መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ግሪን ሆፕ ሪኒወብል ኢነርጂ

ግሪን ሆፕ ሪኒወብል ኢነርጂ

ግሪን ሆፕ ሪኒወብል ኢነርጂ የተመሠረተው በ 2011 ዓ.ም በአቶ አቤል ዘርፉ እና በጓደኛቸው ነው። አረንጓዴ የታዳሽ ኃይል (Green hope Renewable Energy) የሚሠራቸው ሥራዎች በዋናነት

  • የታዳሽ ኃይል ኤሌክትሪክ አቅርቦት (Renewable Energy)
  • የሕንፃ ኤሌክትሪክ መሥመር ዝርጋታ (Building installation)
  • የተለያዩ የኤሌክትሪክ ገመዶች አቅርቦት እንዲሁም ተያያዥ ሥራዎች
  • የጥገና እና የጥሬ እቃ አቅርቦት አገልግሎት ናችወ።

አቶ አቤል ወደ ታዳሽ ኃይል አቅርቦት ሊገቡ የቻሉት የሚከተሉትን ነጥቦች በማገናዘብ ነው።

  1. 1ኛ ምክንያት የሀገራችን የኃይል አቅርቦት ማነስ አንዱ ምክንያት ሲሆን፣ ይህም ማለት ከስልሳ በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ አለመሆን እና ችግሩን ለመቅረፍ የሁሉም አካላት አስተዋጽዖ ስለሚያስፈልግ
  2. 2ኛ ምክንያት ደግሞ የድርጅቱ መሥራች አባላት ትምሕርታቸውን በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ (Electrical Engineering) ሙያ መስክ መመረቅ ለድርጅቱ መመሥረት መሠረታዊ መነሻና ጥሩ አጋጣሚ ነበር። ከዚህም ጋር በተያያዘ የጓደኛቸው በኢነርጂ ዘርፍ የተሻለ ዕውቀት እና የሥራ ልምድ ማግኘት እንዲሁም ከድርጅቱ ምሥረታ በፊት ተያያዥነት ያለው ሥራ መሥራታቸው ለድርጅቱ ምሥረታ እና እድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ካደረጉ ነገሮች ውስጥ ይመደባል።

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

ግሪን ሆፕ ሪኒወብል ኢነርጂ ምርቱን በሁለት ዓይነት መንገድ ለአገልግሎት ያቀርባል።

  • የሽያጭ አገልግሎት፦ ይህም የኤሌክትሪክ ገመድ እና አጠቃላይ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን የማቅረብ እንዲሁም የመጠገን ሥራ ነው።
  • የኢነርጂ ሽያጭ፦ ይህም በፀሐይ የሚሠራ የኤሌክትሪክ የታዳሽ ኃይል አቅርቦት ነው። ይህም አቅርቦት በተለያዩ ፓኬጆች እንዲሁም በፍሬ እና በብዛት ምርቱን በሀገሪቱ ገጠራማ ክፍል ያከፋፍላል። ድርጅቱ ከምርት አቅርቦቱ ጋር አያይዞ የታዳሽ ኃይል የጥገና አገልግሎት ይሰጣል። ይህም አገልግሎት በሶላር ኢንታሌሽን ተከላ፣ ኤሌክትሪካል ኢንስታሌሽን እንዲሁም ከፀሐይ ኃይል (Solar Energy) ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሥራዎች እና  የማማከር ሥራዎችን በማጠቃለል ይሠራል።

የድርጅቱ የፓኬጅ አቅርቦት በሁለት ይከፈላል።

  • የመብራት የግል አገልግሎት (Personal Use) እና
  • የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን በመጠቀም ተጠቃሚዎች ገቢ የሚያገኙበትን መንገድ (Productive use of Equipment) መፍጠር ነው። ይህም ፓኬጅ ገንዘብ ገቢ እያደረጉ የሚሠሩበት ነው። ለምሳሌ ሶስት አምፖል እና ሬድዮ ወይም ቴሌቪዥን የሚያጠቃልል ፓኬጅ የግል አገልግሎት ሲሆን፤ የገቢ ማግኛው መንገድ ደግሞ ቴሌቪዥን ከነዲሽ ያቀርብ እና እሱን እያሳዩ ገንዘብ ማግኘት፣ ቀለል ያሉ የመሥኖ (Irrigation) ሥራ በመሥራት፣  ስልኮች እና የፀጉር መቁረጫዎችን ቻርጅ በማድረግ  (Charging Station for Phones) እየተጠቀሙ ገንዘብ እንዲያገኙ ያደርጋል።

አቶ አቤል የቀለም ትምሕርታቸውን ጨርሰው ወደ ሥራ ዓለም ሲገቡ ቀጥታ የኤሌክትሪክ ሥራ ነበር የጀመሩት፤ ሆኖም እንዳሰቡት ሥራው ውጤታማ ስላልሆነ ይህን ሥራውን አቁመዋል። በመቀጠልም ከጓደኛቸው ጋር በመሆን ግሪን ሆፕ ሪኒወብል ኢነርጂ ድርጅት መሥርተዋል። ግሪን ሆፕ ሲመሠረት  ከነበሩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ እና ዋናው የፋይናንስ ችግር ነበር። ሌላው ደግሞ ሥራው ሲጀመር የሥራ ትሥሥሩን መፍጠር ነው። አንድ ኢንተርፕራይዝ (MSE) ለመደራጀት ሰላሳ ቀን ድረስ ሊፈጅ ይችላል በተለይ ደግሞ ክልል ላይ ከሆነ ችግሩ ከበድ ያለ ይሆናል። ሰው ማግኘት፣ ከትክክለኛ ድርጅት (Company) ጋር ተነጋግሮ ሥራ መጀመር እንዲሁም የማስታወቂያ ዕድል አለመኖር ከሚጠቀሱ ከባድ እና ቀላል ችግሮች ጥቂቶቹ ናቸው። እሳቸው እና ጓደኛቸው እንደ ችግሩ ደረጃ ቀስ በቀስ በትዕግስት እየፈቱ መምጣት ችለዋል።

ድርጅቱ ሲመሠረት የነበረው መነሻ ካፒታል ሃያ ሺህ ብር ሲሆን የድርጅቱ ካፒታል አድጎ አሁን አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ ብር ካፒታል ደርሷል።  ድርጅቱ የራሱ የሥራ ቦታ እና ዐሥራ አምስት ጊዜያዊ ሠራተኞች በመቅጠር የሥራ ዕድል ፈጥሮ እየሠራ ነው። ድርጅቱ ከተመሠረተ ሦስት ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን አቶ አቤል ግን በሥራው ከስድስት ዓመት በላይ የሥራ ልምድ አካብተዋል።

ድርጅቱ ቢዝነሱን የሚያስተዋውቀው በሶሻል ሚዲያ እንደ ቴሌግራም እና ሊንክዲን የመሠሉ መድረኮችን  (Platform) በመጠቀም ነው። ሌሎች ሶሻል ሚዲያዎችንም ለመጠቀም እቅድ አለው። የድርጅቱ ዋና መ/ቤት አዳማ ሲሆን በአዲስ አበባ ደግሞ መገናኛ አካባቢ ወኪል ቅርንጫፍ አለው።

 

 

አቶ አቤል ድርጅታቸውን እንዴት እንዳሳደጉት እንደሚከተለው አብራርተዋል፡፡ አንደኛ የራስ ሥራ መሥራት ያካበቱትን እውቀትና  ልምዶችን ያለማንም ከልካይ በደንብ እና በሚገባ ማዳበር ያስችላል፡፡  በዚህ ጊዜ የማኔጅመትን እና የሒሳብ ነክ ሥራዎችን በደንብ ለማወቅ ለሚደረግ ጥረት በቂ ጊዜ ይሰጣል። በዚህም ሂደት ራሳቸውን እና ሥራቸውን ሊያሳድጉ ችለዋል።

 

 

 

የኮቪድ ተፅዕኖ

ድርጅቱ ምርቱን የሚያቀርበው ከቦታ ቦታ (በተለይም በገጠር አካባቢ) በመንቀሳቀስ  በመሆኑ ኮቪድ በወቅቱ ትልቅ ተፅዕኖ ነበረው፡፡  ይህም ስለሆነ የእንቅስቃሴዎች መታገድ እና የማኅበረሰቡ ግንዛቤ በበቂ ሁኔታ አለመኖር ሥራው ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ነበረው። እንዲሁም ከውጭም ሀገር የሚመጣ እቃ ሙሉ በሙሉ በመቆሙ ምክንያት ለስድስት ወር ሥራ ቆሞ ነበር።ይ ሁን እና በኮቪድ ጊዜ ዝም ብለው አልተቀመጡም የሬድዮ ፕላትፎርም እና የተለያዩ አዳዲስ እቅዶችን በማዘጋጀት ኮቪድ ካለፈ በኋላ ወደ ሥራ የገቡ እና ወደ ሥራ የሚገቡ እቅዶችን መቅረጽ ችለዋል።

 


ከምርቶቹ መካከል

  • ብር 37,500  ዋጋ የሚያወጣ የቴሌቭዥን እና ሃያ አራት አምፖል የማብራት አቅም ያለው ሶላር ፓናል።
  • ብር 30,000 ዋጋ የሚያወጣ  ገደግሞ 14 ኢንች ቴሌቭዥን እና ዐሥር ስልኮችን የማስጠቀም አቅም ያለው ሶላር ፓናል።
  • የሶላር ፓናሎች መትከል እና መጠገን እንዲሁም ከነሙሉ እቃቸው ማቅረብ።

ምክር እና እቅድ

ድርጅቱ ከሁለት ዓመት በኋላ የተሻለ ድርጅት የመሆን እና ለቋሚ ሠራተኞች የሥራ እድል መፍጠር እና ኮርፖሬት ቢዝነስ መሆን ነው የሚያስቡት፣ ከዐሥር አመት በኋላ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የታዳሽ ሀይል ቢዝነሶች ዋነኛ መሆን ራዕይ አላቸው።

አንድ ሰው ማንኛውንም ሥራ ለመሥራት ጫናዎችን መቋቋም መቻል አለበት፣ በመቀጠል ደግሞ ትዕግስት ያስፈልጋል። በሥራ ሂደት ላይ የሚፈጠሩ ችግሮች ምክንያት ከመጨነቅ ወደ መፍትሔ መሄድ አለባቸው። ቀጥሎ ሥራውን ማክበር እና ደንበኛን ማክበር ያስፈልጋል፤ ሥራንና ደንበኛን ካላከበረ ምንም ዓይነት ተፈላጊ ሥራ ቢሠራ ደንበኛ አይመጣም፤ ገቢ ማግኝትና ማደግ አይቻልም።

ግሪን ሆፕ ሪኒወብል ኢነርጂ በከፍታ አገልግሎት ጨረታዎችን ይከታተላል፣ እንዲሁም ከሌሎች ድርጅቶች ጋር የፓርትነርሺፕ ጥምረት በመፍጠር ቴክኒካል ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል። ስለ ድርጅቱ የበለጠ መረጃ ለማግኘት በከፍታ ፓኬጅ አማካኝነት ያገኘውን ለገበያ ትስስር አስፈላጊ የሆነውን ፕሮፋይሉን የተለጠፈበትን ፕላፎርም በዚህ ሊንክ ይመልከቱ

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …