መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ታደለ ፋስት ፉድስ

ታደለ ፋስት ፉድስ

ታደለ ፋስት ፉድስ በ 2010 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ነው የተመሠረተው። ድርጅቱ ፈጣን (ቶሎ የሚደርሱ) ምግቦችን በሁለት ደቂቃ ውስጥ የሚያደርስ ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት የተለያዩ ሳንድዊቾችን ለተገልጋይ በሁለት የተለያየ መንገድ ያቀርባል፦  ምግቡን ይዞ መሄድ የሚፈልግ ይዞ ይሄዳል፤ እዛው አረፍ ብሎ መመገብ የሚፈልግ ደግሞ ይመገባል።  ታደለ ፋስት ፉድስ ፈላፈል ሳንድዊችን በአዲስ አበባ ከሚሠሩ ጥቂት የምግብ መሸጫዎች አንዱ ነው።

ድርጅቱ የሚሠራቸው ምግቦች

  • የፆም እና የፍስክ ፈላፈል
  • እስፔሻል ፈላፈል
  • አሳ ሳንድዊች

ማስተዋወቅ እና መሥፋፋት

አቶ ታደለ ገ/ዮሐንስ ምግብ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ወደ አረብ ሀገር ለሥራ ሄደው ይሠሩ ነበር። ሊቢያ በነበሩበት ወቅት የስልሳ አመት አዛውንት ጎዳና ላይ ፋስት ፉድ ሲሠሩ ከተመለከቱ በኋላ እኔም ሀገሬ ተመልሼ ይህንን ብሠራ ጥሩ ነው ብለው ሥራቸውን ትተው ከፍለው በመመለስ መስቀል አደባባይ ላይ መሥራት ጀመረዋል።

አቶ ታደለ ይህን ድርጅት ከመመስረቻቸው በፊት በኮንስትራክሽን ሥራ ነበር የተሠማሩት። ነገር ግን ለሥራ በሄዱበት ወቅት የፋስት ፉድ ምግብ አሠራር ከተመለክቱ በኋላ ሙያውን በመማር እና አንዳንድ ተያያዥ መፅሐፎችን በማንበብ ነው ሥራውን የጀመሩት። ሥራውን ሲጀምሩ የነበሩ ችግሮች ነበሩ ለምሳሌ ሕጋዊ አልነበሩም ስለዚህ ጠዋት ጠዋት ወረዳ ጽ/ቤት ነበር ጊዜያቸውን የሚያሳላፉት ከሰዓት ነው ሥራ የሚሠራው። ሌላው ችግር ደግሞ እሳቸው የሚሠሩት የሥራ ዘርፍ  በወረዳው የሥራ ዝርዝር ውስጥ ውስጥ አልነበረም፤ ይህ ራሱ አንድ ችግር ነበር። ነገር ግን አሳቸው ሲመጡ መሥራት አለብኝ ብለው ስለሆነ ወደ ሀገራቸው የመጡት፣ ሥራውን በአንድ ሳይክል ሦስት ጎማ ያላት ለማሠራት ሰላሳ ሺህ ብር ከፍለው እና ደግሞ ለውስጣዊ ግብዓት ማብሰያ፣ ሲሊንደር፣ ስቶቭ እና የመሳሰሉትን ነገሮች ለማሟላት ሰባት ሺህ ብር አጠቃላይ በሰላሳ ሰባት ሺህ ብር ነበር የጀመሩት። በአንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሥልጠናዎችን ወስደዋል፤ እውቀት አምባ ላይ ከወረዳ እና ከተለያዩ አካላት ሥልጠናዎችን ወስደዋል። በሥራው ላይ አንዳንድ ጥሩም መጥፎም አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ።  ለምሳሌ መንገድ ሲዘጋ ሰው አይኖርም ሥራም አይኖርም እንዲሁ ደግሞ በዓላት ሲኖሩ ደግሞ ጥሩ ሥራ ይኖራል ስለዚህ ሥራ ሲጠፋ ተስፋ አለመቁረጥ ሥራ ሲመጣ ደግሞ ገንዘብ አለማባከን በአግባቡ መጠቀም ጥሩ መሆኑን ይናገራሉ።

ድርጅቱ ጠንክሮ በመሥራቱ አምስት መቶ ሺህ ብር ካፒታል ሊያፈራ ችሏል። ከዚህም በተጨማሪ ለስድስት ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል መፍጠር የቻለ ድርጅት ነው። እንዲሁም አስር ሺህ አራት መቶ ብር ለመንግስት ግብር በመክፈል እና ሀገራዊ ድጋፎች ላይ በመሳተፍ የበኩሉን አስተዋጽዖ እያበረከተ ይገኛል። ድርጅቱ በአንድ ቀን ሁለት ሺህ ሰው የማስተናገድ አቅም አለው።

የሚያቀርባቸው ምግቦች በተመጣጣኝ ዋጋ ሲሆን እንደሚከተሉት አቅርቧል

ድንች ሳንድዊች  – 23 ብር
እንቁላል ሳንድዊች – 25  ብር
እስፔሻል ሳንድዊች – 33 ብር
አሳ ሳንድዊች – 27 ብር

አቶ ታደለ ጋዜጣ እና መፅሔት በመጠቀም እንዲሁም በቴሌቪዥን ምርታቸውን አስተዋውቀዋል።

የኮቪድ ተፅዕኖ

ድርጅቱ በኮሮና ወረርሽኝ በጣም ነው የተጎዳው ለስምንት ወር ኪሳራ ውስጥ ነው የገባው፤ ድርጅቱም በጣም በጥንቃቄ ቢሆንም ምግቦችን የሚያቀርበው ሰው ግን በጣም ይፈራ ነበር። ሁለተኛ ደግሞ ስታዲየም አካባቢ የእግር ኳስ ጨዋታ ስለነበር ብዙ ሰው የምግቡ ተጠቃሚ ነበር። ኮሮና ሲመጣ ግን መሰብሰብ መከልከሉ ሌላው ትልቅ በኮሮና የመጣ ችግር ነው። ደርጅቱ የሠራተኛ ደመወዝ ከቆጠበው በማውጣት እና ብድር በመበደር እየከፈለ ነው የቆየው። አሁን ላይ ትንሽ ይሻላል እየተስተካከለ ነው የተበደረውንም እዳ ዘጠና በመቶ መመለስ ችሏል።

ምክር እና እቅድ

አዲስ ወደ ዘርፉ ለሚገቡ ሰዎች የሚከተለውን መክረዋል፤ ረዳት ሆኖ በመሥራት ለ5 ወይም 6 ወራት ድረስ ሥራውን በመማር፣ ከዛም እንዴት ላዘምነው፣ ምን ልጨምርበት ብሎ በመጠየቅ የተለያዩ ነገሮችን በመጨመር ምርቱን ማሳደግ ነው። ለሥራው ዕሴት በመጨመር፣ ጉግል በማድረግ፣ አዳዲስ አሠራሮችን በመመልከት አቶ ታደለ ሥራቸውን አሳድገዋል። ስለዚህ አዲስ ወደ ሥራው የሚገቡ ሰዎች እንዲሁ እንዲያደርጉ ይመክራሉ።

ድርጅቱ አንደ አጀማመሩ ቢሆን በጣም ትልቅ ደረጃ መድረስ ይችል ነበር። ነገር ግን የኮቪድ መከሰት አሁን ባገሪቱ ውስጥ ያለው ችግር እና የዕቃዎች እጥረት፣ ሲሊንደር እና ማሸጊያ እቃዎች በቀላሉ አለመገኘታቸው እንዲሁም የሀገር ውስጥ ምርቶችም እንደልብ አለማግኘት የድርጅቱን እደገት ገትቶታል።

አቶ ታደለ ሌሎች ሰዎች ሥራውን እንዲሠሩ ይመክራሉ፤ ይህም ማኅበረሰቡን እና አገልጋዩንም እንደሚጠቅም እርግጠኛ ናቸው። በዚህ ሥራ ፋና ወጊ ናቸው፤ አሁንም ሥራው ገና አልተነካም ይላሉ።ይህ ሥራ በሌላው ዓለም ላይ በብዛት ብዙ ቦታ ላይ ተለምዶ እየተሠራበት ነው። ሀገራችን ላይ ግን የለም። አዲስ አበባ ላይ በስፋት ቢሠራ የብዙ ወጣቶችን ህይወት መቀየር ይችላል ብለዋል። በመስኩ ብዙ ገበያ አለ፤ ትንሽ ችግር ያለው የእቃ ችግር ነው ይህም ቢሆን ብዙ ሰው ሥራውን ከጀመረ እቃውን የሚያመጡ ሰዎች ስለሚኖሩ ችግሩ ይፈታል ብለዋል።

ድርጅቱ መገናኛ፣ ሜክሲኮ እና ፒያሳ ቅርንጫፎችን ለመክፈት እቅድ አለው። አሁን ያለው የጥቃቅን እና አነስተኛ ድርጅቶችን የሚመለከተው ሕግ ቅርንጫፎችን ስለመክፈት ግልጽ ስላልሆነ  ይህን ነገር ሲስተካከል ቅርንጫፎችን ለመክፈት አቅዷል። እንዲሁም በጣም ትልቅ ችግር የሆነውን የማሸጊያ እቃ ዋጋ መወደድ እና አጥረት ስለሆነ ይህን ለመቅረፍ የራሳቸውን የማሸጊያ እቃ ለማምረት በጥናት ላይ ይገኛሉ።

በከፍታ ቴሌግራም ቻናል በመጠቀም ምርታቸውን ለማስተዋወቅ እና መረጃዎችን ለመከታተል እንደሚጠቀሙበት የድርጅቱ መሥራች አቶ ታደለ ገልፅዋል።  በሬድዮ የከፍታን ማስታወቂያ ሰምተዋል።

አቶ ታደለ እግዚአብሔርን እና የመንግሥትን አካላት አመስግነዋል።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …