መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / እንደ እናት እንጀራ ማከፋፈያ

እንደ እናት እንጀራ ማከፋፈያ

የተመሠረተው በወ/ሮ ኤልሻዳይ ተካልኝ በግል ኢንተርፕራይዝነት በ2012 ዓ.ም ነው። ድርጅቱ የሚያቀርበው አገልግሎት የእንጀራ ምርት አገልግሎት ነው።

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

ድርጅቱ ምርቱን

  • ለሆቴሎች
  • ለሱቆች
  • ለተለያዩ ዝግጅቶች (ደስታ፣ ሀዘን፣ ምርቃት) እና
  • ለቀጥታ ተጠቃሚዎች እንደ ፍላጎታቸው ያቀርባል

የድርጅቱ መሥራች ወደ እንጀራ የሥራ ዘርፍ ከመሠማራታቸው በፊት በተማሩበት የኢንጂነሪንግ ትምህርት ለስድስት ወር ካዲስ አበባ ውጭ ሠርተዋል። በመቀጠልም አዲስ አበባ በመመለስ የፈሳሽ ሳሙና  እንደ አሁኑ በብዛት ሳይስፋፋ በፊት በቤታቸው ከባለቤታቸው ጋር በመሆን አምርተው ለተወሰነ ጊዜ ለገበያ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ይሁና እና ለፈሳሽ ሳሙና የሚሆኑት ግብዓቶች አንዳንድ ኬሚካሎች ስለነበሩ ይህም በጣም ትልቅ ጥንቃቄ በመፈለጉ ሥራውን ትተው ሌላ ሥራ ማሰብ ጀመሩ። እንጀራ ምግብ ነክ ስለሆነ ብዙ ተጠቃሚ አለው፤ የእንጀራ ሥራ ብንሠራ ያዋጣናል የሚለውን በማጥናት ከአንድ ጓደኛቸው ጋር ስለ እንጀራ ሥራ በሚገባ ከተመካከሩ በኋላ ወደ እንጀራ ምርት ገብተዋል።

የድርጅቱ መሥራች ከድርጅቱ ምሥረታ በኋላ በመጀመርያው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብዙ አስቸጋሪ ነገሮችን አሳልፈዋል። ለምሳሌ የእህል ግብዓቶችን መጠን አለማወቅ፣ የግብዓት እና የቤት ኪራይ ዋጋ መጨመር እንዲሁም የኤሌክትሪክት ኃይል ማነስ ከነበሩት ችግሮች ተጠቃሽ ናቸው። እንዲሁም በሥራው የነበሩ ችግሮችን ሥራውን በደንብ ለማወቅ በሂደት ከልምድ እየተማሩ ነው የፈቱት። ለምሳሌ በአንድ አጋጣሚ መስተካከል የሚችል ሊጥ አገልግሎት ላይ ያለማዋል አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር። እንጀራ በተለያየ ምክንያት ሲበላሽ ወደ ቤት በመውሰድ፣ ከሠራተኞች በመማር ተስፋ ባለመቁረጥ እና በትጋት በመሥራት ነው አሁን ያለውን የጥራት ደረጃ ላይ የደረሰው።

ድርጅቱ በቀን አንድ ሺህ ስምንት መቶ እንጀራ የማምረት አቅም አለው። ፆም ሲገባ ትዕዛዝ ስለሚቀንስ ሥራ ትንሽ ይቀንሳል፤ ይሁን እንጂ የድርጅቱን የማምረት አቅም የገደበው የኤሌክትሪክ ኃይል ማነስ እና በተደጋጋሚ መቆራረጥ ነው። ይህንንም ችግር ለመቅረፍ የተለያቱ የምጣድ አይነቶችን ሞክረዋል የድርጅቱ መሥራች፤ ነገር ግን ይህ ነው የሚባል መፍትኂ ስላላገኙ አሁን የላቀች ምጣድ በመጠቀም የድርጅቱን ምርት ለማሳደግ በሂደት ላይ ናቸው። “አንዳንድ ኃይል ቆጣቢ ምጣዶች ኃይል ይቆጥባሉ ግን ምርት ላይ የሚሰጡት የእንጅራ መጠን ከተለመደው የእንጀራ መጠን በጣም ያነሰ ነው” ይህን ደግሞ የሚወስድ ሱቅ ወይም ተጠቃሚ የለም ብለዋል ወ/ሮ ኤልሻዳይ።

ኤልሻዳይ ተካልኝ የእህል አቅራቢ ድርጅት ለአንድ እንጀራ ከስምንት ብር እስከ አሥር ብር በማስከፈል ምርቱን በማቅረብ ላይ ይገኛል። እንዲሁም የጤፍ እንጀራ በብዛት ለሚፈልጉ እንደፍላጎታቸው በጥራት ያቀርባል።

ድርጅቱ የቤት ኪራይ እና የመብራት ክፍያን (ወጪ) ወደ እንጨት በማዞር የላቀች ምጣድ ለመጠቀም ወስኗል፤ ይህም የድርጅቱን ምርት በቀን በትንሹ ወደ ሁለት ሺህ እንደሚያሳድገው ጠቅሰዋል።

 

ድርጅቱ ሥራዎችን የሚሠራው በዋናነት በሰው በሰው ሲሆን በተጨማሪም  በፌስቡክ ገፅ ሥራቸውን ያስተዋውቃሉ። አሁን ደግሞ በ2merkato .com የቀረበውን የከፍታ የኢንተርፕራይዝ ፓኬጅ በመጠቀም ጨረታዎች እየተከታተሉ ጨረታዎች ላይ ይሳተፋሉ። በዚህም ጥሩ ልምድ አግኝተዋል፤ ለሚቀጥለው አስፈላጊ ልምዶችን ለማዳበር ጠቅሟቸዋል። በጨረታው ምክንያትም የቫት ተመዝጋቢ መሆን ችለዋል።

ድርጅቱ ለሦስት ሴቶች እና ለሁለት ወንዶች ጊዜያዊ እንዲሁም ለሁለት (አንድ ወንድ እና አንድ ሴት) ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል ፈጥሯል። በተጨማሪም ድርጅቱ ከዐሥር በላይ ቋሚ ደንበኞች አሉት።

የኮቪድ ተፅዕኖ

ኮቪድ ከፍተኛ ተፅዕኖ ነበረው ምክንያቱም ሰው የውጭ ምግብ መጠቀም አቁሞ ስለነበር። ወ/ሮ ኤልሻዳይ እና ባለቤታቸው በግል ሌላ ሥራ በመሥራት ራሳቸውን እና ድርጅቱን በመደጎም የኮቪድን ጊዜ አሳልፈዋል።

ምክር እና እቅድ

“ወደ እንጀራ ሥራ የሚገቡ ሥራው በጣም ትዕግስት እንደሚፈልግ አውቅው ታጋሽ መሆን አለባቸው። ሁለተኛ ደግሞ የግዴታ የሥራ ቦታ ላይ መገኘት መቻል አለባቸው። ሥራው ክትትል በጣም ይፈልጋል በተለይ መጀመሪያ አካባቢ። አዲስ ወደ ዘርፉ የሚገቡ ሰዎች ጊዜያቸውንም በሙሉ በሥራው ላይ ለማዋል ዝግጁ መሆን አለባቸው” ሲሉ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።

ድርጅቱ ከሦስት ዐመት በኋላ የእንጀራ ብቻ ሱቅ በመክፈት የታወቀ እና ጥራት ያለው እንጀራ የመሸጥ እቅድ አለው።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …