ጋሻ አነስተኛ የፋይናንስ (ማይክሮፋይናንስ) ተቋም አክስዮን ማኅበር በአነስተኛ ንግድ ላይ ለተሰማሩ እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተ ሰብ ክፍሎች የብድር፣ የቁጠባ እና የአረቦን አገልግሎት ለመስጠት በ1990 ዓ.ም. ተቋቋመ።
የጋሻ አገልግሎቶች፦ የቁጠባ፣ የብድር እና የአረቦን አገልግሎቶች
- የቡድን ብድር ይህ የብድር ዓይነት አነስተኛ ገቢ ላላቸው የንብረት ወይም የደመወዝ ዋስትና ማቅረብ ለማይችሉ ነገር ግን በቡድን መደራጀት ለሚችሉ ደንበኞች የሚሠጥ ሲሆን የብድር መጠኑም ከ1,000- 200,000 ብር ድረስ ነው።
- ልዩ ብድር ይህ የብድር ዓይነት በቡድን መደራጀት ለማይፈልጉ ነገር ግን በግላቸው ዋስትና አቅርበው መውሰድ ለሚፈልጉ የተጀመረ እና ንግድ ሥራ ላላቸው የሚሰጥ ሲሆን የብድር መጠኑም ከ1,000-200,000 ብር ድረስ ነው፤ ዋስትናው የቤት ካርታ፣ የመኪና ሊብሬና የደመወዝ ዋስትና ሊሆን ይችላል።
- የፍጆታ ብድር ይህ የብድር ዓይነት በቡድን የመንግሥትም ሆነ መንግሥት ነክ ያልሆነ ድርጅት ሠራተኞች ደመወዛቸውን ዋስትና በማድረግ የሚሰጥ የብድር ዓይነት ነው። ደንበኞቹ ባላቸው ደመወዝ መጠን ከ1,000-10,000 ብር የሚወስዱበት የብድር ዓይነት ነው። ብድሩን ደንበኛው ለፈለጉ ዓይነት አገልግሎት መጠቀም ይችላሉ።
- የግዴታ ቁጠባ ጋሻ ብድር ለሚሰጣቸው ደንበኞች ከብድር ስርጭት በፊት እና ከብድር ስርጭት በኋላ የሚሰበሰብ የቁጠባ ዓይነት ሲሆን፤ አከፋፈሉም በሳምንት ወይም በየሁለት ሳምንት እንዲሁም በየወሩ የሚሰብሰብ የቁጠባ ዓይነት ነው። ይህን ቁጠባ ብድሩ ተከፍሎ ሳያልቅ ማውጣት አይቻልም፤ ለዚህም የቁጠባ ዓይነት ጋሻ በዓመት 7 በመቶ ወለድ በዓመት ይከፍላል።
- የውዴታ ቁጠባ ይህ የቁጠባ ዓይነት ማንኛውም ግለሰብ በፈለገበት ሰዓት በፈለገበት ጊዜ ያለምንም ቅደመ ሁኔታ የሚቆጠብ የቁጠባ ዓይነት ሲሆን ጋሻም ለዚህ የቁጠባ ዓይነት ጠቀም ያለ ወለድ 9 በመቶ በዓመት ይከፍላል፤ ይህ ቁጠባ ደንበኛው በፈለገ ጊዜ ማውጣት ይችላል።
- የግዜ ገደብ ቁጠባ ጋሻ በጊዜ ገደብ ለሚያስቀምጡ ደንበኞች የተሻለ ጥቅም የሚያስገኝ ክፍያ ይከፍላል። ይህን ዓይነት ቁጠባ ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ድርጅት ቢያንስ ለ6 ወር እና ከዛ በላይ ከብር 100,000 ጀምሮ ሲያስቀምጥ የሚያገኙው የቁጠባ ዓይነት ነው። ጋሻ ለዚህ የቁጠባ ዓይነት በዓመት 12 በመቶ ወለድ ይከፍላል።
ጋሻ አሁን ላይ እየሰጠ ያለው የኢንሹራንስ አገልግሎት ደንበኞችን ከድንገተኛ አደጋ ለመከላከል ነው፤ ይህ አገልግሎት ተግባራዊ የሚሆነው በቡድን ብድር ደንበኞች ላይ ብቻ ነው። ደንበኛው ከጋሻ የብድር አገልግሎት አግኝቶ ብድሩን ሳይከፍል ህይወቱ ቢያልፍ ጋሻ ሙሉ ለሙሉ ብድሩን ከኢንሹራንስ ቋት አውጥቶ ይሸፍናል። ይህን አግልግሎት የሚያገኘው ደንበኛ አስቀድሞ በብድር መጠኑ መሰረት የብድሩን ከ1-2% ፕሪሚየም መክፈል ይኖርበታል።
- ጋሻ የብድር ደንበኞችን በዓመት የሚታሰብ ወለድ በብድር መጠን ላይ የማይቀናነስ እንደ ብድር አይነቱ ከ 21-23% ያስከፍላል ነገር ግን ደንበኛው ወለድ የሚከፍለው ለተጠቀመበት ጊዜ ብቻ ነው፤
- ጋሻ ቁጠባን ለማበረታታም ከ7-12 % ወለድ ለደንበኞች ይከፍላል፤
- በተጨማሪም በሁሉም የብድር ዓይነት ላይ 3 % የአገልግሎት ክፍያ ያስከፍላል።
ጋሻ፦ ምሥረታ፣ ራዕይ፣ ተልዕኮ እና ዓላማዎች
ጋሻ ለባለድርሻ አካላትና ለደንበኞቹ ስለድርጅቱ አመሠራረትና ስለሚሰጣቸው አገልግሎቶች ግልጽ የሆነ ማስረጃ በመስጠት በብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ቁጥር MFI/006/98, በ15/5/98 እና በአዲስ አበባ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ በቁጥር 27025, ግንቦት 26, 1990 ዓ.ም. በተከፈለ 200,000 ብር እና በተፈረመ 800,000 ብር ካፒታል በ763 ባለአክሲዮኖች ተመሰረተ።
የጋሻ ራዕይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተ ሰብ ክፍሎች ህልማቸውን ዕውን ሲያደርጉና እምቅ ችሎታቸውን ሲጠቀሙ ማየት ነው።
የጋሻ ተልዕኮ በገጠርና በከተማ ለሚንቀሳቀሱ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በሙሉ አዳዲስ ፈጠራን የሚያራምዱትን ጠንካራ ቁጠባ መር መካከለኛ የፋይናንስ ተቋም በመሆን ማገልገል ነው።
ጋሻ አነስተኛ ፋይናንስ ተቋም አክሲዮን ማህበር ዋናውና የረዥም ጊዜ ዓላማው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተ ሰብ ክፍሎች ድህነትን ለማስወገድ የሚያስችላቸውን ተቋም መመሥረትና ማጎልበት ነው።
ስለዚህም ጋሻ የሚከትሉት ዝርዝር ዓላማዎች አሉት።
- በአነስተኛ የንግድ ተግባር ላይ ለተሰማሩ የኅብረተ ሰብ ክፍሎች የተለያዩ ዓይነት የገንዘብ ነክ አገልግሎቶች ለመስጠት የሚችል ብቁ የሆነና ባለብዙ ቅርንጫፍ ወደ ሆነ የገንዘብ አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ማደግ፣
- በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ በሚገኙ ኅብረተ ሰብ ክፍሎች ዘንድ የቁጠባን ጽንሰ ሃሳብና ልማድ ማበረታታት፣
- የአገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑት የኅብረተ ሰብ ክፍሎች ልዩ ልዩ የቁጠባና የብድር አገልግሎቶችን ሊያገኙ የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸትና ማስተባበር፣
- በአነስተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችንና በስራቸውም ተቀጣሪ የሆኑትን ግለሰቦች ገቢ ማሳደግ፣
- የደንበኞች ራስን የመቻል እና የተሳትፎ ደረጃ በግለሰብ ሆነ በቡድን ደረጃ እንዲጎለብት ማበረታታት።
- ሴቶች በአነስተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ በአክስዮን ባለቤትነት፣ በቦርድ አባልነት፣ በተበዳሪነት፣ በቡድን እና በኅብረት አመራርነት፣ በጋሻ መደበኛ ሠራተኛነት ደረጃ እንዲሳተፉ ማበረታታት፣
- ከመንግሥት፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እና ከሌሎች አግባብነት እና በተለያየ መንገድ ተጠቃሚና ተሳታፊ ከሚሆኑ አካላት ጋር ጤናማ የሆነ የሥራ ግንኙነት በመፍጠር ለአነስተኛ የንግድ እንቅስቃሴና በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የኅብረተ ሰብ ክፍሎች ለሥራ ምቹ የሆነ ሁኔታን መፍጠር።
ጋሻ የአነስተኛ ፋይናንስ ተቋም አድራሻ
ቅርንጫፍ | ስልክ ቁጥር |
---|---|
ዋና መሥርያ ቤት (ሃያ ሁለት) | 0953 967737 |
መርካቶ ቅርንጫፍ | 0923 121645 |
እንጦጦ ቅርንጫፍ | 011 8685464 |
ኮልፌ ጎጃም በረንዳ ቅርንጫፍ | 0920 579120 |
ቢሾፍቱ ቅርንጫፍ | 011 4334558 |
የካ ቅርንጫፍ | 011 6587621 |
አዳማ ቅርንጫፍ | 022 1117670 |
ማስታወሻ፦ ይሄ መረጃ የተዘጋጀው ለጋሻ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አክስዮን ማኅበር በአካል ሄዶ በመጠየቅ በተገኘው መረጃ ላይ ተመሥርቶ ለጥቃቅን እና አነስተኛ ድርጅቶች በሚጠቅም መልኩ ተቀናብሮ ነው።