ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅትም ምርቱን ሙሉ በሙሉ ከእንጨት ሥራዎች እየሠራ ይገኛል።
ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት
አቶ ቃለአብ የእንጨት ሥራ ድርጅት ሊመሠርቱ የቻሉት ከልጅነታቸው ጅምሮ የሚያውቁት ሥራ በመሆኑ ነው። ወደ እንጨት ሥራ ዘርፍ የተቀላቀሉበትን አጋጣሚ እንዲህ ብለው አካፍለውናል። ሥራውን መርጠውት ሳይሆን አንድ የሰፈራቸው ሰው ሰፈር ከምትውል እኔ ጋ ቀለል ቀለል ያለ ሥራ አለ፤ ሥራ ብሎ አስቸገባቸው። እሳቸውም ረዳት ሆነው በመጀመር እስከ ሙሉ ረዳት በመቀጠልም ደግሞ ሙሉ አናጺ በመሆን በሥራው ላይ የሃያ አራት ዓመት የሥራ ልምድ ማካበት ቻሉ። ይሄንን ልምዳቸውን ተንተርሰው እና በራሴ ብሠራ የተሻለ ገቢ አገኛለሁ ብለው ከአራት ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የራሳቸውን የእንጨት እና ብረታ ብረት ድርጅት መሠረቱ።
ከመንግሥት በተቀበሉት ሼድ፣ በፊት ሲሠሩበት የነበረው ድርጅት በሰጣቸው አንድ ማሽን እና ከሌላ ሰው ደግሞ በወሰዱት ድሪል፤ እንዲሁም ሌሎች እቃዎችን ደግሞ ከሚያውቋቸው ሱቆች በዱቤ በመውሰድ ሃያ ሺህ ብር (ብር 20,000) በሚጠጋ ካፒታል ድርጅቱን መሠረቱ። ድርጅቱ አሁን ላይ የካፒታል አቅሙን ወደ ዐምስት መቶ ሺህ ብር (ብር 500,000) አሳድጓል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ እንደ ሥራው ዐይነት ከፍ ወይም ዝቅ ሊል የሚችል ሆኖ ለስድስት ሴቶች እና አራት ወንዶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
ድርጅቱ ሥራዎችን የሚሠራው በብዛት በራሱ በማፈላለግ ሲሆን እንዳንዴ ደግሞ ቀለል ያሉ ጨረታዎች ላይ በመሳተፍ እንዲሁም ከመርካቶ እና ከክልል ከተሞች በሚመጡ ትዕዛዞች ነው። የድርጅቱ ምርት የማምረት አቅም እንደ ሥራው ዐይነት እና መጠን የሚወሰን ቢሆንም ለምሳሌ የቢሮ ጠረጴዛዎችን በአንድ ሳምንት ውስጥ ሰላሣ የማምረት አቅም አለው፤ ኖርማል ጠረጴዛ እና የቲቪ ማስቀመጫ ደግሞ ባንድ ሳምንት አርባ ማምረት ይችላል። ያመረታቸውን ምርቶችም አሁን ትንሽ የጸጥታ ሁኔታ እና የመንገድ መዘጋት ስላቀዘቀዘው ነው እንጂ በፊት ቢሾፍቱ (ደብረዘይት)፣ አዳማ (ናዝሬት)፣ ጎንደር፣ ወሎ፣ ወዘተ ምርቶችን ለነጋዴዎች በማቅረብ ይሠሩ። ይሁን እና 2merkato.com ለጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ያዘጋጀውን የከፍታ አገልግሎት በመጠቀም የሥራ ዕድላቸውን እያሰፉ ይገኛሉ።
ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች
- ቁምሳጥን
- ጠረጴዛ
- ኪችን ካቢኔት
- በእንጨት እና ብረት ሙሉ የቢሮ የፓርቲሽን ሥራ
- ቲቪ ስታንድ እና
- በራሳቸው በአቶ ቃለአብ ዲዛይን የተነደፉ የጫማ መደርደሪያዎችን ይሠራል።
የኮቪድ ተፅዕኖ
በኮቪድ ወቅት ድርጅቱ በትልቅ ኪሳራ ውስጥ አልፏል። የድርጅቱ የሥራ መጠን በጣም ቀንሶ ነበር። ይህም የሆነው አንደኛ በጣም ፍርሃት ነበር፤ ሁለተኛ የእንጨት ሥራ በባሕሪው ንክኪ ያለው እና አብሮ የሚሠራ ሥራ ስለሆነ ይህን ለማድረግ ባለመቻሉ ሲሆን፤ እንዲሁም ሥራ የሚያሠራ ሰው መቀነሱ ነበር። እነንኝህ ነገሮች ድርጅቱ በኮቪድ ጊዜ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዲያልፍ አድርገውታል ሲሉ የድርጅቱ መሥራች ተናግረዋል።
ምክር እና ዕቅድ
ወደ እንጨት ሥራ ለሚገቡ ሰዎች እሳቸው የሚሉት ምንም ያህል የረጅም ጊዜ የሥራ ልምድ ቢኖራቸውም ሥራ መፈለግ ከባድ ነው፤ በመቀጠል ደግሞ የሥራ መስመር ውስጥ ለመግባት ቀላል አለመሆኑ ሌላው ተጠቃሽ ነገር ነው። ግን ዐላማ ካለ እና ምንም አማራጭ እንደሌለ አስበው ከገቡ ውጤታማ መሆን ይቻላል ብለዋል። ሥራው በትንሽ ካፒታል የሚሠራ ሥራ ነው። ነገር ግን ከፍ ለማለት ሲፈለግ ለምሳሌ ጨረታ ለመሳተፍ ካፒታል ይፈልጋል። የዚህም ምክንያቱ ሥራ በጨረታ ሲመጣ እና ሲሠራ የሥራ ማስኬጃውን ግማሽ አሸናፊው ነው የሚሸፍነው፤ ሃያ አምስት በመቶ (25%) መጀመርያ ላይ ይለቀቃል። ተጨማሪ ክፍያ የሚለቀቀው ደግሞ ሥራው ታይቶ፣ ታምኖበት እና ኮሚቴ አይቶት ስለሆነ ብዙ ሂደት አለው። ስለዚህ የገንዘብ አቅም ያስፈልጋል። የገንዘብ አቅም ላለው ድርጅት ጨረታ ላይ ተሳትፎ ካሸነፈ፣ ሙሉውን ሥራ ወስዶ አጠቃላይ ሠርቶ ማስረከብ በጣም ውጤታማ ያደርጋል። ገና ጀማሪ ከሆነ ግን በትንሽ በትንሹ ቢሠራ ጥሩ ነው።
ድርጅቱ ወደ ፊት በተሻለ እና በሰፊ ሁኔታ ለመሥራት ዕቅድ አለው፤ አሁን ያለው ነገር ከተስተካከለ ሥራው ይሻሻላል ብለዋል።
የድርጅቱን አገልግሎት መጠቀም የሚፈልጉ የድርጅቱን ስልክ በዚህ ሊንክ በመግባት ዐይተው መደወል ይችላሉ።