መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / አጸደ፣ ነሲባ እና ጓደኞቻቸው የእንጀራ መጋገር ሥራ

አጸደ፣ ነሲባ እና ጓደኞቻቸው የእንጀራ መጋገር ሥራ

ይህ ኢንተርፕራይዝ የተመሠረተው በ 2001 ዓ.ም በ ወ/ሮ ነሲባ ራህመቶ እና በዐሥራ ዘጠኝ መሥራች አባላት ነው። ድርጅቱ በሀያ መሥራች አባላት ቢመሰረትም በነበረው አስቸጋሪ ሁኔታ ዘጠኝ አባላት የቀን ሥራ ብንሠራ ይሻለናል ብለው ሲያቋርጡ፣ አንድ አባል ደግሞ በሞት ስለተለየች በአሁን ጊዜ ዐሥር መስራች አባላት በድርጅቱ ውስጥ ይገኛሉ።

ምሥረታና ዕድገት

ወደዚህ ዘርፍ እንዴት ሊገቡ እንደቻሉ ሲያስረዱ የወረዳው ቢሮ ከዚህ በፊት ምንም ሥራ የማይሠሩ ወይም ከአረብ አገር የመጡ እና በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ የኅብረተሰቡን ክፍሎች በመሰብሰብ በሚፈልጉት ሙያ ካሰለጠነ በኋላ ሰልጣኞቹ በማደራጀት ድርጅቱን መመሥረት እንዲችሉ አድርጓል። እነሱም ይህን እድል ተጠቅመው ድርጅቱን ሊመሠርቱ ችለዋል። ይህ ደግሞ “አለኝ ብለን የምንተማመንበት ነገር እንዲኖረን ሙሉነት እንዲሰማን አድርጎናል” ሲሉ ወ/ሮ ነሲባ ጠቅሰዋል። ድርጅቱ ሲጀመር በአምስት ሺህ ብር (5000) ድጋፍ ነው። በአሁን ወቅት ሃምሳ ሺህ ብር ገደማ ካፒታል ሊያፈራ ችሏል።

ድርጅቱ ከተመሠረተ እስከ ሦስት አመት ድረስ የነበሩ ሁኔታዎች በጣም ከባድ እንደ ነበሩ የድርጅቱ መሥራች አባል ወ/ሮ ነሲባ ገልጸዋል። ከተደራጁ በኋላ እንደምንም ብለው ለሦስት አመት ቆይተው የነበረው ከባድ ሁኔታ  ቀስ በቀስ እየተሻሻለ ስለመጣ ቁጠባም ጀመሩ። ወረዳውም የባዛር እድሎችን በነጻ እያመቻቸላቸው፤ እንዲሁም ዝግጅቶች ሲኖሩ ለዝግጅቶቹ አስፈላጊውን አገልግሎት በመስጠት እየተንቀሳቀሱ እስከ 2005 ዓ.ም ድረስ ቆይተዋል።

በ2005 ዓ.ም በድርጅቱ ላይ በተነሳ የእሳት አደጋ ድርጅቱ ሙሉ በሙሉ ምንም እቃ ሳይተርፍ ተቃጥሎ ነበር። ድርጅቱ ብዙ ችግሮችን ተቋቁሞ ስለመጣ የተፈጠረው የእሳት አደጋ ተስፋ ሳያስቆርጠው ጊዜአዊ ድንኳን ወረዳው ዋስ በመሆን ከእድር በማምጣት እንዲሁም ከማህበረሰቡ በተሰበሰበ ድጋፍ እና ከሴቶች እና ህጻናት ቢሮ በተገኘ እርዳታ ሀያ ሁለት ሺህ (22,000) ብር እኩል ለሁለት ማኅበራት በመካፈል አጠቃላይ ሀምሳ ሺህ ብር (50,000) በመፍጀት እንደ አዲስ ሊቋቋም ችሏል።

ከድርጅቱ ከቃጠሎ በኋላ ከሴቶች እና ህጻናት ቢሮ ባገኘው ድጋፍ በላቀች ምጣድ ይሠራ የነበረውን ሥራ ወደ ኤሌክትሪክ ምጣድ በማሳደግ እና ቀስ በቀስ እንዳንድ አስፈላጊ እቃዎችን እንደ ጥቅማቸው ደረጃ እያሟላ ሦስት የኤሌክትሪክ ምጣድ እና አንድ የዳቦ ማሽን ሊያስገባ ችሏል። ታዲያ ይህን ለማሳካት የወረዳው ሚና ትልቅ እንደ ነበር ወ/ሮ ነሲባ ገልፀዋል፤ ለምሳሌ ደብዳቤ በመፃፍ፣ አስፈላጊውን አጠቃላይ እርዳታ በማድረግ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት እንደረዳቸው ገልፀዋል።

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

ድርጅቱ የሚሠራው እንጀራ ጋግሮ የመሸጥ ሥራ ብቻ ነው። ምክንያቱም እንጀራ ከወጪ አንጽር የሚያዋጣ ሥራ ስለሆነ ነው።  በፊት ባልትና ሞክረው ነበር፤ በጣም አድካሚ ነው ከድካሙ አንጻር ትርፉ ትንሽ ስለነበር እሱን በመተው የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅም ሞክረው ነበር። ነገር ግን ከእንጀራ ሥራ ጋር የሚሄድ ስላልነበር እሱንም በመተው በደንብ ወደሚያውቁት የእንጀራ ሥራ ሙሉ ለሙሉ ተመልሰው በሙሉ ሀይል መሥራት ጀምረዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የተማሩት ነገር ዝናብ የመታው ጤፍ ከአብሲት ጀምሮ በጣም ስለሚያስቸግር እሱን ለይቶ በወቅ ስለቻሉ እንደዛ አይነት ጤፍ ባለመሸመት ትልቅ ኪሳራ አድነዋል።

ድርጅቱ ሲመሰረት እንድ እንጀራ በአምስት ብር ነበር የሚሸጠው፤ የጤፍ ዋጋ ሲጨምር የእንጀራ ዋጋ አብሮ እየጨመረ ስለመጣ በአሁኑ ጊዜ ለሆቴሎች እና ብዛት ተረካቢዎች አንድ እንጀራ በዘጠኝ ብር ለተመጋቢ ደግሞ አንድ እንጀራ በዐሥር ብር እያቀረበ ይገኛል። እንዲሁም ድርጅቱ ሁለት በብዛት ተረካቢ ደንበኞች እና ብዙ ተመጋቢ ደንበኞች አሉት። አሁን ባላው ሁኔታ ያለምንም ማስታወቂያ በቂ ሥራ እየሰራ ይገኛል። አሁን ድርጅቱን እያስቸገረ ያለው በቂ የሆነ የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት አለመኖር ነው። ድርጅቱ በቀን አንድ ሺህ እንጀራ የማምረት አቅም አለው። በድርጅቱ ውስጥ ሁለት (አንድ ወንድ እና አንድ ሴት) ቋሚ ሠራተኞች አሉ።

ድርጅቱ ምርቱን ቢዝነስ ካርድ በመጠቀም ያስተዋውቅ ነበር አሁን ግን ታዋቂ ስለሆነ ምንም ማስታወቂያ አይጠቀሙም። ምርታችው ጥራት ያለው ስለሆነ ከሩቅ ከየካ አባዶ ድረስ እየመጡ የሚገዙ ደንበኞች አሉት።

ወደ ፊት ወደ ጥቅምት ወር 2014 ዓ.ም. ላይ ያለውን ቦታ በማስፋት ከእንጀራው ጋር የሚሆን ትንሽ እንደ ሽሮ ቤት ለመጨመር አስበው ዝግጅት እየጨረሱ ይገኛሉ።

ድርጅቱ በ2merkato ለኢንተርፕራይዞች የሚሰጠውን የከፍታ  አገልግሎት በቴሌግራም ቻናል መረጃ በመከታተል እና አስፈላጊ ጥያቄ ሲኖር በጥሪ ማዕከል በመደወል እንደሚጠቀሙ ወ/ሮ ነሲባ ገልጸዋል።

የኮቪድ ተፅዕኖ

የኮቪድ ተፅዕኖ ከባድ ነበር፤ ምክንያቱም በቀን ከሃያ እና ከሃያ ያነሰ እንጀራ ብቻ ይሸጥ የነበረበት ጊዜ ነበር። ይህ ደግሞ እንጀራው እንዲባክን አድርጓል። በነበሩ ቋሚ ደንበኞች ምክንያት እነሱን ብቻ በማገልገል ቆይቶ ቀስ በቀስ እየተሻሻለ ሲመጣ የምርቱንም መጠን እያዩ ቀንሰውት የነበረውን የምርት ሂደት ቀስ በቀስ እየጨመሩ መጥተዋል። ሥራው አሁን ደህና ነው ሲሉ ወ/ሮ ነሲባ አስረድተዋል።

ምክር

አዲስ ለሚጀምሩ የሚሰጡት ምክር ምንም ሥራ ላይ ተግባብቶ መሥራት መቻል አለባቸው፤ ከሥልጠና ጀምሮ ወይም ከመጀመሪያው ጀምሮ የሚግባቡ ሰዎች መሆን አለባቸው – ብዙ ድርጅቶች የሚፈርሱት ባለመግባባት ስለሆነ። ቀጥሎ የእንጀራ ሥራ ጽናት ይጠይቃል፤ ስለዚህ ምንም ችግር ቢፈጠር ተስፋ አለመቁረጥ ያስፈልጋል ብለው ይመክራሉ ወ/ሮ ነሲባ።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …