መነሻ / ፋይናንስ እና ኢንቨስትመንት / አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ አቅርቦት የሚያገኙበት ዕድል

አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ አቅርቦት የሚያገኙበት ዕድል

(ታምራት አበራ)

በኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው እየሠሩ ሥራዎን የሚያካሂዱበት ካፒታል እያጠርዎ ይቸገራሉ? ወይስ የሚሠሩበት ማሽን ኪራይ ራስ ምታት ሆኖብዎታል? ይህ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚገጥማቸው ትልቁ ችግር ነው። ይህንን ችግር ለመቅረፍ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ፋይናንስ ፕሮጀክት ነገሬ ብሎ በመሥራት ላይ ይገኛል፤ የእርስዎ ኢንተርፕራይዝ መስፈርቱን የሚያሟላ ከሆነም ከፕሮጀክቱ የፋይናንስ አቅርቦት ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

ዋነኛ የፋይናንስ ምንጭ ተደርገው የሚታሰቡት የገንዘብ ተቋማት (ባንኮች እንዲሁም የብድር እና ቁጠባ ተቋማት) በልዩ ልዩ ምክንያቶች እንዲህ ያሉ ኢንተርፕራይዞችን በበቂ መጠን እያገለገሉ አይደለም። ምክንያታቸው የኢንተርፕራይዞቹ ልዩነት ስፋትን (የመጠን፣ ፍላጎት እና አቅም ልዩነት) በተመለከተ ያለ የመረጃ ክፍተት፣ የተቋማዊ አቅም ውሱንነት፣ ለገበያው ተስማሚ የሆኑ ምርቶች እጥረት፣ ተስማሚ የብድር ሂደቶች አለመኖር እና ሌሎችንም ያካትታሉ። እነዚህ የገንዘብ ተቋማት፣ በተለይ ደግሞ የብድር እና ቁጠባ ተቋማቱ የሚያንቀሳቅሱት ጥሬ ገንዘብ በማጣት ይቸገራሉ። በዚህ ላይ፣ ከእነዚህ የገንዘብ ተቋማት አብዛኞቹ የአቅም ውሱንነትም ጭምር ስላለባቸው ለአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ብድር ለመስጠት የሚያስችል ይዞታ የላቸውም።

የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ፋይናንስ ፕሮጀክት ከገንዘብ ተቋማት ጋር በመሥራት ለአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ አቅርቦት እንዲሰጥ ያግዛል። የፕሮጀክቱ ተሳታፊ የሆኑ የፋይናንስ ተቋማት ለሥራ ማስኬጃ ካፒታል እና የካፒታል ዕቃ ኪራይ ፋይናንስ ለተመረጡ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ምድቦች ያቀርባሉ።

በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ የሥራ ዘርፎች

በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉት የሥራ ዘርፎች ከ 6 – 100 ሠራተኞች ያሏቸው እና በሚከተሉት የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ መሆን ይኖርባቸዋል፡-

  • ማኑፋክቸሪንግ
  • አግሮ ፕሮሰሲንግ
  • ቱሪዝም
  • ኮንስትራክሽን

አገልግሎት አቅራቢ ተቋማት

በአሁኑ ሰዓት፣ አሥራ ሁለት ባንኮች እና ዘጠኝ የብድር እና ቁጠባ ተቋማት የዚህ ፕሮጀክት አካል ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ የሚከተትሉት ተቋማትም ውል ፈጽመው በፕሮጀክቱ መሠረት አገልግሎት የሚያቀርቡ ናቸው፡-

የሥራ ማስኬጃ ካፒታል ብድር አቅራቢዎች

ባንኮች

  • እናት ባንክ
  • ብርሃን ባንክ
  • ሕብረት ባንክ
  • ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ
  • አባይ ባንክ

የብድር እና ቁጠባ ተቋማት

  • አዲስ ብድር እና ቁጠባ ተቋም
  • አማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋም
  • ቪዥን ፈንድ
  • ሃርቡ ማይክሮ ፋይናንስ
  • ዋሳሳ ማይክሮ ፋይናንስ

የካፒታል ዕቃዎች ኪራይ ፋይናንስ አቅራቢዎች

  • አዲስ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ አ.ማ. (አዲስ አበባ)
  • ካዛ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ አ.ማ. (ትግራይ ክልል)
  • ዋልያ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ አ.ማ. (አማራ ክልል)
  • ኦሮሚያ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ አ.ማ. (ኦሮሚያ ክልል)
  • ደቡብ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ አ.ማ. (ደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል)
  • የኢትዮጵያ ልማት ባንክ (ለጊዜው አገልግሎቱን ያቋረጠ)


ታምራት አበራ በፈርስት ኮንሰልት የፋይናንስ ጉዳይ አማካሪ ናቸው። በአሁኑ ወቅት በዓለም ባንክ በሚመራ ፕሮጀክት ላይ የሚሠሩ ሲሆን፣ ከቦሎኛ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስ አስተዳደር የማስተርስ ዲግሪ አላቸው።

ታምራት አበራን በኢሜይላቸው tamrat.amboma@gmail.com ሊያገኙዋቸው ይችላሉ።

 

ይህንንም ይመልከቱ

ቤተ-ሐበሻ ቁጠባ እና ብድር ኀላፊነቱ የተወሰነ የኅብረት ሥራ ማኅበር

ኅብረት ሥራ ማኅበር ሰዎች የጋራ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ያላቸውን ዕውቀት፣ ጉልበት፣ ጊዜ እና ሀብት በማሰባሰብ ችግሮቻቸውን …