ድርጅቱ በጥቃቅን እና አነስተኛ ማኅበር በግለሰብ ደረጃ ተደራጅቶ ሥራ የጀመረው በ2009 ዓ.ም በአቶ ለማ መሥራችነት ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የባሕላዊ እቃዎችን በጥራት በማምረት ለገበያ ያቀርባል። ምርቱንም ሽሮሜዳ፣ ፖስታ ቤት እና መርካቶ አካባቢ በአዲስ አበባ እንዲሁም በክልል ከተሞች ደግሞ በባሕር ዳር፣ ሻሸመኔ እና ናዝሬት ለተረካቢዎች ያቀርባል። ድርጅቱ ከሌሎች የባህል ጌጣጌጥ አምራቾች የሚለየው ምርቱን እራሱ ማምረቱ፣ በራሱ የማሳያ ሱቅ በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረቡ እና ዋስትና መስጠቱ ነው።
ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች
- ትልቅ እና ትንሽ የባህል ጌጣጌጦች
- ባህላዊ አልባሳት
- ባህላዊ ከበሮዎች
- የሥዕል ሥራዎች
- የቆዳ ሥራዎች
- የእንጨት ፍልፍል ቅርፃቅርፆች
- የተለያዩ የባህላዊ ኮፍያዎች እንዲሁም የእጅ፣ የእግር፣ የአንገት እና ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ ጌጣጌጦችን ያመርታል።
ምሥረታ እና ዕድገት
አቶ ለማ በጥቃቅን እና አነስተኛ ተደራጅተው መሥራት ከመጀመራቸው በፊት ለዐሥር ዓመታት በሙያው በግላቸው ሲሠሩ ቆይተዋል። በፊት ይሠሩት የነበረው ሥራ ከክፍለ ሀገር ጦስኝ የሚባል ተክል ለሻይ እና ለበርበሬ አገልግሎት የሚሆን እንዲሁም ቅመማ ቅመሞችን እና ሳሳ ያሉ የቀርከሀ ዝምድና ካላቸው ዕፅዋት የሚሠሩ ቀለል ያሉ ባህላዊ እቃዎችን በመሥራት እና በአዲስ አበባ የተለያየ ቦታ በመንቀሳቀስ ይሸጡ ነበር።
ምርታቸውን ጠዋት በመነሳት ልደታ፣ ቦሌ፣ ካዛንችስ፣ ፒያሳ፣ መገናኛ፣ አራት ኪሎ፣ ለገሀር፣ ስታዲየም እና ብሔራዊ በመሄድ ይሸጡ ነበር። በዚህ ወቅት እሳቸው የባህላዊ ጌጣጌጦች አድናቂ ስለነበሩ እየገዙ ያጌጡ ነበር። ጌጣ ጌጦቹን አድርገው በመዲናዋ ሲንቀሳቀሱ ብዙ ሰዎችን የማግኘት አድል ፈጥሮላቸዋል። የሚያገኙዋቸውም ሰዎች ልብሱን ከየት ገዛህው?አ ለህ ወይ? የአንገት ሀብሉን ከየት ገዛህው? እያሉ ይጠይቋቸው ነበር። በዚህ ጊዜ ነበር እንደኔ የባህል ሥራ የሚወድ እና የሚያደንቅ ብዙ ሰው አለ ብለው በማሰብ እኔም እንዴት መሥራት እችላለሁ? እቃውን የት አገኛለሁ? የሚሉትን ጥያቄዎች በደንብ አስበው ካጠኑ በኋላ መርካቶ በመሄድ አቅማቸው በፈቀደው ጥሬ እቃ በመሸመት የእጅ ጌጥ መሥራት የጀመሩት በዚህ ሁኔታ ላይ ሁለት እና ሦስት ቀን ሳይተኙ ሲሠሩ የቆዩባቸው ሌሊቶች እንደበሩ ያስታውሳሉ። ከዚያም የሠሩትን ከሌሎቹ ምርቶቻቸው ጋር አብረው በመያዝ መሸጥ ጀመሩ። ከጊዜ በኋላ የጌጣጌጡ ሥራ ተፈላጊነት እየጨመረ ሲመጣ ቀስ በቀስ የጌጣጌጡን ሥራ እየጨመሩ የቅመማቅመም ሥራውን እና የቀርከሀውን እየቀነሱ ሙሉ በሙሉ ወደ ባህል ጌጣጌጥ ሥራ ተሰማርተዋል።
ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት
ድርጅቱ ሲጀመር ነገሮች አልጋ ባልጋ አልነበሩም ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎችን አሳልፈዋል። ሥራውን ሲጀምሩ ቋሚ የሆነ የምርት ማሳያ እና የማምረቻ ቦታ ስላልነበር የሚያመርቱትን ምርቶች በእጃቸው በመያዝ በመንቀሳቀስ ነበር ለገበያ የሚያቀርቡት። ይህም ምርቱ በፀሀይ እና በዝናብ በቀላሉ እንዲበላሽ አድርጎታል። ከዚህም የተነሳ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ሆኖም ትጋት በመጨመርና በትዕግስት አስቸጋሪውን ጊዜና ሁኔታ ተቋቁመውታል። አቶ ለማ ብዙ ጊዜ ምርታቸውን የሚሸጡት የተሻለ ገቢ በሚያገኙበት ብሔራዊ ቲያትር ቤት አካባቢ በመሆኑ ሌላ ቦታ መንቀሳቀስ በመተው ብሔራዊ አካባቢ ብቻ መሸጥን አጠናክረዋል። ብሔራዊ አካባቢ ቋሚ ቦታ ካገኙ በኋላ ቦታው ጣራ ስለሌለው እቃዎቻቸውን ጧት ከቤት ወደ ሥራ ቦታ ማታ ደግሞ ወደ ቤት በመውሰድ ሲሠሩ ቆይተው አንደ ቅን ግለሰብ ሺህ ሰለሞን አካባቢ እቃ ማስቀመጫ ሲተባበራቸው ከቤት ማምጣቱ ቀርቶ ጧት በማውጣት ማታ እያስገቡ ሲሠሩ ቆይተዋል። እቃው ሲወጣና ሲገባ እንግልቱ እና ፀሐዩ እና ዝናቡ በዓመቱ መጨረሻ ብዙ ምርት ተበላሽቶ ኪሳራ ያስከትል ነበር። ነገር ግን ተስፋ ባለመቁረጥ ቀስ በቀስ ገበያው እያደገ አሁን ሁለት መቶ ሺህ ብር ካፒታል እና ለአራት ቋሚ ሠራተኞች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል። “የምርት ማሳያ ሱቅ አለመኖር ኪሳራ ያስከትል የነበረ ሲሆን ከዚህም የተነሳ ሁለት እና ሶስት ማዳበሪያ ተበላሽቶ ከሥራ ውጭ ይሆን ነበር። አሁን ግን እግዚአብሔር ይመስገን ባገኘነው የማሳያ ሱቅ ምክንያት የምርት ብልሽት ተወግዷል” ብለዋል የድርጅቱ መሥራች።
ድርጅቱ ሲመሠረት ምርት የሚያመርተው ካዛንችስ አካባቢ ነበር። የድርጅቱ አሠራር ሠራተኞች ሥራውን በደንብ እስከሚችሉት ድረስ ወርክሾፕ ላይ በመጠነኛ ደመወዝ ሲሠሩ ይቆዩና ሥራውን ሲችሉ ደግሞ በሠሩት ሥራ ክፍያ የሚፈጸምበት አሠራር እንዳለ ተናግረዋል። ይህ ደግሞ ድርጅቱንም ሠራተኞቱንም ተጠቃሚ አድርጓል። በዚህ ሂደት የባህል ሙያን በማስተማር የዜጎችን ሥራ አጥነትን ችግር በመቀነስ የበኩሉን አስተዋጽዖ በማበርከት በጣም ብዙ ባለሙያዎችን ድርጅቱ ሊያፈራ ችሏል። የወርክሾፕ ኪራይ ሲጨምር ደግሞ ጀሞ ፉሪ አካባቢ የወርክ ሾፕ ቦታ በመቀየር የኮቪድ ወረርሽኝ እስከሚከሰት ሲሠራ ቆይቷል።በዘርፉ ልምድ እና ተሞክሮ ያላቸው አምራቾች ባለመኖራቸው ድርጅቱ የሚገጥሙትን ችግሮች በራሱ እየሞከረ እና ከችግሩና ስሕተቱ እየተማረ እንዲሁም ከልምዱ ሌሎችን እያስተማረ ብዙ ብቁ ባለሙያዎችን መፍጠር ችሏል።
ድርጅቱ ምርቱን የሚያስተዋውቀው በቢዝነስ ካርድ ሲሆን እንዲሁም በሬድዮ እና በቴሌቭዥን እንዲሁም ከውጭ ሚዲያዎች ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ ለሥራው ትልቅ እሴት እና እውቅና አበርክቶለታል።
የኮቪድ ተፅዕኖ
በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ወደ አገር ውስጥ የሚመጡ ቱሪስቶች ቁጥር መቀነስ እና መቆም በዚህም ሥራው በጣም በመቀዝቀዙ ተፅዕኖው ከባድ ነበር። ድርጅቱ ለአምስት ወራት ያህል በመዘጋቱ ሥራው በጣም ከባድ ኪሳራ ውስጥ ገብቶ ነበር፤ አቶ ለማ ከወንድማቸው ገንዘብ በመበደር እንደገና ሊያሰቀጥሉት ችለዋል። ድርጅቱ ነገሮች ሲሻሻሉ ሠራተኞች ለሥራ መሥሪያ የሚያስፈልጉ የጥሬ እቃዎችን አቅርቦት በማቅረብ ሠራተኞች በቤታቸው ሆነው ሥራቸውን እንዲቀጥሉ አድርጓል።
ምክር እናእቅድ
የድርጅቱ የወደ ፊት እቅድ ቅርንጫፎችን በላሊበላ፣ ጎንደር፣ ባሕር ዳር፣ ሻሸመኔ፣ አዋሳ፣ አዳማ (ናዝሬት)፣ እና ጎርጎራ በመክፈት ለማስፋፋት እና ትልቅ የኢትዮጵያን ሙሉ ባህል የሚያሳይ ዓለም ዓቀፍ ሙዚየም ለመክፈት እና አንዳንድ ለሥራው የሚያስፈልጉ ከውጭ የሚመጡ የጥሬ እቃ አቅርቦቶችን በአገር ውስጥ እንዲመረቱ ማድረግ ነው።
አዲስ ወደ ሥራው የሚገቡ ሰዎች ቅድሚያ ተሰጥኦ ሊኖራቸው ይገባል። “ሥራውን ከወደዱት ትልቅ ገንዘብ ባላገኝበት እንኳን ይህን ሥራ ብሠራ ደስ ይለኛል ብለው ቢገቡ እና በትዕግሥት ወደ ውጤት ለመድረስ የሚያስችል ነው በማለት ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ይችላሉ” ሲሉ መክረዋል።
ምርታቸውን ለማስተዋወቅ እና መረጃዎችን ለመከታተል ካሁን በሁዋላ በ2merkato.com ለጥቃቅን እና አነስተኛ ድርጅቶች የተዘጋጀውን የከፍታ ፖርታልን የቴሌግራም ቻናል እንደሚጠቀሙበት ገልፀዋል።