እሸቱ እና ሣምሪ ልብስ ስፌት አገልግሎት የተመሠረተው በአቶ እሸቱ ደጉ እና በባለቤታቸው በወ/ሮ ሣምራዊት መሥራች አባልነት በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የልብስ ስፌት ሥራዎችን ይሠራል። የዚህ ድርጅት መስራቾች በልብስ ስፌት እና በፋሽን ዲዛይን ሥራ የዐሥራ ሰባት ዓመት ድምር ልምድ አላቸው።
የሚያመርታቸው ምርቶች እና የሚሠጣቸው አገልግሎቶች
- የፋሽን ዲዛይን ሥልጠና
- የልብስ ስፌት እና ዲዛይን ሥልጠና
- የማማከር አገልግሎት
- ተያያዥነት ያላቸው የማቴሪያል እቃ አቅርቦት
- የሀበሻ ልብሶች
- የራት ልብሶች
- የሙሽራ ልብስ (ቬሎ)
- የወንዶች ሙሉ ልብስ
- የሥራ ልብሶች (workwear cloth) እንደ ቱታ፣ የህክምና ባለሙያዎች ጋዋኖች፣ የአስተናጋጆች ጋዋን፣ የጥበቃ ልብሶች እና የተለያዩ ዩኒፎርሞች እንዲሁም አጠቃላይ የጋርመንት ሥራዎችን ከዲዛይን ጋር አብሮ ይሠራል።
ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት
አቶ እሸቱ ድርጅቱን ከመመሥረታቸው በፊት ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በቴክስታይል ኢንጂነሪንግ ተመርቀው ጋርመት ጥራት ቁጥጥር ላይ ለስድስት ዓመታት ሠርተዋል። ባለቤታቸውም በፋሽን ዲዛይነርነት እንዲሁ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው በፋሽን ዲዛይን ሥራ ለአምስት ዓመታት ሠርተዋል። ሁለቱም በቂ የሥራ ልምድ ስለነበራቸው በራሳችን ሠርተን እንደግ በማለት እና ኅብረተ ሰቡ በሃገሩ ምርት ኮርቶ እንዲጠቀም በማሰብ አስፈላጊውን ጥናት እና ዝግጅት አድርገው ኩል ዲዛይን ድርጅትን መሥርተዋል።
ድርጅቱ ሲመሠረት በሁለት ሠራተኞች እና ከአዲስ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ ሥራ አክሲዮን ማኅበር በብድር በወሰዱት ሁለት ማሽኖች ነበር። ድርጅቱ አሁን ሃያ ማሽኖች እና ቋሚ ዐሥራ ሶስት ሠራተኞች አሉት። አምስቱ ድርጅቱ ውስጥ ተምረው የተቀጠሩ ሲሆኑ፤ ሠላሳ ለሚደርሱ ጊዜያዊ ሠራተኞች ደግሞ (እንደ ሥራው ዓይነትና ብዛት ሊጨምር እና ሊቀንስ ቢችልም) የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
ድርጅቱ በቀን ሦስት መቶ ሸሚዞችን በጥራት፣ በሠለጠነ የሰው ኃይል እና ዘመናዊ ማሽኖችን በመጠቀም ጥራቱን በጠበቀ መልኩ የማምረት አቅም አለው። የአቶ እሸቱ በጥራት ተቆጣጣሪነት የስድስት ዓመት የሥራ ልምድ ድርጅቱ ለሚያመርታቸው ምርቶች የጥራት ደረጃ እስከ ኤክስፖርት ደረጃ የሚተካከል እንዲሆን አድርጎታል ይላሉ አቶ እሸቱ። ድርጅቱ በቀን አምስት መቶ ቱታ እና ጋዋን የማምረት አቅም አለው። ሰፋ ያለ ወይም ትልቅ ሥራ ከመጣ ደግሞ ለሌሎች ድርጅቶች በመስጠት እና ለሌሎችም የሥራ እድል በመፍጠር ሥራዎችን ይሠራል። እንደ ተጨማሪ ኢንተርፕራይዞችን የማማከር አገልግሎት፣ ሶፍት ስኪል ሥልጠና መስጠት እና ኤክስፖርት ለሚያደርጉ ድርጅቶች የምርት ጥራት ክትትል አገልግሎቶችንም ይሰጣል።
ድርጅቱ ከሠራቸው ሥራዎች መካከል፦ በ2014 ዓ.ም. የመካላከያ ዩኑፎርም ዲዛይን፤ የጨርቁ ባሕሪ (ቴክኒካል ስፔክ) ከሚለበስበት መልክኣ ምድራዊ አቀማመጥ ጋር የሚጣመር ዲዛይን፣ የክሩ ስፌት ቶሎ የማይቀደድ እና የክሩ ጥንካሬ ሁሉንም ያገናዘበ፣ ጥራት እና ውበት ባለው ዲዛይን ሠርተዋል። ለዚህም የቴክኒካል፣ ኳሊቲ እና ዲዛይን ስፔስፊኬሽን ሠርቷል። በተጨማሪም ከአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ፌደራል ፖሊስ፣ ህጻናት አድን ድርጅት (Save the Children)፣ እና ጋምቤላ ዩንቨርስቲ ጋር ሥራዎችን የሠራ ሲሆን፤ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን ደግሞ የተማሪዎች ዩኒፎርም የዲዛይን ንድፍ እና የሱፐርቫይዚንግ ሥራዎችን ሠርቷል።
ይህ ድርጅት መንግሥት የሥራ ቦታ ስለሰጠው ድርጅቱም ይገባቸዋል ብሎ የሚያስባቸውን የማኅበረ ሰብ ክፍሎች በነጻ የልብስ ስፌት እና ዲዛይን ስልጠና ይሰጣል።
የድርጅቱ መሥራች ልምድ እና መሠረታዊ ክህሎቶችን ከትምህርት በመማር እንዲሁም ከትምህርታቸው ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት ያለው ሥራ በመሥራት እና በሥራ ልምድ እና ተሞክሮዎችን አካብተዋል።
ድርጅቱ ሥራውን የሚያስተዋውቀው አንደኛ የሚመጣውን ደንበኛ ተገቢውን መስተንግዶ በመስጠት በመቀጠልም የሚሠራለትን ሥራ በጥራት በመሥራት ነው።
ኩል ዲዛይን ሥራዎችን የሚሠራው ከጅምላ አከፋፋዮች ጋር በመሆን እና ጨረታ በ2merkato.com በኩል ለጥቃቅን እና አነስተኛ ድርጅቶች በተዘጋጀው የከፍታ ፓኬጅ በመጠቀም ነው። ኩል ዲዛይን በዚህ ፓኬጅ በኩል ጨረታዎችን በጣም ይሳተፋል። በዚህም ዐሥራ አምስት ጨረታዎችን አሸንፏል።
የኮቪድ ተፅዕኖ
ኮቪድ ብዙ ችግር አምጥቶ ነበር፤ ነገር ግን የድርጅቱ መሥራቾች በመጣጣር እና አብሮ የመጣውን ጥሩ አጋጣሚ በመፈለግ ማስክ በማምረት፤ እንዲሁም ስድስት ሠራተኞችን በመያዝ ማስክ በመሥራት ለጤና ጣቢያዎች እና ለክልሎች በመላክ፤ እንዲሁም ልብስ መሠረታዊ ነገር በመሆኑ አንዳንድ የሱፍ ልብሶች፣ ለልደት እና አንዳንድ ድርጅቶች ለሠራተኞቻቸው ዩኒፎርም ስለሚፈልጉ እንዲህ ዓይነት ሥራዎችን በመሥራት እንዲሁም ሥራ ሲጠፋ ከሌሎች ድርጅቶች ሥራ በመቀበል በጣም ትንሽ በሆነ ትርፍ ሥራዎችን በመሥራት ለሠራተኞች ደመወዝ እንዲሆን በማድረግ እየሠራ አሳልፏል።
ምክር እና እቅድ
ድርጅቱ ወደ ፊት በአራት ክልል ከተሞች ትምህርት ቤት ለመክፈት እቅድ አውጥቶ እየሠራ ይገኛል።
አቶ እሸቱ ስለ ግል ሥራ (ድርጅት) የሚከተለውን ብለዋል። የራስ ሥራ ደስታን ይፈጥራል። ለሰዎች የሥራ እድል መፍጠር እነዛ ሰዎች ራሳቸውን እንዲቀይሩ አስተዋፅዖ ማድረግ ያስችላል፤ ይሄም ለሰዎቹ ደስታን ይፈጥራል። ሠራተኞች ራሳቸው ሥራውን አምነው ሲመጡ፣ ህይወት ሲመሠርቱ ይህ በጣም ያስደስታል። ልምድን ለሰው ማስተላለፍ እውቀት እንዲኖራቸው በማድረግ ቋሚ የሆነ የሥራ ዕድል መፍጠር እንዲችሉ ማድረግ ይህም ለመንግሥት፣ ለሃገር እና ለወገን ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። ለወጣቶችም አርአያ መሆን ያስችላል።
ወደ ዘርፉ የሚሠማሩ ሰዎች ሰዓት አክባሪ መሆን አለባቸው። በሥራ ቦታ መከባበር አስፈላጊ ነው። እንዲሁም ንፅህና በሚገባ መጠበቅ አለበት – የጋርመንት ሥራ እንደመሆኑ።
እንደ ተጨማሪ መንግሥት የመሸጫ ቦታ ቢያመቻች ጥሩ ነው። አንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ኢንተርፕራይዞችን ጨረታዎች ላይ ያለማሳተፍ ነገሮች ይታያሉ። ይህ ደግሞ በመመርያ የጸደቀ ስለሆነ መንግሥት ግንዛቤ ማስጨበጫ መንገዶችን አመቻችቶ ግንዛቤ ቢያስጨብጣቸው ጥሩ ነው ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።