ድርጅቱ የተመሠረተው በ2006 ዓ.ም በአቶ ብርሃን ዲባባ እና በሁለት መሥራች አባላት ነው። ይህ ድርጅት የሚያመርታቸው ምርቶች አጠቃላይ የአልባሳት አይነቶች ናቸው።
የሚያመርታቸው ምርቶች
- የህጻናት ሱሪ እና ጃኬቶች
- የአዋቂዎች ጃኬት፣ ጋዋን፣ የደንብ ልብስ፣ ሱሪዎች
- ብዙ ዓይነት ዲዛይን ያላቸው ቲሸርቶች
- ሹራቦች እና ካፖርቶች እንዲሁም
- የዝናብ ልብሶች እና
- አጠቃላይ ከጅንስ የሚሠሩ አልባሳትን ያመርታል
ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት
አቶ ብርሃን ወደ ጋርመንት የሥራ ዘርፍ የገቡት በዘርፉ የመማር እድል አግኝተው እንደሆነ ተናግረዋል። ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ በሥራው በተለያዩ ትልቅ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው በመሥራት ስድስት ዓመታትን አሳልፈዋል። ስለ ጋርመንት ሥራ አስፈላጊውን ልምድ ከቀሰሙ በኋላ በራሳቸው ለመሥራት የሚያስችላቸውን ክህሎት በደንብ በእውቀት እና በአቅም ሲያገኙ ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በሰላሣ ሺህ ብር ካፒታል ቢ ኤም ኤች ጋርመንትን መስርተዋል።
ድርጅቱ ሲመሠረት የነበሩ መሥራች አባላት ሦስት የነበሩ ሲሆን አሁን ግን አንድ አባል በመቀነሱ በሁለት መሥራች አባላት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ይህ ድርጅት ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ብዙ ችግሮችን ቢገጥሙትም ተስፋ ባለመቁረጥ እና መፍትሔ በመፈለግ ሊያድግ ችሏል። በዚህም የካፒታል መጠኑን ወደ አስር ሚሊዮን ብር ያደረሰ ሲሆን በተጨማሪ ደግሞ አንድ ቅርንጫፍ ጀሞ ላይ በመክፈት ለሰላሣ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሮ የሚገኝ ድርጅት ነው።
ቢ ኤም ኤች ጋርመንት ሥራዎችን የሚሠራው የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ሲሆን ለአብነት ያህል የሚከተሉት መንገዶች ይጠቀማል፦ ለምሳሌ መርካቶ ካሉ ደንበኞች የሚመጡ ሥራዎች ወስዶ በማከፋፈል፣ እንዲሁም አቶ ብርሃን በፊት ሠርተው ከሚያውቋቸው ድርጅቶች ጋር በመነጋገር እና 2merkato.com ለጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ያዘጋጀውን የከፍታ አገልግሎት ተጠቅመው ጨረታ ላይ በመሳተፍ በዚህም ሁለት ጨረታዎችን ሊያሸንፉ ችለዋል። የጨረታ አገልግሎቱ የተለያዩ ጨረታዎችን በማውጣቱ በጣም ጠቅሟቸዋል፤ ይህም የተለያዩ ሥራዎችን ስለሚሞክሩ ሌሎች ሥራዎች ላይ የሚወጡ ጨረታዎች እንዲያዩ እና እንዲሳተፉ ትልቅ እድል እንደፈጠረላቸው ጠቅሰዋል።
የኮቪድ ተፅዕኖ እና ሌሎች ያጋጠሙ ችግሮች እና መፍትሔዎቻቸው
የኮቪድ ተፅዕኖ በጣም ከባድ ነበር። ሥራ ሙሉ በሙሉ ቆሞ የነበረ ሲሆን፤ ይህ ደግሞ ለሠራተኛ ደሞዝ መክፈል አስቸጋሪ አስቸጋሪ አድርጎት ነበር። ደህና የሚሠሩ ሠራተኞች ፈርተው ሲሄዱ አቶ ብርሃን ራሳቸው ሥራውን ስለሚያውቁት ከባለቤታቸው ጋር በመሆን በመሥራት ጊዜያዊ ሠራተኞች ሲያስፈልጉ ደግሞ ከቤተሰብም ከሌላም ቦታ ገንዘብ በማምጣት ቢዝነሱን በመደጎም የኮቪድን ጊዜ አልፏል። በዚህም ችግር ምክንያት በየካቲት 2012 መቶ አሥር የነበረው የሠራተኞች ቁጥር አሁን ወደ ሠላሳ አምስት ሊወርድ ችሏል።
ቢ ኤም ኤች ያጋጠመው ሌላ ችግር ደግሞ የዋጋ አለመረጋጋት እና እንደ ልብ ወደ ክልሎች አለመንቀሳቀስ፤ እንዲሁም የመርካቶ ሱቆች ሥራ ሲቀዘቅዝ ፍላጎት ማነስ ከሚጠቀሱ ችግሮች ውስጥ ናቸው። እነዚህም ችግሮች እንደ ደረጃቸው ከባለቤታቸው ጋር በመሆን እየፈቱ መጥተዋል።
ምክር እና እቅድ
አንድ አዲስ ሰው ሥራ ሲጀምር መሥራት ካለበት በላይ ጫና ፈጥሮ መሥራት መቻል እንዳለበት አስቦ እና አውቆ መሥራት አለበት። እስከሚችለው ድረስ መሥራት ሲርበው ይበላል እንጂ በምሳ ሰዓት ምሳ በሻይ እያለ የሚሠራ ከሆነ አይገፋም ሲሉ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።
ድርጅቱ ወደፊት ጨርቅ ለማምረት የሚያስፈልጉ የተለያዩ ማሽኖችን በማምጣት ፋብሪካ የመክፈት እና በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ዙሪያ ትልቅ ለውጥ የማምጣት እቅድ አለው።
“ወደ ዘርፉ ለሚገቡ ሰዎች ገንዘብ ስላላቸው ብቻ መግባት ወደ ሥራው መግባት ተገቢ አይደለም። ምክንያቱም ሥራው ሲሠራ መክበዱ አይቀርም፣ ያኔ ነገሮችን አመዛዝኖ መሥራት አስፈላጊ ይሆናል። እውቀት ከሌለ ደግሞ ኪሣራ ነው የሚመጣው። ስለዚህ ሙያው ቢኖር የሚፈጠሩ ችግሮችን እንደ ደረጃቸው ለመቅረፍ ይረዳል። እኔ ለምሣሌ ማሽን ላይ እሠራለሁ፣ እቆርጣለሁ፣ ዲዛይን አወጣለሁ፤ የኮሮና ጊዜንም በዚህ ነው ላሳልፍ የቻልኩት። ስለዚህ እውቀት በጣም አስፈላጊ ነው። ሌላው ደግሞ ያለ እውቀት ሥራ ሲጀመር መጭበርበር አለ ሥራውን ከታወቀ ግን መጭበርር አይኖርም” ሲሉ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።
የድርጅቱን አገልግሎት መጠቀም የሚፈልጉ የድርጅቱን ስልክ በዚህ ሊንክ በመግባት ዓይተው መደወል ይችላሉ።