በኢትዮጵያ ከስልሳ (60) ዓመታት በላይ ሥራ ላይ የነበረው የንግድ ሕግ አዋጅ ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትናንትናው ዕለት (በ16/07/2013 ዓም) በሙሉ ድምጽ ጸድቋል።
በምክር ቤቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ መሰረት አባተ የንግድ ሕጉን ረቂቅ አዋጅ ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል። ባለፉት 34 ዓመታት የንግድ ሕጉን ለማሻሻል የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ቢደረጉም ማሻሻያው ለምክር ቤቱ የቀረበው በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም መሆኑን አስታውሰዋል።
ቋሚ ኮሚቴው ረቂቅ አዋጁን የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ በዝርዝር አይቶ ማሻሻያ ማድረጉንም ነው የገለጹት። ኢትዮጵያ አሁን ከደረሰችበት የንግድ እንቅስቃሴ አኳያ ለንግዱ ማኅበረሰብ የተቀላጠፈ አሠራር መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ሰብሳቢዋ፣ በተለይ አገሪቷ የዓለም አቀፉ የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገውን ጥረትን የበለጠ ይረዳል ብለዋል።
የምክር ቤቱ አባላትም የሕጉ መሻሻል በተለይ በንግዱ ዘርፍ የሚታዩ ህገወጥ አሰራሮችን ለማሻሻልና ፍትሃዊ የንግድ ስርዓት ለመዘርጋት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
አሁን የጸደቀው የንግድ ሕግ ባለፉት ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ባሉ ጊዜያት ውስጥ በሀገር ውስጥም ሆነ በአለም አቀፉ የንግድ ስርዓት ላይ የተስተዋሉ ለውጦችን እና ዘመናዊ አሰራሮችን ከግምት ያስገባ ሕግ መሆኑን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በድረ ገጹ አስነብቧል።
የዜና ምንጮች፦ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የፌስቡክ ገጽ እና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ድረ ገጽ