቀርበው ባዛር በመጠቀም ሲሆን በአመት አራት ጊዜ በሚዘጋጁ የጥቃቅን እና አነስተኛ ድርጅቶች ባዛሮች ላይ በመሳተፍ ያመረታቸውን ምርቶች ይሸጣል። በዚህ አጋጣሚ ደግሞ ቢዝነስ ካርድ ለደንበኞች ይሠጣል፤ ይህንንም ዐይተው ጨርቆስ ማምረቻ ሼድ በመምጣት ሥራዎች የሚያሠሩ ደንበኞች አሉ። የሚመረቱት ምርቶች ጥራት ስላላቸው እና ተመጣጣኝ ስለሆኑ ባዘር ወጥተው የሚመለሱ ምርቶች ጥቂት እንደሆኑ አቶ አስፋ ተናግረዋል።

 

 

 

የድርጅቱ መሥራች እንዳንድ ነገሮችን ሲፈልጉ ሥልጠና እና ተሞክሮ ጓደኞቻቸው ጋር በመሄድ ይወስዳሉ። ይህም ችግሮች ቀድመው እንዳይፈጠሩ እና ከተፈጠሩም እንዴት መፍታት እንድሚችሉ አስተምሯቸዋል።

ድርጅቱ  የሚያመርታቸው ምርቶች ዋጋ እንደሚከተው አስቀምጧል

  • ቦርሳ፦ ከስድስት መቶ ብር ጀምሮ እስከ ዘጠኝ መቶ ብር ድረስ
  • ቀበቶ፦ ከመቶ ሠላሳ ብር ጀምሮ እስከ ሁለት መቶ ብር ድረስ
  • የወንድ የኪስ ቦርሳ፦ መቶ ሃምሳ ብር
  • የሴት ዳማ ቦርሳዎች፦ ከስምንት መቶ ብር እስከ አንድ ሺህ ብር ድረስ
  • ቁልፍ መያዣዎች፦ ከሃያ አምስት ብር እስከ ሃምሳ ብር ድረስ አምርቶ ለገበያ ያቀርባል።

ይህ ድርጅት ለማስታወቂያ አዲስ ሚዲያ፣ ብሥራት ሬድዮን ይጠቀማል።

የኮቪድ ተፅዕኖ

ኮቪድ ለድርጅቱ በጣም አስቸጋሪ የነበረ ሲሆን ሥራ ሳያቆሙ ሠራተኞችን በመቀነስ አንዳንድ ሥራዎችን በመሥራት ነው ጊዜውን ያሳለፉት። አሁን ግን ትንሽ ነገሮች እየተሻሻሉ ስለሆነ ሠራተኞች የመጨመር ሀሳብ አላቸው።

ምክር እና እቅድ

አቶ አሰፋ እንዳሉት “እንደ አጠቃላይ የቆዳ ሥራ ላይ በአሁኑ ጊዜ ያለ ችግር የአቅርቦት ችግር ነው።” ጥሬ እቃ በጣም እጥረት ከመኖሩ የተነሳ ድርጅቱ አንዳንዴ የወሰዳቸውን ሥራዎች ማጣናቀቅ ባለመቻሉ ለማቋረጥ እና ለመመለስ ተገዷል።

አቶ አሰፋ አሁን  በዚህ ሥራ ቤተሰባቸውን ያስተዳድራሉ። ሌሎች አካል ጉዳተኞችንም በመሰብሰብ እና በማሠልጠን ኑ እና ተሞክሮ ውሰዱ ሥራው እንዴት እንደሚሠራ እዩ እና እናንተም ሥሩ እያሉ ይመክራሉ፣ ያሳያሉ። በቆዳ ሥራ ላይ ውጤታማ ለመሆን አንደኛ በታዘዘው ሰዓት ሥራውን አጠናቆ ማቅረብ፣ በመቀጠል ደንበኛን ማክበር በጣም አስፈላጊ ነው። እንዲሁም ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም ሲሉ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።

ድርጅቱ ወደ ፊት ማሽኖች በመጨመር የማምረት አቅሙን ማሳደግ እና በጨረታዎች ላይ ለመሳተፍ እንዲሁም በተቻለው መጠን ጥሬ እቃ ገዝቶ የማስቀመጥ እቅድ አለው።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …