ኒዮ የውሃ ሥራዎች የተመሠረተው በአቶ ጀማል አብዱልጀባር እና በሦስት መሥራች አባላት በ2006 ዓ.ም. ነው። ኒዮ የውሃ ሥራዎች አጠቃላይ የውሃ ሥራዎች የሚሠራ ድርጅት ሲሆን በሰብ ኮንትራት ደግሞ የኮንስትራክሽን ሥራዎችን ይሠራል።
ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት
አቶ ጀማል አብዱልጀባር ድርጅቱን ከመመሥረታቸው በፊት ለአንድ ዓመት በውሃ ሥራ ላይ ተቀጥረው ሠርተዋል። በዚህ ወቅት እንደ እሳቸው ተመሳሳይ የሥራ መስክ ላይ የተሰማሩ ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን “ለምን በራሳችን አንሠራም? የተማርነው ትምህርት ዋተር ሰፕላይ እና ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት በመሆኑ እና ሥራውን ስለምናውቀው እስቲ እንሞክረው” በማለት ድርጅቱን መሥርተዋል።
ከድርጅቱ ምሥረታ በኋላ የተወሰኑ ሥራዎችን እንደሠሩ ነገሮች በጣም አስቸጋሪ በመሆናቸው የድርጅቱን ሥራ ገታ በማድረግ ሁሉም አባላት ወደ ሌሎች ሥራዎች ይገባሉ። ትንሽ ቆይተው ሁኔታዎች እንደ ተሻሻሉ በድጋሚ በ 2011 ዓ.ም. ላይ መልሶ በማቋቋም ወደ ሥራ ገብተዋል። ድርጅቱን እንደ አዲስ ሲመሠርቱ የመሥራች አባላትን ቁጥር ወደ ስምንት አድጓል፤ ይህም የሆነው ካለው ጥቅም አንጻር ሥራ ለማምጣት እንዲሁም የድርጅቱን ደረጃ ወደ ደረጃ ሰባት ከፍ በማድረግ ለማሻሻል እንደሆነ የድርጅቱ መሥራች ጠቅሰዋል።
ድርጅቱ አጠቃላይ የውሃ ሥራዎችን የሚሠራ ሲሆን በዋተር ሰፕላይ ኤክስፓንሽን ሥራዎች ላይ ደግሞ በሠፊው እየሠራ ይገኛል። እንዲሁም በሠብ ኮንትራት ቀለል ያሉ የኮንስትራክሽኝ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። የድርጅቱ መሥራቾች ያላቸው የዘጠኝ ዓመት የሥራ ልምድ ሥራዎችን በአግባቡ ማከናወን እንዲችሉ አድርጓቸዋል። ለዚህም ማሳያ ይሆን ዘንድ የራሳቸውን ሕይወት በማሻሻል ብሎም ለሌሎችም የሥራ እድል መፈጠር ችለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ድርጅቱ ሲመሠረት የነበረው መነሻ ካፒታል ዐሥራ ስምንት ሺሕ ብር ነበር፤ አሁን ከዐምስት መቶ ሺሕ ብር በላይ ካፒታል በማድረስ አቅሙን ማሳደግ ችሏል። እንዲሁም ለስምንት ዜጎች ቋሚ እንዲሁም ለዐምስት ዜጎች ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠር ችሏል።
ድርጅቱ ሥራዎችን የሚሠራው ጨረታ በመከታተል ብቻ ነው። በየወረዳው ለኢንተርፕራይዝ ብቻ ተብለው የሚወጡ ሥራዎችን (ጨረታዎችን) በመከታተል እና በመወዳድር እና በማሸፍ በዓመት አንድ ወይም ሁለት ሥራዎችን ይሠራል። በድጋሚ ከተመሠረተ በኋላ ዐሥራ ዐምስት የሚጠጉ ፕሮጀክቶን ሠርቶ ማስረክብ ችሏል።
አቶ ጀማል 2merkato.com ለጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ያዘጋጀውን የከፍታn አገልግሎት መጠቀም ከጀመሩ በኋላ በጣም እንደወደዱት ገልፀዋል። ይበልጥ ደግሞ በፊት ይከታተሉ የነበረው በኢሜይል ነበር። አሁን ደግሞ የሞባይል መተግበሪያ መጠቀም መጀመራቸው ሌሎች ዘርፎችን ማየት እንዳስቻላቸው እና ስለወደፊት ምን መሥራት አለብን? ምን መሥራት እንችላለን? የሚለውን በደንብ በማጤን የወፊት የሥራ አቅጣጫቸውን እንዲያስተካሉ እንደረዳቸው ገልጸዋል።
የኮቪድ ተፅዕኖ
በኮቪድ ወቅት ለድርጅቱ የነበረው ሁኔታ በጣም ጥሩ የሚባል ነበር፤ ምክንያቱም በነበረው ሁኔታ ለተለያዩ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ጣቢያዎች እና ሌሎች ድርጅቶች የቧንቧ ቦኖ ውሃ እና እጅ መታጠቢያ መሠራት አለበት ስለተባለ ይህንን በመሥራት ድርጅቱ በጣም መጠቀም ችሏል።
ምክር እና ዕቅድ
የድርጅቱ መሥራች “አንድ ሠው ሥራ ሲሠራ የራሱን ሥራ አክብሮ መሥራት መቻል አለበት። የተሰጠውን ሥራ በጥራት እና በጊዜ ለማስረከብ ቢሠራ ውጤታማ መሆን ይችላል።” ሲሉ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።
ድርጅቱ ከዐሥር ዓመት በኋላ (2021 ዓ.ም.) የደረጃ አቅሙን ወደ ደረጃ አንድ ለማድረስ (ለማብቃት) ዕቅድ አቅዶ እየሠራ ይገኛል።