መንግስት ካስቀመጠው የሲሚንቶ ዋጋ በላይ በሚሸጡ የሲሚንቶ አከፋፋዮች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ አስታወቀ ፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በሲሚንቶ ግብይት ውስጥ ያሉ ህገ-ወጥ ደላሎችን ከገበያ ሰንሰለቱ በማስወጣት እየናረ የመጣውን የሲሚንቶ ዋጋ ለማስተካከል የመሸጫ ዋጋ በመተመን ከፋብሪካ አውጥተው የሚያከፋፍሉ የመንግስት የልማት ድርጅቶችና መመሪያውን አክብረው ለመስራት የተስማሙ የግል ነጋዴዎች ተመርጠው በቅርቡ ወደ ስራ መግባታቸው ይታወሳል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮው አላስፈላጊ የሲሚንቶ ዋጋ ንረትን በመቆጣጠርና ዋጋ በመተመን የኮንስትራክሽን ዘርፉ እንዳይዳከም በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
ከፋብሪካዎች ተረክበው የሚሸጡ አከፋፋዮች የሚሸጡበት የአንድ ኩንታል ዋጋ እንደየርቀቱ ከ240.20 ብር እስከ 388.10 ብር እንዲሆን የተወሰነ ቢሆንም አንዳንድ አከፋፋዮች ግን ከተቀመጠው ዋጋ በላይ በመሸጥ ላይ እንደሚገኙ በተደረገ የመስክ ምልከታ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
መንግስት ባስቀመጠው የሲሚንቶ ዋጋ መሰረት ግብይት በማይፈጽሙ የሲሚንቶ አከፋፋዮች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወሰድ ቢሮው ገልጿል፡፡
ምንጭ (የዜና እና የሲሚንቶ ዋጋ ተመን ምስል)፦ የአዲስ አበባ ከተማ ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢሮ የፌስቡክ ገጽ