መነሻ / የጥቃቅን እና አነስተኛ መረጃ / ወቅታዊ መረጃ / መግቢያ የተሰኘ የዴሊቨሪ እና የቢዝነስ ሊስቲንግ መተግበሪያ አገልግሎት ላይ ዋለ
megbia-logo

መግቢያ የተሰኘ የዴሊቨሪ እና የቢዝነስ ሊስቲንግ መተግበሪያ አገልግሎት ላይ ዋለ

ኢቢዝ ኦንላይን ሶሉሽንስ ኃ.የተ.የግል ማኅበር “መግቢያ” (megbia.com) የተሰኘ አዲስ የሞባይል መተግበሪያ መልቀቁን አስታውቋል። ይህ መተግበሪያ ተጠቃሚዎች በአቅራቢያቸው የሚገኙ ቢዝነሶችን በቀላሉ እንዲያገኙ ከመርዳቱም በላይ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ከየተኛውም ቦታ ሆነው ምግብ አዘው እንዲደርሳቸው ያስችላል። መተግበሪያው ሙሉ በሙሉ የተሠራው የኢትዮጵያ ትልቁ የቢዝነስ ፖርታል የ 2merkato.com ባለቤት በሆነው ድርጅት ባለሙያዎች ነው።

ኢቢዝ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሬስቶራንቶች እና በሺህዎች የሚቆጠሩ ልዩ ልዩ ቢዝነሶች መተግበሪያው ላይ እንደሚገኙ ገልጿል። ተጠቃሚዎች መተግበሪያውን በመጠቀም የፈለጉትን ምግብ ከበርካታ ሬስቶራንቶች አማርጠው ያሉበት ድረስ እንዲመጣላቸው ማዘዝ ይችላሉ።

በኢቢዝ ኤዲተር እና የፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት አዲስ አሰፋ፣ “ፕሮጀክቱ እዚህ ደረጃ ለመድረስ ሁለት ዓመት ሙሉ ተለፍቶበታል። የመጀመሪያው ዓመት የቢዝነስ ጽንሰ ሐሳቡን ለማዳበር እና መረጃ ለመሰብሰብ የዋለ ሲሆን፣ ሁለተኛው ዓመት ደግሞ መተግበሪያውን በመሥራት እንዲሁም የቢዝነስ ጽንሰ ሐሳቡን እና መረጃውን በማጥራት አልፏል” ሲሉ ያስረዳሉ።

አቶ አዲስ መተግበሪያውን ለአጠቃቀም ምቹ እና ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ ብዙ ታስቦበታል ብለዋል። መተግበሪያው በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ሲሆን፣ ተጠቃሚዎች በቀላሉ ስልካቸውን በማወዘዋዝ ቋንቋውን መለወጥ ይችላሉ።

በመግቢያ መተግበሪያ፣ ተጠቃሚዎች ቢዝነሶችን በቢዝነሱ ስም እና ዓይነት፣ እንዲሁም በሚገኝበት ሰፈር ስም ፈልገው ማግኘትም ይችላሉ። አቶ አዲስ እንደሚሉት እንዲህ ያለው ገጽታ፣ በተለይ እንደ አዲስ አበባ ብዙ ሰው ቦታዎችን በመንገድ ስያሜ ሳይሆን በሰፈር ስም በሚያውቅበት ሁኔታ እጅግ ጠቃሚ ሆኖ ይገኛል። በተጨማሪም በስልክ ላይ ባለ መገኛ ጠቋሚ (location service) መሠረትም ቢዝነሶችን ማሰስ ይቻላል።megbia-delivery

“ምግብ እና መጠጥ አማርጦ ማዘዝ በጣም ቀላል እና አስደሳች በሆነ መንገድ ቀርቧል። አሁን ላይ ከመቶ ያህል ሬስቶራንቶች መግቢያን ተጠቅሞ ምግብ እና መጠጥ ማዘዝ የሚቻል ሲሆን፣ በየዕለቱ ደግሞ በርካታ ሬስቶራንቶች እየተጨመሩ ይገኛሉ። ያለ ጥርጥር ሁሉም ሰው የሚወደውን ዓይነት ምግብ ከሚመርጠው ሬስቶራንት ፈልጎ የማግኘት ዕድል አለው” ይላሉ አቶ አዲስ።

መተግበሪያው በአንድሮይድ በጉግል ፕሌይ ስቶር የቀረበ ሲሆን፣ መግቢያ የአፕል ስልክ ላላቸው ተጠቃሚዎች ደግሞ በቅርቡ ዝግጁ ሆኖ እንደሚቀርብ ተገልጿል።
ኢቢዝ 6131 በሚል ቁጥር ያደራጀው የጥሪ ማዕከል ለመግቢያ አገልግሎት ድጋፍ ይሰጣል፤ የተጠቃሚዎችን ትዕዛዞች ለማስተላለፍ እና ጥያቄዎችን ለመመለስም ይውላል። በተጨማሪም፣ ደንበኞች መተግበሪያውን መጠቀም ከተቸገሩ ወይም የኢንተርኔት ግንኙነት ከተቋረጠባቸው፣ ቀጥታ 6131 ላይ በመደወል ያሻቸውን ማዘዝ ይችላሉ።

ኢቢዝ ኦንላይን ሶሉሽንስ ኃ. የተ. የግል ማኅበር ፣ ለ11 ዓመታት በላይ በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ትልቁ የቢዝነስ ፖርታል የ 2merkato.com ባለቤት ነው።

የዜና እና የምስል ምንጭ፦ ኢቢዝ ኦንላይን ስፕሉሽንስ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር

ይህንንም ይመልከቱ

kefta-care-training-2

ከፍታ ለ20 ኢንተርፕራይዞች ሥልጠና ሰጠ

ከፍታ ከኬር ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ለ20 በሴቶች ለሚተዳደሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ሥልጠና ሰጠ። ሥልጠናው ያተኮረው …