መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ከበደ ደስታው እና ጓደኞቻቸው የፊኒሺንግ ሥራ

ከበደ ደስታው እና ጓደኞቻቸው የፊኒሺንግ ሥራ

ከበደ ደስታው እና ጓደኞቻቸው የፊኒሺንግ ሥራ ድርጅት የተመሠረተው በአቶ ከበደ ደስታው እና ሦስት መሥራች አባላት በ2010 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን እና የፊኒሺንግ ሥራዎችን ከውሃ ሥራ ውጪ የሚሠራ ድርጅት ነው።

ድርጅቱ የሚሠራቸው ሥራዎች

  • አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራ
  • የብሎኬት ሥራ
  • የልስን ሥራ
  • የቀለም ቅብ ሥራ
  • የሳኒተሪ ሥራ
  • የቻክ፣ ቧንቧ እና የኤሌክትሪክ ሥራዎች

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

አቶ ከበደ ወደ ፊኒሺንግ የሥራ መስክ የገቡበትን አጋጣሚ እንዲህ ሲሉ ነበር የገለጹት፤ በታዳጊነታቸው እና በወጣትነታቸው የተማሩት ትምህርት ይኸው በመሆኑ እና ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ በዘርፉ ተቀጥረው በመሥራታቸው ነው። አቶ ከበደ በፊኒሺንግ ሥራ ተቀጥረው በሠሩባቸው ሰባት አመታት ውስጥ ቀስ በቀስ አንዳንድ ቀለል ያሉ ሥራዎችን በትርፍ ጊዜያቸው እና በእረፍት ጊዜያቸው መሥራት ጀመሩ። እነዚህ ቀስ በቀስ የሚሠሯቸው ሥራዎች መጠን ሲጨምር በግል ብሠራ ደግሞ ይበልጥ ተጠቃሚ እሆናለሁ ብለው ከበደ ደስታው ፊኒሺንግ ድርጅትን መሠረቱ።

ድርጅቱ በአሁኑ ሰዓት በስፋት ሥራውን እየሠራ የሚገኘው በኮንዶሚኒየሞች ላይ ነው። በተጨማሪ ደግሞ ሌሎች ቀለል ያሉ የፊኒሺንግ እና የፈርኒቸር ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። ይህ ድርጅት ባለ ሦስት መኝታ እና ባለ ሁለት መኝታ ቤት አፓርታማ እና ቪላዎችን የኢንተርየር ዲዛየን በመሥራት የአሠሪው አቅም ጥሩ ከሆነ ይህም ማለት የጥሬ እቃ አቅርቦት ችግር ከሌለበት ከዐሥራ ዐምስት ቀን እስከ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ፊኒሺንግ ሠርቶ የማስረከብ አቅም አለው። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ 2merkato.com ለጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ያዘጋጀውን የከፍታ አገልግሎት በመጠቀም ጨረታዎች ላይ መሳተፍ ጀምሯል።

አቶ ከበደ በፊኒሺንግ ሥራ ላይ ያለው ትልቁ ተግዳሮት ሥራ ማምጣት ከዛም ያንን ሥራ በአግባቡ ተቆጣጥሮ ሠርቶ በተባለው ጊዜ ማስረከብ ነው ብለዋል። ይህ ማድረግ ከተቻለ ያ ሥራ ራሱ በራሱ ሌላ ሥራ ያመጣል፤ ስለዚህ እዚህ ላይ በደንብ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ሁለተኛ ደግሞ ከሠራተኛ ጋር ያለ ግንኙነት መልካም መሆን አለበት – በተለይ ደግሞ በዚህ ዘርፍ፤ ምክንያቱም ሥራው በራሱ ሠራተኛ ሥራ ትቶ ሌላ ቦታ ሄዶ እንዲሠራ የሚጋብዝ ነው። የአንድ ቀን ወይም የሁለት ቀን ሥራዎችን በመሃል በራሱ የሚሠራበት አጋጣሚ ይኖራል። አቶ ከበደ ከነበራቸው ልምድ እሳቸውም እዚህ ቦታ ላይ ስለነበሩ እንዴት ይህን ችግር መፍታት እንዳለባቸው ያውቃሉ። ከሠራትኛ ጋር ጥሩ የሆነ ግንኙነት መፍጠር አቻ የሌለው መፍትሔ ነው ሲሉ ተናግረዋል። ጥሩ ግንኙነት ካለ ሠራተኛው ራሱ ሥራ ያመጣል ሲሉ አክለዋል።

ከበደ ደስታው ፊኒሽኒንግ ሥራ ድርጅት በብር 300 (ሦስት መቶ ብር)  መነሻ ካፒታል ነበር የተመሠረተው፤ አሁን ላይ ለፈርኒቸር ሥራ እና ለፊኒሺንግ ሥራ የሚያስፈልጉ ማሽኞችን በበቂ ሁኔታ ማሟላት ችሏል። ከዚህ በተጨማሪ የድርጅቱ መስራቾች ጥሩ ኑኖ መኖር ችለዋል፤ እንዲሁም ዐሥራ ዐምስት ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ድርጅት ሆኗል።

የኮቪድ ተፅዕኖ

በኮቪድ ጊዜ እንቅስቃሴ በመቀነሱ ምክንያት ድርጅቱ ሥራውን አቆሞ አስጀጋሪ ጊዜ ነበር ያሳለፈው።

ምክር እና ዕቅድ

ወደ ፊኒሺንግ ሥራ የሚገቡ ሰዎች ሥራውን ወደውት እና ዐውቀውት ቢገቡ ጥሩ ነው፤ ይህም ሥራውን ለመሥራት እና ደንበኛን ለማሳመን አስፈላጊ ነው። ሌላው ደግሞ ፊኒሽንግ ሥራ ላይ ብዙ እቃዎች እና የሥራ ዘርፎች አሉ፤ ስለዚህ ይህን ማወቅ አልያም ደግሞ ሥልጠና መውሰድ ያስፈልጋል ብለው ምክራቸውን አስተላልፈዋል።

የድርጅቱ መሥራች እንደ ተሞክሯቸው የግል ሥራ መልካም እና አስቸጋሪ ነገሮች አሉት በማለት ተከታዮቹን ሃሳቦች አጋርተዋል። የግል ሥራ መሥራት ትርፋማ ያደርጋል፤ ይህ የሚሆነው ግን ጊዜን ለራስ መጠቀም ሲቻል ነው። ይህ ማለት ደግሞ የገቢ ዕድገት የሚወሰነው በራሱ በመሥራቹ የትጋትና አስተሳሰብ መጠን ነው። ወደ ፊት ትልቅ ህልም ካለው እና በተሻለ ጊዜውን ከተጠቀመ ያሰበውን ማሳካት ይችላል። በደንብ ከሠራ ያድጋል፤ ካልሠራ ደግሞ ያው ምንም ለውጥ አይመጣም። ተግቶ መሥራት ካልቻለ የግል ሥራ ባይጀምር የተሻለ ነው ብለዋል። እሳቸው ሥራውን ሲጀምሩ ትልቅ ያገኙት ልምድ ሰው ማወቅ ነው ብለዋል። ከምንም በላይ ጥቅም አለው፤ በዚህ ስር ብዙ ነገሮች ሊባሉ ቢችሉም መጨረሻው ግን ሥራ ያመጣል ሲሉ ገልጸዋል።

ድርጅቱ ወደ ፊት የተቋራጭነት ደረጃውን ወደ ደረጃ ሦስት በማሳደግ አጠቃላይ የኮንስትራክሽን ሥራዎችን የመሥራት ዕቅድ አለው።

የድርጅቱን አገልግሎት መጠቀም የሚፈልጉ የድርጅቱን ስልክ በዚህ ሊንክ በመግባት ዓይተው መደወል ይችላሉ

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …