መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / መንሽ የግብርና ማሺነሪ፣ መሣርያዎች ሌሎች የብረት ሥራዎች

መንሽ የግብርና ማሺነሪ፣ መሣርያዎች ሌሎች የብረት ሥራዎች

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ውብሸት ደለለኝ እና በጓደኞቻቸው በ2002 ዓ.ም. ነው። የጤፍ መውቂያ ማሽን በዋናነት የሚያመርተው ምርት ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ የእርሻ መሣሪያዎ ች(የግብርና መሣርያዎች)፣ የውሃ መሳቢያ እና መቆፈሪያዎች፣ የባዮ ጋዝ ምድጃዎች እና ማብላያዎች፣ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች እና ለትምህርት ቤት እና ለቢሮ የሚሆኑ የፈርኒቸር ምርቶችንም ያመርታል።

የሚያመርታቸው ምርቶች በዋናነት ሦስት ሲሆኑ፣ እነዚህም፦

 1. የእርሻ መሣሪያዎች (የግብርና ማሽኖች)
 2. የኮንስትራክሽን ማሽኖች
 3. የትምህርት ቤት እና የቢሮ ፈርኒቸሮች ናቸው

 

 

 

 

 

 1. የእርሻ መሣሪያዎች (የግብርና ማሽኖች)
 • ሁለገብ የእህል መውቂያ ማሽን(ስንዴ፣ ጤፍ፣ ማሽላ፣ ዳጉሳ እና ሩዝ)
 • የበቆሎ መፈልፈያ ማሽን
 • የእንስሳት መኖ ማቀነበባሪያ ማሽን (መፍጫ እና መደባለቂያ)
 • የተለያዩ የወፍጮ ማሽኖች
 • አኩሪ አተር መውቂያ ማሽን
 • የዶሮ ቤት
 • የወተት መናጫ፣ የማር ማጣርያ  እና መጭመቂያ
 • የጉሎ መፈልፈያ
 • የጤፍ መዝርያ
 • የሩዝ መፈልፈያና መፈተጊያ

2. የኮንስትራክሽን ማሽኖች

 • ጠጠር እና አሸዋ ማጠቢያ ማሽን
 • ጋሪ
 • የብሎኬት ማምረቻ ማሽን
 • የእምነበረድ፣ የድንጋይ መቁረጫ እና መፍጫ ማሽን
 • ለኮንስትራክሽን ሥራ የሚሆኑ ደረጃዎች እና የኮንስትራክሽን መወጣጫዎ ች(Scaffolding)
 • ለክብ የኮንክሪት ቱቦ ማውጫ የሚያገለግሉ ሞልዶች (Concrete pipe ring molds)

3. የትምህርት ቤት እና የቢሮ ፈርኒቸሮች እንዲሁም ሌሎች ማሽኖች

 • የተለያዩ በእንስሳት የሚጎተቱ ጋሪዎች (Animal drawn cart)
 • የተማሪዎችየመቀመጫ ወንበሮች
 • ጠረጴዛ
 • የተማሪዎች መማሪያ ጥቁር ሰሌዳ
 • የሥዕል መሳያ ጠረጴዛ
 • የብረታ ብረት ሥራዎች
 • ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ሼልፎች፣ ጠረጴዛ እና ወንበሮች
 • የከንች ሥራ እንዲሁም እንደ ደንበኛው ፍላጎት እና ሃሳብ የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራል።

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

አቶ ውብሸት ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የገቡት የተማሩት ትምህርት ጄኔራል ሜካኒክስ በመሆኑ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ በዘርፉ ተቀጥረው የተለያዩ የማሽን ፈጠራ ሥራዎችን በመሥራት ስድስት ዓመት አሳልፈዋል። በቂ ልምድ እና ተሞክሮ ከቀሠሙ በኋላ በግል ሥራ እንዲጀምሩ ካደረጋቸው አጋጣሚዎችን አንዱ ይሠሩት የነበረው የጤፍ መውቂያ ማሽን ማበጠሪያ አልነበረውም።  ስለዚህ ይህን የተሻለ አድርጌ መሥራት እችላለሁ፤ ለዚህ ደግሞ በቂ ዕውቀት አለኝ፤ ስለዚህ ይህን ማሽን ማበጠሪያ ብገጥምለት ለገበሬው ሥራ ያቀላል በማለት የመጀመሪያ ማሽናቸውን ሠሩ። ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የሀገራችንን ግብርና ኋላ ቀር ስለሆነ ዘመናዊ ማሽኖችን ብንሠራ እኛም፣ ገበሬውም፤ ሀገራችንም ተጠቃሚ እንሆናለን በማለት ድርጅታቸውን መሠረቱ። ድርጅቱ በዐሥር መሥራች አባላት ተመሥርቶ አሁን በሦስት መሥራች አባላት እየንቀሳቀሰ ይገኛል።

ድርጅቱ በሂደት የጤፍ መሙቂያ ማሽን የፓተንት ሰርተፍኬት ተቀብሏል። ቀስ በቀስ ሌሎች ማሽኖችን በማምረት እና የተለያዩ ሀሳቦችን ከገበሬው እና ከተለያዩ አካላት በመቀበል በዓይነት እና በብዛት ጠርቀም ያሉ ማሽኖችን ማምረት ችሏል። ለዚህም ስድስት ተጨማሪ የፓተንት ሰርተፍኬቶችን ተቀብሏል።

ድርጅቱ አሁን ያለው የማምረት አቅም እንደ ማሽኑ ዓይነት፣ ጥሬ እቃ አቅርቦት እና ሌሎችም ነገሮች ታሳቢ በማድረግ የሚወሰን ነው። ለምሳሌ ግን አንድ ሁለገብ የእህል መውቂያ ማሽን ማለትም ጤፍ፣ ስንዴ፣ ማሽላ እና ሩዝ መፈልፈል እና መውቃት የሚችል ማሽን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እስከ መቶ ማሽኖች የመሥራት አቅም አለው። ይሄንንም ማምረት የሚችለው ሌሎች ተጓዳኛ ሥራዎችን  ለምሳሌ እንደፈርኒቸር የመሳሰሉ ቀለል ያሉ ሥራዎችን ዐብሮ እየሠራ ነው።

የድርጅቱ መሥራች የድርጅቱን ሥራ ለማሳደግ እና ለማስፋት የተለያዩ አቅጣጫዎችን ተጠቅመዋል። ለምሳሌ የተለያዩ ሥልጠናዎችን በከስተመር ሰርቪስ እና ማኔጅመንት እና በዲዛይን፣ እንዲሁም ሌሎች ልምዶችን ከሌሎች ሰዎችን ጋር በመለዋወጥ፣ በተጨማሪም ኤግዚብሽን እና ባዛሮች ላይ በመሳተፍ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ያሉትን አምራቾች በማየት ብዙ ነገሮችን ተምረዋል። ምርታቸውንም በሀገር እና በውጭ ሀገር ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚችልበት መንገዶችን በማወቅ እያሻሽሉ እንዲመጡ እና እንዲያሳድጉ አድርጓቸዋል።

ድርጅቱን ምርቱን ካቀረበባቸው ድርጅቶች መካከል

 • ፋኦ (FAO / Food and agricultural Organization)
 • ህፃናት አድን ድርጅት (Save the Children)
 • ዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል (ICRC / International Red Cross Ethiopia)
 • ኤቲኤ (Agricultural Transformation Agency)
 • ወርልድ ቪዥን (World Vision Ethiopia)
 • ኤስኤንቪ (SNV) – በአዲስ አበባ እና በባሕር ዳር
 • ኤስ ጂ 2000 (SG 2000) እና
 • የተለያዩ የመንግስት ቢሮዎች፣

በተጨማሪም ምርቱን ቀጥታ ለገበሬዎች ያቀርባል።

ድርጅቱ ሥራዎችን የሚያስተዋውቀው እና የሚሠራው በአዲስ አበባ እና በክልሎች በሚዘጋጁ ኤግዚቢሽኖች እና ሌሎች በሚዘጋጁ መድረኮች ላይ በመሳተፍ ነው። እንዲሁም በሰው በሰው ብዙ ይሠራል፤ ብዙ ሥራው ቀጥታ ከገበሬዎችን ጋር ስለሆነ እነሱ ራሳቸው ገበሬዎቹ ናቸው የማስተዋወቅ ሥራውን የሚሠሩት። በተጨማሪ ደግሞ ጨረታዎችን ላይ በመሳተፍ ሃያ የሚደርሱ ጨረታዎችን አሸንፎ ሥራንው ሠርቶ አስረክቧዋ።

ድርጅቱ አሁን ባለው አቅም ሃያ ለሚደርሱ ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል መፍጠር የቻለ ሲሆን በተጨማሪ ደግሞ ለአምስት ዜጎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ይህ ድርጅት ሲመሠረት የነበረው መነሻ ካፒታል ሃምሳ ሺህ ብር ሲሆን አሁን ካፒታሉ ሰባት ሚሊዮን ብር ደርሷል።

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ማሽኖች ዋጋ

 • የጤፍ መውቂያ ማሽን እስከ ብር 120,000 (አንድ መቶ ሃያ ሺህ ብር)
 • የበቆሎ መፈልፈያ ማሽን እንደ ዓይነቱ ቢለያይም እስከ ብር 95,000 (ዘጠና አምስት ሺህ ብር)

የኮቪድ ተፅዕኖ

በኮቪድ ጊዜ የነበረው ሁኔታ በጣም ከባድ በመሆኑ ሠራተኞችን ለመቀነስ ተገዶ ነበር። ምክንያቱም ገበያው በጣም በመቀነሱ፣ ለጥንቃቄም እንዲመች እና ከወጪም አንፃር ለማመጣጠን እንዲያመች ነው። ይሄን በማድረግ ነበር የኮቪድን ጊዜ ያለፉት።

ምክር

አቶ ውብሸት አዲስ ወደ ዘርፉ ለሚገቡ ሰዎች “ዕውቅት ያስፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ሰዎች መሆን አለባቸው። ሁለቱ ሥራውን ለመጀር የሚያስፈልጉ ሲሆኑ በሥራው ሂደት ውስጥ ደግሞ ትዕግስት አስፈላጊ ነው። ማሽኑ ተሰርቶ ሲያልቅ የሆነ ችግር ቢፈጠር በትዕግስት ማለፍ እና መፍትሔ መፍጠር የሚችሉ መሆን አለባቸው” ሲሉ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።

አቶ ውብሸት በተጨማሪም “ድርጅቱ የእርሻ መሣሪያ አምራች እንደመሆኑ፣ ይህም ለሀገራችን ግብርና እድገት ትልቅ አስተዋፅዖ ስለሚያበረክት፣ መንግስት ድጋፍ ቢያደርግ ጥሩ ነው። ይህም ከውጭ የሚመጣ ምርትን በማስቀረት ብዙ የውጭ ምንዛሬ ወጪን ማስቀረት ይችላል።” ብለው ሀሳባቸውን አካፍለዋል።

የድርጅቱን አገልግሎት መጠቀም የሚፈልጉ የድርጅቱን ስልክ በዚህ ሊንክ በመግባት ዓይተው መደወል ይችላሉ

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …