መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / “የእኛን ሥራ ብዙ ሰው ይሠራዋል የእኛን ሀሳብ ግን ማንም ሊሠራው አይችልም” ቲኬ ማሽን የመገጣጠም ሥራ
tk-machine-assembly

“የእኛን ሥራ ብዙ ሰው ይሠራዋል የእኛን ሀሳብ ግን ማንም ሊሠራው አይችልም” ቲኬ ማሽን የመገጣጠም ሥራ

ቲኬ ማሽን የመገጣጠም ሥራ የተመሠረተው በ 2007 ዓ.ም በአቶ ሲሳይ ደጉ እና በጓደኛቸው መሥራች አባልነት ነው። ድርጅቱ የሚሠራው ሥራ ማሽን የመገጣጠም ሥራ (Assembling) ነው። በአጭር ጊዜ ብዙ ማሽኖችን የመገጣጠም እና የማምረት አቅም አለው። ከዚህ በተጨማሪ የአሉሚኒየም ምርቶችን ያመርታል።

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች

  • ፖምፓ (ፊውል ፓምፕ) ቴስተር
  • ኖዝል ቴስተር
  • ስፒኒንግ ማሽን
  • የአሉሚየም ምርቶች፦  ማኅበረሰቡ የሚጠቀምባቸው እንደ ድስት፣ የድስት ክዳን ፣ የአሉሚኒየም መዘፍዘፊያዎችን እና ሌሎችም የአሉሚኒየም ተያያዥ ምርቶችን
  • ድርጅቱ በተጨማሪ አልጋ፣ በሮች፣ መስኮቶች እንዲሁም የብረት እና  የአሉሚኒየም ምርቶችን  ያመርታል።

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

አቶ ሲሳይ ድርጅቱን ከመመሥረታቸው በፊት በጋራዥ ሥራ ውስጥ ተቀጥረው በመሥራት የዐሥራ ሁለት ዓመት የሥራ ልምድ አላቸው። ይህም የሥራ ልምድ ከድርጅቱ ምሥረታ በኋላ ለፖምፓ (ፊውል ፓምፕ) ቴስተር ምርት አሠራር ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል። ድርጅቱ ሲመሠረት መሥራቾች ሁለት የነበሩ ቢሆንም በቡድን መሥራት ትልቅ ውጤት እንደሚያመጣ መሥራቾቹ ስላመኑበት ተጨማሪ ሁለት አባላትን በመጨመር አሁን ላይ አራት መሥራች አባላት በድርጅቱ ውስጥ ይገኛሉ። ማሽኖችን መገጣጠም ከመጀመራቸው በፊት የጥገና አገልግሎት ለ4-5 ይሰጡ ነበር።

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች ከውጭ ሀገር የሚመጡ ምርቶችን የሚያስቀሩ እና ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ የሚያድኑ እንዲሁም በጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው። ለምሳሌ ፊውል ፓምፕ ቴስተር አንዱ ተጠቃሽ ነው።

አቶ ሲሳይ በጋራዥ ሥራ በሚሠሩበት ጊዜ የተገነዘቡት ነገር የማሽን ሥራ ትልቅ ችግር ወይም እጥረት ነበር። ስለዚህ ይህን ችግር የሚቀርፍ ነገር ብንሠራ ውጤታማ እንሆናለን በማለት ነው ወደ ድርጅቱ ምሥረታ የገቡት።

ቲኬ ሲመሠረት በሃያ ሺህ ብር ካፒታል ነበር። ድርጅቱ በአሁን ወቅት  የካፒታል አቅሙ ሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር ደርሷል። ከዚህም በተጨማሪ የኢንጂነሪንግ እውቀትን ለብዙ ሠራተኞችን አሰልጥኖ በማብቃት የሙያው ባለቤት አድርጓል። እንዲሁም በየዓመቱ ዐሥራ አምስት ለሚሆኑ የቴክኒክና ሙያ ተማሪዎች የአፕረንቲስሺፕ (apprenticeship) ዕድል ሲሰጥ ቆይቷል፣ እየሰጠም ይገኛል። ድርጅቱ በሚሠራቸው ሥራዎች ጥራት አማካኝነት ተመርጠው በወረዳ ቲዲኤስ የሚባል ለኢንተርፕራይዞች የንግድ አገልግሎት የሚያገለግል ቤት ለመሥራት ተመርጦ ሠርቶ ለወረዳው አስረክቧል። ድርጅቱ ጥሩ ልምድ ነው የሚለው ነገር በወቅቱ ትክክለኛ ባለሙያ ለሥራው ደጋፊ አድርጎ ማስገባቱ ለሥራው እድገት ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክቷል። በአሉሚኒየም ሥራ ከውጪ ሀገር ከባለሙያዎች ጋር በመሆን ልምድ ቀስመዋል – መሥራቾቹ። ትክክለኛ ዘርፍ ውስጥ ያለ ሰውን ማናገር ሥራው ላይ ትልቅ ጠቃሚ አስተዋፅዖ አለው።

ድርጅቱ አሁን ላለበት የስኬት ደረጃ ሊበቃ የቻለው አንደኛ በአምራች ዘርፍ  ውስጥ ለመግባት ትልቅ ሥራዎችን መሥራቱ፤ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ምንም ዓይነት ችግር አለመኖሩ ነው። ሰዎች የሚጣሉባቸው እና ድርጅቶች የማያድጉባቸ መንገዶች አንዱ እኩል የጋራ ተጠቃሚነት አለመኖር ነው፤ ቀጥሎ ደግሞ የወሰዱትን ሥራ በሌሎች ሰዎች የሚሸፈን ከሆነ እና የተስተካከለ የፋይናስ አሠራር ከሌለ ለድርጅት መውደቅ ትልቅ መንስኤዎች እንደሆኑ የድርጅቱ ባለቤት ገልጸዋል። ይህም ድርጅት እነዚህ ችግሮች በመቅረፉ ነው ወደ እድገት ማማ ሊወጣ የቻለው።

ድርጅቱ ሥራ የሚሠራው በሰው በሰው ሲሆን ቀጥሎ ደግሞ የሥራ ቦታው ሱማሌ ተራ እንደመሆኑ ብዙ ማሽኖች የሚጠገኑት እና የሚመረቱት እዚህ አካባቢ ስለሆነ ቦታውም ትልቅ አስተዋፅዖ አለው። ሁለተኛ ደግሞ የአሉሚኒየም ሥራው ነው ይህም ሥራ ለሕብረተሰቡ አስፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በማምረት ያቀርባል፤ በዚህ ደግሞ ማኅበረሰቡ ራሱ ምርቱን በመፈለግ ይመጣል። አሁን ደግሞ በቅርቡ የሚለቀቅ የቴሌግራም ቻናል እያዘጋጀ ነው።

የኮቪድ ተፅዕኖ

ኮቪድ ለድርጅቱ መልካም አጋጣሚ ነበር ምክንያቱም ሥራ የለም ብለው አልተቀመጡም። የጊዜውን ችግር የሚፈታ መፍትሔ በማምጣት ከእጅ ንክኪ የራቀ የእጅ ማስታጠቢያ በመሥራት ከአራት መቶ እስከ ስድስት መቶ ሺህ ብር ሊያገኙ ችለዋል። ወደ ገበያ ቀጥታ አልገቡም እንጂ በመዲናዋ ላይ የድርጅቱ የእጅ መታጠቢያ በደንብ ይታወቃል።

ምክር እና እቅድ

ድርጅቱ ከምስት አመት በኋላ፦ የድርጅቱ ምርት በአዲስ አበባ የታወቀ ይሆናል፤ አንድ ሚሊዮን ምርቶችን ለማህበረሰቡ ያከፋፍላል። ቢያንስ ቢያንስ ሃምሳ የሽያጭ ሠራተኞች እና ሃምሳ አምራች ሠራተኞች በድርጅቱ ውስጥ ይቀጠራሉ። የድርጅቱ የካፒታል ጣራ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊየን ብር ይደርሳል።

አቶ ሲሳይ የከፍታን አገልግሎት ያውቁታል አባል የመሆን ፍላጎት አላቸው ሰፊ የሥራ እድል እንድሚፈጥርላቸውም ያምናሉ።

ሰዎች መሠረታዊ ዕውቀት ካላቸው በግላቸው ቢሠሩ ይመረጣል፤ ብዙ መሥራት ይችላሉ። አዲስ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚገቡ ሰዎች አምራች ለመሆን ይግቡ – አገልግሎት ለመስጠት ብቻ አይግቡ። ቲኬ ድርጅትን ዋጋ ያስከፈለው ይህ ነበር ለአራት እና አምስት አመት አገልግሎት ብቻ መስጠቱ እና ወጥ የሆነ ሽያጭ አለመኖር ትልቅ ዋጋ አስከፍሎታል። “ያኔ እንደ ተመሠረተ ቶሎ አምራች ብንሆን ኖሮ ትልቅ ደረጃ መድረስ እንችል ነበር። ስለዚህ አዲስ ጀማሪዎች ወደ ሥራው ሲገቡ መሥራት ማንኛውንም ፈተና ለማለፍ ቁርጠኝነት እና የሚሠራው ሥራ የሚታይ እና የሚጨበጥ መሆን አለበት። በመጨረሻ ምንም አይነት ምርት ሲያመርቱ ወጥ የሆነ ሽያጭ በጣም አስፈላጊ ነው።”ሲሉ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …